Site icon ETHIO12.COM

የኤሌክትሪክ ሀይል ማስተላለፊያ ገመድ የሰረቁት ግለሰቦች በአምስት አመት ከስድስት ወር ፅኑ እስራት ተቀጡ

1ኛ ተከሳሽ ታምራት ማቲዮስ እና 2ኛ ተከሳሽ አዱኛ ቱኒ የተባሉ የ20 አመት እድሜ ያላቸዉ ወጣት ተከሳሾች የመሰረተ ልማት አውታሮችን ለመጠበቅና እና ለመቆጣጠር በ1996 ዓ.ም በወጣዉ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የወንጀል ህግ አንቀፅ 32/1/ሀ እና የቴሌኮምዩኒኬሽንና የኤሌክትሪክ ሀይል አውታሮችን ደህንነት ለመጠበቅ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 464/97 አንቀፅ 4 ላይ የተደነገገውን በመተላለፍ በፈፀሙት ወንጀል ተከሰዋል፡፡

ተከሳሾች ያልተገባ ብልፅግና ለራሳቸው ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ የሀገርን ኢኮኖሚ በሚጎዳ ሁኔታ በኤሌክትሪክ ሀይል አውታር ላይ ነሐሴ 18 ቀን 2013ዓ.ም በግምት ከሌሊቱ 6፡40 ሰአት ሲሆን በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 03 አስተዳደር ክልል ልዩ ቦታው ጎተራ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በማሳለጫ መንገዱ ውስጥ ለምድር ባቡር መስመር ተዘርግቶ አገልግሎት እየሰጠ ከሚገኘው ንብረትነቱ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ተቋም የሆነ 33 ሜትር ርዝመት ያለው የኤሌክትሪክ ሀይል ማስተላለፊያ ከመዳብ የተሰራ ገመድ አጠቃላይ ዋጋው 53,212.5 (ሀምሳ ሶስት ሺህ ሁለት መቶ አስራ ሁለት ብር ከሀምሳ ሳንቲም) የሆነ ገመድ በመጋዝ በመቁረጥ እየጎተቱ ሳለ በአጋጣሚ ቦታው ላይ በደረሱ ሰዎች እጅ ከፍንጅ የተያዙ በመሆኑ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በፈፀሙት በኤሌክትሪክ ሀይል አውታር ላይ የተፈፀመ የስርቆት ወንጀል ተከሰው በፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት 1ኛ ልዩ ልዩ ወንጀል ችሎት ቀርበዋል፡፡

ተከሳሾች በተመሰረተባቸው ክስ ላይ የእምነት ክህደት ቃላቸውን ተጠይቀው ወንጀሉን አልፈፀምንም በማለት ክደው የተከራከሩ በመሆኑ ዐቃቤ ሕግ በክሱ የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊቱ መፈጸማቸውን ያሰረዳሉ ያላቸዉን 4 የሰው ምስክሮችን አቅርቦ ያስደመጠ ሲሆን፤ ከዚህም በተጨማሪ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አዲስ አበባ ቅርንጫፍ የተገኘና የተቆረጠውን የኤሌክትሪክ ገመድ የዋጋ ግምት የሚገልፅ የሰነድ ማስረጃ በማቅረብ ተከራክሯል፡፡ ፍርድ ቤቱም የዐቃቤ ሕግ ምስክሮችን መርምሮ ተከሳሾች እንዲከላከሉ ብይን ሰጥጧል፡፡

ይሁንና ተከሳሾች የመከላከያ ማስረጃ እንደሌላቸው በመግለጻቸው ምክንያት ፍርድ ለመስጠት በያዘው ተለዋጭ ቀጠሮ መሰረት ጥር 17 ቀን 2014 ዓ.ም በዋለው ችሎት ተከሳሾች በተከሰሱበት ወንጀል ጥፋተኛ ናቸው በማለት ፍርድ ሰጥቷል፡፡

ይህንኑ ተከትሎ ዐቃቤ ሕግ የወንጀል ድርጊቱ የተፈፀመው በቡድን እንዲሁም ሌሊት ላይ ጨለማን ተገን በማድረግ በመሆኑ ይህው እንደ ቅጣት ማክበጃ ተወስዶ ተገቢው ቅጣት ይጣልባቸው ሲል የቅጣት አስተያየቱን አቅርቧል፡፡

በፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት 1ኛ ልዩ ልዩ ወንጀል ችሎት ጉዳዩን መርምሮ ወንጀሉ ሌሊት እንዲሁም በጋራ በመሆን የተፈፀመ መሆኑን እንደ ቅጣት ማክበጃ በመውሰድ፤ በሌላም በኩል ደግሞ ተከሳሾቹ ካሁን ቀደም ምንም የወንጀል ክስ ሪከርድ የሌለባቸው መሆኑን እንደ ቅጣት ማቅለያ በመያዝ ጥር 24 ቀን 2014ዓ.ም በዋለው ችሎት ተከሳሾች እያንዳንዳቸው በ5 አመት ከ6 ወር ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ወስኖባቸዋል፡፡

Attorney general

Exit mobile version