ETHIO12.COM

የሿሿ ማጅራት መቺዎችና የመሰረተ ልማት ዘራፊ ተጠርጣሪዎች ተያዙ

በአዲስ አበባ ከተማ በቡድን በመደራጀት የተለያዩ ወንጀሎችን የፈፀሙ 51 ተጠርጣሪዎችን ይዞ ምርመራ እያጣራ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡

ወንጀል ፈፃሚዎቹ የህዝብ መገልገያ በሆኑ ልዩ ልዩ የመሰረተ ልማት አውታሮች ላይ እና ሿሿ የተሰኘውን የሌብነት ወንጀል በመደራጀት ሲፈፅሙ እንደነበር ፖሊስ ገልፆል፡፡

ወንጀል ፈፃሚዎቹ ልዩ ልዩ የመሰረተ ልማት አውታሮችን ኢላማ በማድረግ ወንጀል ሲፈፅሙ እንደነበር የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቆ በተለይ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር የኃይል ማስተላለፊያ ኬብሎችን ፣የኢትዮ ቴሌኮም ለልዩ ልዩ አገልግሎት የዘረጋቸውን ኬብሎች እና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች እንዲሁም ለጋራ መኖሪያ ቤቶች የኤሌትሪክ ኃይል ማስተላፊያ የተዘረጉ የኤሌትሪክ መስመሮች ላይ ትኩረት አድርገው ወንጀሉን ሲፈፅሙ እንደነበር በአዲስ አበባ ፖሊስ የወንጀልና ትራፊክ አደጋ ምርመራ ዘርፍ የልዩ ልዩ እና የተደራጁ ወንጀሎች ምርመራ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ኮማንደር አለማየሁ አያልቄ ገልፀዋል፡፡

ለቀላል ባበሩ ከተዘረጉ ሃዲዶች ላይ ብሎኖችን እየፈቱ ሲወስዱ የነበሩ እና የባቡር ኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ላይ ስርቆት ሲፈፅሙ የተገኙ 10 ወንጀል ፈፃሚዎችና የተሰረቀውን ንብረት የሚገዙ 4 ተጠርጣሪዎች ከተሰረቁት ንብረቶችና ወንጀሉን ለመፈፀም ሲገለገሉባቸው ከነበሩ ልዩ ልዩ ቁሳቁሶች ጋር ተይዘው ምርመራ እየተጣራባቸው ይገኛል፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ በመሰረተ ልማት አውታሮች ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን ለመከላከል ባደረገው ጥረት የኢቲዮ ቴሌኮም ፣ የኢትዮጵያ ኤሌትሪክ አገልግሎት ፣ የወሃና ፍሳሻ አገልግሎት እንዲሁም የቤቶች ልማት ካስገነባቸው 40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ላይ የተሰረቁ የኤሌትሪክ ገመዶችን እና ልዩ ልዩ ንብረቶችን አስመልሷል፡፡ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ 23 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተጠራባቸው እንደሚገኝ የገለፁት ኮማንደር አለማየሁ ፖሊስ ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት በመስጠት እና የምርመራ ቡድን በማደራጀት ባከናወነው ተግባር በተለይ የተሰረቁ የባቡር መሰረተ ልማቶች የሚከማቹበት ቤት በቦሌ ክፍለ ከተማ እንደሚገኝ በመለየት እርምጃ መወሰዱን ተናግረዋል፡፡

እንደ ኃላፊው ገለፃ በመሰረተ ልማት አውታሮች ላይ ወንጀል ሲፈፅሙ ከተያዙት ግለሰቦች በተጨማሪ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ መስለው በከተማችን በተለያዩ ስፍራዎች ተደራጅተው በተለምዶ ሿሿ የተባለውን የሌብነት ወንጀል ሲፈፅሙ የነበሩ 27 ተጠርጣሪዎች እና ወንጀሉን ለመፈፀም ይጠቀሙባቸው የነበሩ 9 ተሽከርካሪዎች የተያዙ ሲሆን በተሽከርካሪ በመታገዝ የቅሚያ ወንጀል ሲፈፅሙ የነበሩ 9 ግለሰቦች እና ወንጀሉን ለመፈፀም ሲጠቀሙባቸው የነበሩ 5 ሞተር ብስክሌቶች እና 3 የተለያዩ ተሽከርካሪዎች ተይዘዋል፡፡ በወንጀለኞቹ ከተቀሙ ንብረቶች መከከል 880ሺ ብር የዋጋ ግምት ያለው አይነቱ ቪትዝ የሆነ ተሽከርካሪን ጨምሮ ልዩ ልዩ የሞባይል ስልኮችና ሌሎች የተለያዩ ኤግዚቢቶችን ማስመለስ እንደተቻለ ኮማንደር አለማየሁ አያልቄ ገልፀዋል፡፡

በመሰረተ ልማት አውታሮች ላይ የሚፈፀሙ ልዩ ልዩ ወንጀሎችን አስቀድሞ ለመከላከል የአዲስ አበባ ፖሊስ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን እና ወንጀሎቹን ለመከላከል የህብረሰቡ ትብብር እንደሚያስፈልግ የጠቀሱት ኃላፊው በተለይ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ተቋማት ቅንጅት ሊጠናከር እንደሚገባ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

(ኢ ፕ ድ)

Exit mobile version