Site icon ETHIO12.COM

በህገወጥ መንገድ ሲዘዋወሩ የነበሩ 19 ሺ 447 ጥይቶች በቁጥጥር ስር ዋሉ

መነሻቸውን ከአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ያደረጉ 19 ሺ 447 ጥይቶች እና 3 ሽጉጦች በህገወጥ መንገድ
ሲዘዋወሩ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ባደረገው ክትትል ከአዲስ አበባ ፖሊስ እንዲሁም ከአማራ እና ከኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽኖች ጋር በቅንጅት በተሰራው ስራ በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርጓል፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ መረጃ እንዳመለከተው፤ መነሻውን ከአማራ ክልል ባህርዳር ከተማ ያደረገ አንድ ህገ
ወጥ የጦር መሣሪያ አዘዋዋሪ ግለሰብ የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3 A 79848 አ.አ በሆነ ፒካፕ ተሽከርካሪ 4 ሺ 847 የክላሽ ጥይት ጭኖ መዳረሻውን አዲስ አበባ ከተማ ለማድረግ በመጓዝ ላይ እያለ በተደረገ ክትትል በቁጥጥር ስር ውሏል።

ግለሰቡ አዲስ አበባ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ሱሉልታ ከተማ ሲደርሰ ከኦሮሚያ ፖሊስ ጋር በመተባበር አዘዋዋሪው
ከነጦር መሣሪያው ነው በቁጥጥር ስር የዋለው።

በተመሳሳይ የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ3 አ.ማ 20386 በሆነ ፒካፕ ተሽከርካሪ ከአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ወልዲያ ከተማ ተጭኖ ወደ ጎንደር እንዲደርስ ታቅዶ የነበረ 14ሺ500 የክላሽ ጥይት በቁጥጥር ስር ውሏል፡፡

በህገወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረው ጥይት እና አዘዋዋሪው ደቡብ ጎንደር ዞን ንፋስ መውጫ ከተማ ላይ
ከአማራ ፖሊስ ጋር በመተባበር መያዛቸው ታውቋል።

መነሻውን አማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን ደሴ ከተማ ያደረገ አንድ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ አዘዋዋሪ ግለሰብ
በህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ ላይ በእህል ውስጥ 100 የብሬን ጥይት እና 3 ቱ ርክ ሰራሽ ሽጉጥ ደብቆ በመጫን ለማሳለፍ ያደረገው ሙከራም በጸጥታ ሃይሎች መክሸፉን መረጃው አመልክቷል፡፡

መዳረሻውን ደቡብ ክልል ከፋ ዞን ቦንጋ ከተማ ለማድረግ በመጓዝ ላይ በነበረው ህገወጥ መሣሪያ ላይ
በተደረገው ክትልል አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የካ ክፍለ ከተማ ኮተቤ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ጋር በመተባበር አዘዋዋሪው ከነጦር መሣሪያው በቁጥጥር ስር እንዲውል ተደርጓል።

ህገወጥ የጦር መሣሪያዎቹን በቁጥጥር ስር በማዋል ረገድ የህብረተሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ ሚና ማበርከቱን ያመለከተው መረጃው፤ ይህ እገዛ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቋል፡፡ – (ኢ.ፕ.ድ)

Exit mobile version