Site icon ETHIO12.COM

ተመሳጥረው ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ ሊዘርፉ የነበሩ የባንክ ሰራተኞችና አበሮቻቸው ክስ ተመሰረተባቸው

ዐቃቤ ህግ ሐሰተኛ ቼኮችን እና የክፍያ ማረጋገጫ ደብዳቤዎችን በመጠቀም ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተለያዩ ቅርንጫፎች ከ60 ሚለየን ብር በላይ ሊያወጡ በሞከሩ የባንክ ሰራተኞች እና ግብረአበሮቻቸው ላይ ክስ መሰረተ

በጠቅላይ ዐቃቤሕግ ዘርፍ የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጄነራል ዐቃቤ ሕግ ከፖሊስ ጋር በመሆን ሲያካሂድ የነበረውን ምርመራ በማጠናቀቅ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ላይ ከሚሳተፈው እና በቀድሞ የሳሊኒ ኮንስትራክሽን በአሁኑ ዊቢውልድ ኢትዮጵያ ተብሎ ከሚታወቀው ድርጅት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሂሳብ ውስጥ በድርጅቱ ስም ሀሰተኛ ቼኮች እና የክፍያ ማረጋገጫ ደብዳቤዎችን በማዘጋጀት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጅግጅጋ ከተማ በሚገኙ የተለያዩ የባንኩ ቅርንጫፎች ይዘው በመቅረብ በድምሩ ብር 62,986,469.50 ወጪ ለማድረግ በሞከሩ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የጅግጅጋ ዲስትሪክት የዲጅታል ባንኪንግ ስራ አስኪያጅን ጨምሮ በወንጀል ድርጊቱ ተሳትፎ በነበራቸው 6 ተከሳሾች ላይ ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ መስርቷል፡፡

ክሱም የካቲት 25 ቀን 2014 ዓ.ም ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የሙስና ወንጀል ችሎት ቀርቦ 4 ተከሳሾች ያቀረቡት የክስ መቃወሚያ ላይ የዐቃቤ ህግን ምላሽ ለመጠባበቅ እና ሌሎች ቀሪ 2 ተከሳሾች ደግሞ መቃወሚያቸውን ይዘው እንዲቀርቡ በሚል ችሎቱ ለመጋቢት 05 ቀን 2014 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡

ምንጭ የፍትህ ሚኒስቴር

Exit mobile version