Site icon ETHIO12.COM

ሊበራሊዝም እንዲሸነፍ ከሆነ ራሽያ ልክ አትሆንም?

በዚህ ገፅ አፍሪካ አህጉር ድሃ ሆና በመቆየት የአውሮፓ እና በዋናነት የአሜሪካ መጠቀሚያ እንድትሆን በተናጥል ሀገራቱ እና በተቋማቶቻቸው (IMF፤ ዓለም ባንክ፤ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፤ NGOs፤ ወዘተ) በኩል የሚያደርጓቸውን ተግባራት እና ውጤት በቀላሉ ለምሳሌ እንዲሆኑ Confession of an economic hitman (ጆን ፓርኪንስ)፤ Dead Aid (ዶምቢሳ ሞዬ)፤ Kicking away the ladder (ሃ ጆንግ ቻንግ)፤ ወዘተ አይተናል።

ምዕራባውያን ሁሉም አቋማቸው በሚያስብል ደረጃ በሌሎች ሀገራት ላይ ዘላቂ (ለዘመናት የሚሆን) አድቫንቴጅ እየወሰዱ መኖር ነው። አውሮፓውያን በመቶዎች አመታት ቅኝ ገዝተው በዘረፏቸው ሀገራት ላይ ዛሬም የውለታ ከፋይነት ስሜት ሳይሆን ዘረፋቸው ለመጪው ትውልድ እንዲተላለፍ ስልት በመንደፍ ይበልጥ ድሃ ማድረጋቸውን ቀጥለዋል።

ለዚህ አይነቱ ስሜት የምዕራቡ ዓለም መሪ አሜሪካ ያላት ፍላጎትም ተንኮልም እርምጃም ከመክፋቱ የተነሳ የአለም ሀገራትን በተዘዋዋሪ መምራት፤ መከፋፈል፤ 21ኛው ክፍለ ዘመን ከገባ እንኳ ያፈረሰቻቸው ሀገራት ስንት ደረሱ?

መቋቋም ያልቻሉት #ለምሳሌ፦ ኢራቅ፤ ሶሪያ፤ የመን፤ ሊቢያ፤ አፍጋኒስታን… የተሰነጠቁት ሶማሊያ (5 ቦታ)፤ ኢትዬጲያ (2 ቦታ ከኤርትራ ጋር)፤ ሱዳን (2 ቦታ ደቡብ ከሰሜን)፤ ስፔን፤ ኮሪያ፤ ቬትናም ከቻይና፤ ታሪኮቻቸው ሲፈተሽ የምዕራቡ ዓለም እና የአውሮፓ ሀገራት እጆች በቀጥታም በተዘዋዋሪም እንደነበረበት ያሳያል።

ጉልበታቸውን የተቀሙት ከእስያ፤ ላቲን አሜሪካ እና አፍሪካ ድረስ ያሉ ሀገራት ፖሊሲ ሲቀረፅላቸው፤ መሪ ሲመረጥ ሲነሳባቸው አልፎ ሲገደልባቸው፤ የማይበርድ የግጭት ምክንያት ሲፈለፈልባቸው፤ አማፂ ሲደራጅባቸው ቆይቶ #የድህነት_አዙሪት ውስጥ እና ጊዚያዊ የመፍረስ አደጋ ያለብን ከጥቂቶቹ በስተቀር የዓለም ሀገራት ውስጥ በአብዛኛው ነው።

ይህን አስከፊ ሁኔታ የተረዱም ሆኑ ያልተረዱ ሀገራት ከጣልቃ ገብነቱ መላቀቅ አይደለም መሞከሩ የሚያስከፍለው ዋጋ ማዕቀብ እና ጦርነት መሆኑን ኩባ፤ ቬንዙዌላ፤ ፖናማ፤ ኢራን፤ ቱርክ፤ ራሽያ፤ ቻይና፤ ኤርትራ፤ አሁን ኢትዮጵያ፤ ወዘተ ምስክር ናቸው።

የዓለም የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ አብዬት በተናጠል ሀገር ሁኔታ ብቻ የሚወሰን ለመሆን በጣም አስቸጋሪ ሆኗል! ላለፉት 70 ዓመታት የመጨረሻዋ የሞከረችውም ያሳካችውም ሀገር ቻይና ሳትሆን አትቀርም።

የራሽያ እና የዩክሬን ጦርነት በሶሻሊዝም እና በሊበራሊዝም ርዕዮተዓለም አስተሳሰብ ጋር ያለው ቅራኔ እየሰፋ መምጣት ውጤት እንደሆነ ይሰማኛል። ታሪክን እንደተማረ ሰው ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማግስት እስከ ቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት መጠናቀቅ (በሀገራችን የደርግ መውደቅ ድረስ ማለት ነው) ድረስ የአሜሪካ ፍላጎት ጦርነት በአውሮፓ ምድር ላይ የፈጠረውን ውድመት እንደ ጥሩ እድል ነበር የተጠቀመችው ሶሻሊስት ስርዓት ከማፍረስ ጀምሮ (ሶቬት ህብረትን መበተንን ጨምሮ) ከማርሻል ፕላኑ የማገገሚ ሰነድ ማግስት NATOን በማቋቋም በዓለም ላይ የሃይልም የኢኮኖሚ ሚዛኑን ወስዳለች።

በአጋጣሚ ሆኖ ሀረር ፕሪፖራቶሪ ስኩል ተማሪ ሳለሁ ኮምፒውተር ክፍል ተጀመረ እና ለመጀመሪያ ጊዜ Dell ኮምፕዩተር ላብ ውስጥ ስነካ እና ለመድ ስል ሰርች ያደረኩት Cold War ብዬ ነበር እና ኢንተርኔት ስለሌለ እዛው ኮምፒውተሩ ውስጥ የ Wikipedia አጭር ቪዲዬ ነበር እና መሪዎች ቀዝቃዛው ጦርነት በተጠናቀቀ ቅስፈት የሚያደርጉት ፌሽታ ነበር የሚያሳየው በሁኔታው ተገርሚያለው ወደ ተመቸ ምዕራፍ የገፋን ይመስል ነበር። አሁን ዩቲዩብ ላይ ብትገቡ ሊገኝ የሚችል አጭር ቪዲዬ ነው።

ሁለቱም አውዳሚ የአለም ጦርነቶች የአሜሪካንን ምድር አልነኩም (ጃፓን የሃርበር ደሴት ላይ ካደረሰችው የቅስፈት ጥቃት ውጪ ማለቴ ነው! ታዲያ ምን ሆነ? ጃፓን በቅርቡ ራሽያ ዩክሬን ጦርነት ላይ በድጋሚ ካልተሞረ በስተቀር የመጀመሪያውንም የመጨረሻውንም የአቶሚክ ቦንክ በ48 ሰዓታት ውስጥ በድጋሚ በመጣል ከተሞች እና ቀጣይ ትውልድን አጠፋች! ተሳትፎዋ እዚህ ጋር አበቃ!)።

የሊበራሉ አስተሳሰብ የሀገራት ኢኮኖሚያዊ ፖሊሲ ከርዕዮተዓለሙ ጉምቱ ፈጠራዎች እነ አሜሪካ ጋር ካልተስማማ የማይቀበል ብቻ ሳይሆን ጫና የሚፈጥር ነው። ለዚህ ነው ያላከበሩትን ሰብዓዊ መብት አክብሩ፤ ያላከበሩት ዲሞክራሲያዊ መብት ጠብቁ፤ ዘግተው ያደጉበትን ገበያ ክፈቱ፤ አርሶ አደር አትደጉሙ፤ ወዘተ እያሉ ትዛል ካልሆነ ማዕቀብ የሚባል በትር የሚልኩት።

የሊበራሉ አስተሳሰብ ዓለምን እንዳይውጣት የሚታገሉት እና መስዋትነት እየከፈሉ ያሉት ሀገራት ቻይና፤ ኢራን፤ ኩባ፤ ራሽያ፤ ቱርክ፤ ሰሜን ኮርያ፤ ዝማባብዊ (በሙጋቤ ወቅት)፤ ቬንዙዬላ፤ ኤርትራ እና ጥቂቶች ናቸው ቋሚ አቋም ያላቸው።

በቅድመ ሁኔታ ላይ ላልተመሰረተው እና የጋራ ተጠቃሚነት የተሻለ አካሄድ ያለውን የቻይና የንግድ አጋርነት እየመረጡ ፊታቸውን ወደ ምስራቋ ሀገር እያዞሩ ያሉት ብዙዎች ናቸው! ኢትዮጵያንም ጨምሮ! ስለዚህ የሊበራሉ ጨፍላቂ አስተሳሰብ የተስተካከለ እንዲሆን ካስፈለገ ከጊዚያዊ ተጠቃሚነት በዘለለ ለመሰዋትነት የቀረበ ቁርጠኝነት ሀገራት መታገል መጀመር ካለባቸው ወቅቱ አሁን ጥሩ ነው።

በሀገራቶች መካከል ቋሚ ወዳጅም ጠላትም ላይኖር ይችላል! ተመሳሳይ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ አማራጭችን መጋራት ግን ይቻላል። ራሽያ የምትዋጋው ሊበራሉ ካፒታሊስት ስርዓት አካሄዱ የልጅ ልጆቿ ስጋት መሆኑን አምና ከሆነ አልያም ዩክሬን በጦርነቱ ያለችው ይህ ርዕዮተዓለም መዳኛዬ ነው (ዘለንስኪ አሜሪካ ቃል ገብታልን አምነናት ከዳችን እንዳለው!) በሚሉት መርሆች መሰረት ያደረገ መሆኑን መረዳት ተገቢ ነው።

#በሎጂክ ደረጃ አግባብ የማይመስሉ በዓለማችን ላይ እየሆኑ ያሉ ብዙ ነገሮች አሉ! ግብፅ ኢትዮጵያ ግድብ ላይ ያላት አቋም፤ ቻይና ቬትናም ላይ ያላት አቋም፤ አሜሪካ ኢትዮጵያ ላይ ያላት ጫና፤ ራሽያ ዩክሬን መውረሯ፤ አሜሪካ ሰሜን ኮሪያን መጥመዷ፤ የሊቢያ እና የኢራቅ መወረር እና መፍረስ፤ አሜሪካ ኢራን እንዳታድግ መፈለጓ፤ ሳውዲ የመንን መቀጥቀጧ፤ ወዘተ በአመክንዬ ልክ አይመስለም ነገር ግን እየሆነ ያለውም በጉልበት ልክ የሆነው የምታዩት ነው። “እንዲህ መደረጉ ትክክል አይደለም!” የሚል ክርክር መድከም ብቻ ነው!

የራሽያ እና ዩክሬን ጦርነት ለዓለም ኢኮኖሚም ፖለቲካም ላይ መከራው ቀላል አይሆንም! ነገር ግን ይህ ግጭት የርዕዮተዓለም ለውጥ እና የሃይል ሚዛንን ለማስተካከል ከሆነ ከብዙ አንግል ለምዕራቡ ክፍል ድጋፍ ባለመስጠት የገለልተኛ አቋም ማሳየት እና የበረቱ ሀገራት ራሽያ ዩክሬንን መውጋቷን ሳይሆን ለሂደቱ አርነት ለመፍጠር ከሆነ ከተገፉት ኢራን፤ ቱርክ፤ ቻይና፤ ራሽያ፤ ወዘተ ጎን መሆን መጥፎ ነው ብዬ አላምንም።

ቻይና በቀጠለው የአሜሪካ ድጋፍ ቬትናምን ኦፍሺያሊ ልትቀማት ብትሞክር ቻይና ቬትናምን አትወርም?

#ለምሳሌ፦ ሱዳን በተባበሩት መንግስታት ራሽያን እንድትቃወም እና አቋሟን እንድንታንፀባርቅ በአውሮፓ እና አሜሪካዊያኑ በውትወታ ተጠምዳለች! የዚህ አይነቱ ጎራ ልየታ መቀጠሉ ስለማይቀር ማሰብ እና ምክንያታዊ ለመሆን መሞከር ተገቢ ነው። በርግጥ ከፍተኛውን የውጪ ምንዛሬ ግኝቱን ከምዕራቡ በእርዳታ እር ብድር ለሚሞላው የአፍሪካ አህጉር ረጂዎቻቸውን እውነታውን እያወቁም መካድ ከብዷቸው “ራሽያ ስርዓት ያዢ!” እያሉም ያሉ አሉ።

__________//__________

ሃሳቡ የውይይት ነው! ጦርነት ፊልም አይደለም በስሜት የሚደገፍም የሚተነተንም አይደለም። ስለዚህ ወደፊትም ወደኋላም የዓለምን ሁኔታ ከታሪክም በመነሳት አገናዝበት ለመወያየት ነው ያቀረብኩላችሁ! ሎጂክ እና በገሃድ ስናስተናግድ የኖርነው እውነታውን ከግምት ከተን እንወያይበት።

The Ethiopian Economist View

Via yitagesu Ambaye

Exit mobile version