ETHIO12.COM

ጠ.ሚ አቢይ ለውጡን እንዲደግፉ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ፈንድ ተቋም ዳይሬክተር መወያየታቸውን አስታወቁ

ከክሪስታሊና ጆርጂየቫ ጋር

በአፍሪካ አውሮፓ የጋራ መድረክ ለመሳተፍ ብራስልስ የገቡት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ፣ ጎን ለጎን ለዓለም አቀፍ ተቋማትና ከገራት መሪዎች፣ እንዲሁም ከአውሮፓ ሕብረት ጋር እንደሚመክሩ አስቀድሞ በተገለጸው ጠቅላይ ዛሬ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ፈንድ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ጋር መወያየታቸውን ለሕዝብ መረጃ በሚሰጡበት አውዳቸው አመልክተዋል።

ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ፈንድ ተቋም ማኔጂንግ ዳይሬክተር ክሪስታሊና ጆርጂየቫ ጋር መወያየታቸውን ያስታወቁት አብይ አሕመድ፣ “ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ፈንድ ተቋም ጋር ያላትን ትብብር ስለ ማጠናከር እና የለውጡን ሂደት በቀጣይነት ስለ መደገፍ ተወያይተናል” ሲሉ አስፍረዋል። ዝርዝር ጉዳይ አላነሱም።

በተመሳሳይ የአብን ሊቀመንበር አቶ በለጠ ሞላ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዑክ ሆነው ወደ ብራስልስ ማምራታቸውን ተከትሎ የአማራ ተቆርቋሪ መሆናቸውን በሚገልጹና በውጭ አገር ሆነው በሚታወቅና በማይታውቅ ስም በማህበራዊ ገጽ፣ እንዲሁም በዩቲዩብ ከፍተኛ ዘለፋ እየተሰነዘረ ነው። ይህንኑ ተከትሎ የምክር ቤት አባል የሆኑትና የአብን ስራ አስፈሳሚ አቶ ክርስቲያን ታደለ የሚከተለውን ብለዋል።


የአብኑ ሊቀመንበር ጓድ በለጠ ሞላ (ፒኤችዲ) በአፍሪካ–አውሮፓ የጋራ መድረክ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን አባል ሆነው እየተሳተፉ ይገኛሉ።

ከ4 ዓመታት ባነሰ ትግል፣ በጀማሪ የፖለቲካ ልምድ እና ከመቼውም ጊዜ በላይ ንውጽውጽታ በሚያንገላታው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ አብን በክልል ምክርቤት፣ በክልል/ከተማ መስተዳደር ምክር ቤት፣ በፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲሁም በሚኒስትሮች ምክር ቤት ውክልናዎች አግኝቷል።

የግርጌ ማስታዎሻ፦ ሕዝባችን በወርዱና በቁመቱ ልክ እንዲወከል ማድረግ አንደኛው ግባችን ነበር። በተሟላ መልኩ ባይሆኑም የሕዝባችን አጀንዳዎች በሁሉም የውክልና እርከኖች መወከላቸው በጎ ጅምር ነው። በያንዳንዱ የውክልና እርከን የምንሰራውን ሪፖርት ማቅረቢያ መድረኩ ፌስቡክ ስላልሆነ አልፎ አልፎ ከዚህም ከዚያም የሚሰነዘሩ ትቺቶችን ባልኮንንም እውነትነት አላቸው ብዬ ግን አልወስድም። ሌላው ማዶ ለማዶ ሆኖ ድንጋይ መወራወር ኢትዮጵያችን እስከዛሬ የመጣችበት ባሕል ነው። ተቀራርቦ መነጋገር፣ የጋራ በሚያደርጉን አገራዊ ጉዳዮች በጋራ መቆም፣ በሚያለያዩን ጉዳዮች በምክንያትና ሃሳብ ጥራት መሞጋገት፣…አዲስ ባሕል ነው። ይህ ባሕል አብን የቆመለትና መታገያ መርኁ ነው። እንደንቅናቄ ትግሉ የሚያስገኛቸውን ሕዝባዊና አገራዊ ግቦችን እንጂ ትግሉን ራሱን ግብ አድርገን አንወስድም። ይኼ የአብን መንገድ ነው። ለሕዝብ ሌላ የተሻለ መንገድ አለኝ የሚል ካለ መብቱ ነው። ትቺቶችን በፀጋ የምንቀበል፤ ምክረሐሳቦችንም በአዎንታ የምንወስድ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ አብን በራሱ መንገድ እንጂ በሌላ መንገድ ሊጓዝ አይችልም።

Exit mobile version