ETHIO12.COM

በአዲሱ የአብርሆት የህዝብ ቤተመፃሕፍት ደጃፍ የቆመው ኪነ ሀውልት ትርጉም ምንድን ነው?

በቅርፁ ፣ የስነውበት ሁኔታ በተጨማሪ የልጅነትን ደፋር ነፃነት ያጣመረ ኪነ ሀውልት ነው።
ከቅርብም ከሩቅም በሰዎች መተላለፊያ መንገድ ዳር በመሆኑ ለሁሉም አይኖች የተጋለጠ ነው። ወደ መፃሕፍት ቤቱ ዘልቀው ንባብ ከመጀመራቸው በፊት ሁሉም ተመልካቾች ባለፉበት የልጅነት ወራት ተናፋቂና አስገራሚ ድርጊት ዘና የሚሉበትን ዕድል እንዲፈጥር ሆን ተብሎ የተመረጠ ነው ኪነጥበብ ነው።

ከነሀስ ቀልጦ የተሰራው ህፃን በልዩነት ነፃነቱ ከዚህ ዓለም ማናቸውም ተፅዕኖ ነፃ ስለሆነ ነባር የዕውቀትና የመረጃ ክምር ላይ ተኝቶ ባደግንባቸው ፊደልና ቁጥር የተሰራ ሉል/ ዓለም/ ጋር ሞቅ ያለ ጨዋታ ይዟል።
ይጠይቃል ይገረማል ይፈልጋል። እያደር ሲጎለምስ የሚፈራውን ገለባብጦና ተገለባብጦ ራሱንና አካባቢውን የማየት ድፍረት በዚች ዕድሜ ላይ ጀምራ እዛው ላይ የምታበቃ ድንቅ የቅፅበት ዘመን ናት።

ሁሉም ሰው ኋላ ተመሳሳይ ሰልፍ ውስጥ መግባቱ ባይቀርም ከርሞ በሚያጣው በነፃነቱ ዘመን የታደለውን ተሰጥዖ በዚህ ቅርፅ ውስጥ ማስቀረት ዋናው የዚህ ቅርፅ አላማ ነው ።

የቅርፁ ትልቅ ተሸካሚ መሠረት ደግሞ እንደተፈጠረ የተተወ ትልቅ አለት ሲሆን ( subliminal ) ውበትን ከሌላው የኤስቴቲክ ቀመር ጋር እንዲያዋህድና ግርምታን እንዲጨምር የተመረጠ ነው ።

ህፃኑና የፊደል ሉል ደግሞ በቀለም ፣በመጠን በቴክስቸር፣ በእይታ ክብደትና ቅለት ተናበው የተቀናበሩ የቅርፁ ይዘትና ቅርፅ ተጫዋችና አጫዋች ኤለመንቶች ናቸው።
የመረጃው ባለቤት ይህን ኪነ ሐውልት ስራ የሰራው ሰዓሊና ቀራፂ በቀለ መኮንን ነው

Addis Ababa press

Exit mobile version