Site icon ETHIO12.COM

በአፍሪካ ቀንድ ከ1.5 ሚሊዮን በላይ የቁም እንስሳት በድርቁ ምክንያት መሞታቸው ተገለፀ

በአፍሪካ ቀንድ በተከሰተው ድርቅ ሳብያ ከ1.5 ሚሊዮን በላይ የቁም እንስሳት መሞታቸውን እና የሰብል ምርትንም በከፍተኛ ደረጃ መቀነሱን የተባበሩት መንግስታት የግብርና ድርጅት ኃላፊ ገለፁ።

በአካባቢው ጉብኝት ያደረጉት በድርጅቱ የአደጋና መቋቋም ዳይሬክተር ሬን ፓዉልሰን፤ በኬኒያ ብቻ በተጠናቀቀው የፈረንጆች ዓመት መጨረሻ 1.4 ሚሊዮን የቁም እንስሳት ሲያልቁ በደቡባዊ ኢትዮጵያም ተጨማሪም 240 ሺህ የቁም እንስሳት ሞተዋል ብለዋል።

በጥቅምት እና ህዳር ወራት መገኘት የነበረበት የዝናብ መጠን እጅግ አነስተኛ መሆኑን ተከትሎ የተከሰተው ድርቁ ከእንስሳት ሞት ባሻገር የሰብል ምርትንም በከፍተኛ መጠን እንደጎዳ ኃላፊው ተናግረዋል።

በዚህም በሶማሊያ እና ኬኒያ ብቻ በተመሳሳይ ወቅት ይገኝ ከነበረው የሰብል ምርት በ58 እና 70 በመቶ እንደሚያሽቆለቁል ይጠበቃል ብለዋል።

በአሁኑ ሰዓት የአካባቢው ማህበረሰብ ምግብ እንዲገዛ፣ ያሉት እንስሳትንም በህይወት እንዲያቆይ እና ድርቅን የሚቋቋሙ ሰብሎችን እንዲዘራ ለማገዝ የ130 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እንደሚያስፈልግም ሬን ፓዉልሰን ገልፀዋል።

ከዚህ ቀደም የተባበሩት መንግስታት የዓለም የምግብ ፕሮግራም በድርቁ ሳብያ በአፍሪካ ቀንድ 13 ሚሊዮን ያህል ሰዎችን ለምግብ እጥረት መዳረጋቸውን እና ከነዚህም ውስጥ 4.5 ሚሊዮን ለሚሆኑት በቀጣዮቹ ስድስት ወራት ድጋፍ ለማድረግ 327 ሚሊዮን ዶላር ያስፈልገኛል ብሎ ነበር።

የዘንድሮው ድርቅ ባለፉት 41 ዓመታት ውስጥ ከተከሰተው ሁሉ ትልቁ መሆኑን የሲጂቲኤን ዘገባ ያመላክታል። EBC

Exit mobile version