Site icon ETHIO12.COM

ኤርትራዊያን ስደተኞች “አሸባሪው ወራሪሃይል ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ፈጽሞብናል” ሲሉ የዓለም ሕብረተሰብ ተማጸኑ

በሰሜን ጎንደር ዞን ማይጠብሪ አካባቢ በስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ውስጥ የቆዩና በሚደርስባቸው ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ወደ ደባርቅ ከተማ የተፈናቀሉት ስደተኞች አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ሲፈጽምባቸው መቆየቱን ተናግረዋል፡፡ በበረሃ የተገደሉ በርካታ በመሆናቸው ዓለም ዓቀፍ ማህበረሰብ እንዲያውቀው ጩኸት እያሰሙ ነው።
በሰሜን ጎንደር ዞን ማይጠብሪ ከተማ አሥተዳደር በስደተኞች መጠለያ ጣቢያ በርካታ ኤርትራዊያን ተጠልለው ይገኛሉ፡፡ስደተኞቹ ከሚኖሩበት መጠለያ ጣቢያ በአሸባሪ ቡድኑ በየጊዜው እየተፈናቀሉ ሲሆን የሰሜን ጎንደር ዞን አሥተዳደር የሚፈናቀሉትን ስደተኞች እየተቀበለ በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ እንዲቆዩ አድርጓል፡፡
ስደተኞቹ እንደተናገሩት አሁን ላይ አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን በአማራ ሕዝብ እያደረሰ ካለው ግፍ ባለፈ በመጠለያ ጣቢያ በሚኖሩት ኤርትራዊያን ስደተኞች ላይም ከፍተኛ በደል እየፈጸመ ነው ብለዋል፡፡
ከማይጠብሪ አካባቢ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ የተፈናቀለው ወጣት መርሃዊ አብርሃ “እኛ በረሃ አቆራርጠንና በጨለማ ተጉዘን ወገን ካለበት መድረስ ብንችልም ብዙ ወገኖቻችን በትግራይ ወራሪ ቡድን መንገድ ላይ ተገድለውብናል፤ በመድኃኒት፣ በምግብና በውኃ እጦት ብዙዎች ሕይወታቸው እያለፈ ነው፤ የሚመለከተው አካል በመጠለያ ላሉት ወገኖች ይድረስላቸው፤ ይህን ዓለም ማወቅ አለበት፤ አፋጣኝ መፍትሔ ይሰጥ” ብሏል፡፡
ወጣት መርሃዊ ከሞት ተርፈን ወገን ካለበት በመድረሳችን እንደገና የተወለድን ያህል ተሰምቶናል ነው ያለው፡፡

የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት የደባርቅ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ አቶ ንዋይ መንግሥቱ የዳባት ማኅበረሰብ ዓለምዋጭ በተባለ ቀበሌ ለስደተኞች መጠለያ እንዲሠራ 91 ሄክታር መሬት ማስረከቡን ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ውስጥ ሰኔ 26/2013 ዓ.ም በ 8 ሄክታር መሬት ላይ 25 ሺህ ሰዎችን የሚይዝ የመጠለያ ጣቢያ ግንባታ ተጀምሮ ከ 7 ወር በኋላ መጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡ ተፈናቅለው የመጡ እና በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ የነበሩ 1 ሺህ 400 ኤርትራዊያኖች ወደተዘጋጀው ቋሚ የስደተኞች መጠለያ እንዲገቡ ተደርጓልም ብለዋል፡፡
በተባበሩት መንግሥታት የሰደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን (ዩኤን ኤች ሲ አር) የጎንደር ዋና ኀላፊ ማማዱ ላሚን የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ሥራ ከማኅበረሰቡ ትብብር ውጭ የሚታሰብ እንዳልነበር ተናግረው ኅብረተሰቡ ላደረገው ትብብር ምሥጋና አቅርበዋል፡፡
በኢትዮጵያ ቆይታቸው ለስደተኞች መሠረታዊ ፍላጎቶችን በማሟላት፤ ስደተኞቹ ከማኅበረሰቡ ጋር መልካም ግንኙነት እንዲኖራቸው ለማስቻል የአካባቢውን ማኅበረሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሠሩ ገልጸዋል፡፡
የዞኑ ዋና አሥተዳዳሪ አቶ ያለዓለም ፈንታሁን በስደተኞች መጠለያ ጣቢያ የሚኖሩ በርካታ ኤርትራዊያን በየጊዜው እየተፈናቀሉ ወደዞኑ ከተሞች ሲመጡ የፀጥታ ኀይሉና ማኅበረሰቡ በእንክብካቤ እየተቀበለ በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ እንዲቆዩ ማድረጉን አሚኮ ዘግቧል።

Exit mobile version