Site icon ETHIO12.COM

ማንነታቸው በማይታወቀ ሰዎች ስም ካሳ በሚል መንግስት ከ65 ሚሊዮን ብር በላይ ተዘረፈ

ዐቃቤ ሕግ የልማት ተነሺ ባልሆኑ ሰዎች ስም ስልሳ አምስት ሚሊዮን ዘጠኝ መቶ ሰባ ሰባት ሺ ስድስት መቶ ሀያ ብር ካሳ የተቀበሉ የመንግስት ስራ ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች ላይ ክስ መሰረተ

በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጄኔራል ዐቃቤ ሕግ ከፖሊስ ጋር በመሆን ሲያካሂድ የነበረውን ምርመራ በማጠናቀቅ በከባድ የሙስና ወንጀል ስር ክስ የመሰረተው የልማት ተነሺ ባልሆኑና እስካሁን ትክክለኛ ማንነታቸው ባልታወቁ 21 ግለሰቦች ስም 65,977,620.00 (ስልሳ አምስት ሚሊዮን ዘጠኝ መቶ ሰባ ሰባት ሺ ስድስት መቶ ሀያ) ብር ካሳ ከመንግስት በመውሰድ ለግል ጥቅማቸው ባዋሉ የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 06 ወና ስራ አስፈጻሚ እና የቦሌ ክፍለ ከተማ መሬት ልማትና ከተማ ማደስ ጽ/ቤት ባለሙያዎችን ጨምሮ በ21 ግለሰቦች ላይ ነው፡፡

ዛሬ የካቲት 30 ቀን 2014 ዓ.ም ክሱ ለፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተልኮ እና ተከፍቶ ችሎቱ ተሰይሟል፡፡ በዚህም መሰረት ዐቃቤ ሕግ የመሰረተው ክስ በችሎቱ ለቀረቡት ተከሳሾች እንዲደርሳቸው የተደረገ ሲሆን በችሎት ያልቀረቡም ተከሳሾች ክሱ ደርሷቸው ለሁሉም ተከሳሾች ክሱን ለማንበብ ፍርድ ቤቱ ተለዋጭ ቀጠሮ ለመጋቢት 13 ቀን 2014 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡

ከወንጀል ድርጊቱ ጋር በተያያዘ የተመዘበረውን የህዝብ ሀብት ለማስመለስ ያስችል ዘንድ የተለያዩ ቤቶች፣ ሕንጻዎች፣ በባንክ የሚገኙ ገንዘቦች፣ ተሸከርካሪዎች እና የኮንስትረክሽን ማሽነሪዎችን እንዲታገዱ ተደርጓል፡፡

በዚህ ዜና ላይ የቀረበው ገለጻ የተከሳሾቹን ተሳትፎ በዝርዝር ያልያዘበት ምክንያት ክሱ በችሎቱ ያልተነበበ በመሆኑ መሆኑን እንድትረዱልን በማክበር እየጠየቅን ከላይ በተጠቀሰው ቀጠሮ ላይ የሚደረጉ የክርክር ሂደቶችን ተከታትለን መረጃ የምናደርሳችሁ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

Ministry of justice

Exit mobile version