Site icon ETHIO12.COM

በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ መሰረታዊ ነጥቦች

ይህ አጭር ጽሁፍ ስለ ሀገራዊ ምክክር ምንነት፣ ጥቅሞችና ዓላማዎች፣ መርሆች እና ምክክሩን ለማሳካት የሚከናወኑ ተግባራትን በተመለከተ የሚያትት ሲሆን የሀገራዊ ምክክር ጽንሰ ሃሳብን ከአዋጅ ቁጥር 1265/2014 አንፃርም አጭር ትንተና ያቀርባል፡፡
መልካም ንባብ

  1. ስለ አገራዊ ምክክር
    ሀገራዊ ምክክር ስር የሰደዱ ሀገራዊ አለመግባባቶችን፣ ግጭቶችን ለመፍታት ጥቅም ላይ የሚውል አንድ አይነት የግጭት መፍቻ ዘዴ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ድርድር (negotiation) የተለያየ ጥቅምና ፍላጎት የሚወክሉ አካላት በሰጥቶ መቀበል መርህ ልዩነቶቻቸውን የሚፈቱበት ዘዴ ነው፡፡ ሌላው ዘዴ እርቅ (reconciliation) ሲሆን የደረሰ በደል ላይ ጥልቅ ውይይት ማድረግና በመተማመን ይቅር በመባባል ስምምነትን ማስፈኛ ዘዴ ነው፡፡ በመጨረሻም የማስማማት (mediation) የግጭት መፍቻ ዘዴ በሶስተኛ ወገን አማካኝነት ልዩነትን ለማስወገድ ጥቅም ላይ የሚውል ነው፡፡
  2. የሀገራዊ ምክክር ከአዋጅ ቁጥር 1265/2014 አንፃር
    ከግጭት መፍቻ ዘዴዎች መካከል አንዱ የሆነውን አገራዊ ምክክር (national dialogue) ለማድረግ እንዲቻል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ማቋቋያ አዋጅ ቁጥር 1265/2014 አውጥቷል፡፡ የአዋጁን አላማ እና ይዘት እንደሚከተለው ለማብራራት ተሞክሯል፡፡

የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ማቋቋያ አዋጅ ተግባራዊ ያደረገው ዘዴ አካታች አገራዊ ምክክርን ነው፡፡ አገራዊ ምክክር በአገራችን ወቅታዊና ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር ተመራጭ ግጭት መፍቻ ዘዴ ነው፡፡ አገራዊ ምክክር አንድ ወጥ ሀሳብ እና አንድ ወገን ብቻውን የሚመክርበት ሳይሆን በየአጀንዳው የተለያዩ ሀሳቦች፣ ጥቅሞች፣ ፍላጎቶችና መብቶች የሚወከሉበትና ምክክር የሚደረግበት፣ እነዚህን ሀሳቦች የሚወክሉ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚወከሉበት ብዝሀነት ያለው መድረክ ነው፡፡ በዚህም በሀገራችን የሚስተዋሉ መሰረታዊ ችግሮችን እና ልዩነቶችን ወደ ጠረጴዛ በማምጣት፣ የተለያዩ ጥቅሞችና የህብረተሰብ ክፍሎች በሚሳተፉበት ምክክር የጋራ መፍትሄ ለማምጣት የተመረጠና ጥቅም ላይ የሚውል ዘዴ ነው፡፡

2.1. የአገራዊ ምክክር ጥቅሞችና ዓላማዎች
የአገራዊ ምክክር ጥቅም በዋናነት ግጭትን ለማስወገድ (peace building)፣ የፖለቲካና ዴሞክራሲ ሽግግርን ለማሳለጥ የሚጠቅም ነው፡፡ በተለይም ግጭቶችን ለመከላከል፣ ለማስተዳደር (conflict management) እና ለመፍታት አይነተኛ መሳሪያ ሆኖ ያገለግላል፡፡ በአለም አቀፍ ደረጃም በበርካታ ሀገራት በተለየዩ ጊዜያት በተለያየ መነሻ ምክንያቶች ሀገራዊ ምክክሮችን አካሂደዋል፡፡ የተወሰኑት የተሳካለቸው ሲሆን በተወሰኑት የሚፈለገውን ግብ ሳያሳካ ቀርቷል፡፡

የሀገራዊ ምክክር አላማዎች መሰረታዊ የሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ያሉ ልዩነቶችን በማጥበብ መግባባትን ለመፍጠር፣ በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች መካከልና ከመንግስት ጋር ያለን ግንኙነት ለማሻሻል፣ መተማመንን ለማጎልበት፣ የመነጋገር የፖለቲካ ባህልን ለማጎልበት፣ ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት፣ ጠንካራና ቅቡልነት ያለው አገረ መንግስት በጋራ ለመገንባት፣ ልዩነቶችን በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ ለመፍታት፣ የዴሞክራሲና የፖለቲካ ሽግግር (transformation) ለማስቻል፣ ልማትን ለማፋጠን የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

በተጨማሪም የሀገራዊ ምክክር አላማ መሰረታዊ አለመግባባቶች፣ ልዩነቶችና ግጭቶች ምን እንደሆኑ መለየት፣ መሰረታዊ ምክንያታቸውን (root cause) መለየት እና በእነዚህ ላይ ልዩነቶችን በምክንያታዊ፣ በሰለጠነ፣ በመቻቻል መንገድ የጋራ መግባባቶች ላይ ለመድረስ እና የግጭቶቹ መንስኤ የሆኑ ልዩነቶችን ለማጥበብ ካልሆነም በልዩነቶች ላይ በመስማማት በሀሳብ ለመለያየት ብሎም ይህን የሀሳብ ልዩነት በዴሞክራሲያዊ፣ ሰላማዊና ህጋዊ መንገድ መፍታት የሚቻልበትን ዘዴ በጋራ በመቀየስ ተግባራዊ ለማድረግ ለመግባባት የጋራ ጥረት የሚደረግበት መድረክ ነው፡፡

2.2. የአገራዊ ምክክር መርሆች
አገራዊ ምክክር ዓላማን ለማሳካት ምክክሩ ሊከተላቸው የሚገቡ መርሆች ውስጥ አካታችነት፣ ግልፅነት፣ ተአማኒነት፣ መቻቻልና እና መከባበር፣ ምክንያታዊነት፣ የምክረ ሀሳቦች ተግባራዊነት እና አውድ ተኮርነት፣ ገለልተኛ አመቻች፣ የአጀንዳ ጥልቀትና አግባብነት፣ ዴሞክሲያዊነት፣ የህግ የበላይነት በአዋጁ የተጠቀሱ ናቸው፡፡ ከነዚህ በተጨማሪነት ኮሚሽኑ አስፈላጊ የሚላቸውን መርሆች ሊያካትት እንደሚችል ተመልክቷል፡፡ ከዚህ አንፃር ኮሚሽኑ ተሳታፊዎች በቅን ልቦና እንዲሳተፉ እና ፍትሀዊነት መርሆችን ሊያካትት ይችላል፡፡

እነዚህን መርሆች በዝርዝር ስንመለከት በመጀመሪያ የምናገኘው አካታችነትን ይሆናል፡፡ አካታችነት ከህጉ ዝግጅት እና ኮሚሽነሮች ምርጫ ጀምሮ በተቻለ መጠን ሰፊ ተሳትፎን ለማረጋገጥ ጥረት የተደረገበት ነው፡፡ በምክክር ሂደትም መሰረታዊ አገራዊ ጉዳዮችን በሙሉ እንደሚያካትት፣ እነዚህ ሀሳቦችና ጥቅሞችን የሚወክሉ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በየደረጃው እንዲሳተፉበት እንደሚያደርግ ይጠበቃል፡፡ ስራዎቹንም በግልፅነት ለህብረተሰቡ የደረሰበትን ደረጃ በማሳወቅ እንደሚከውን ይጠበቃል፡፡ ኮሚሽኑ ስራዎቹን በተአማኒነት ለአገር፣ ለህዝብ፣ ለህግ፣ ለመርህ እና ለስነምግባር ተገዢ ሆኖ እንደሚፈፅሙ ይጠበቃል፡፡ ተወያዮችም በመቻቻልና በመከባበር መንፈስ በሰከነና በሰለጠነ መንገድ ምክክር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡ ሌላው መርህ ምክንያታዊነት ሲሆን ይህም በማስረጃ እና በእውነት ላይ የተመሰረት የሀሳብ መግለፅ እንደሚኖር እና ሀሳቦችን በምክንያታዊነት የመቀበልና የመቃወም አካሄድ እንደሚኖር ህጉ ይጠብቃል፡፡ ከሂደቱ ውጤት ስምምነት የሚደረስባቸው የትግበራ አቅጣጫዎችን መንግስት እና የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ ይተገብራሉ ተብሎም እምነት ተይዟል፡፡ በተለይም ልዩነቶች የሚፈቱበት ህጋዊ አካሄድ አቅጣጫ በሚቀመጥበት ወቅት ተግባራዊ እንደሚደረግ ይጠበቃል፡፡

2.3. የሀገራዊ ምክክር ለማሳካት የሚከናወኑ ተግባራት
አገራዊ ምክክር ከሚያልፍባቸው ሂደቶች ውስጥ መነሻ (initiation)፣ ዝግጅት፣ ምክክር እና ትግበራ (implementation) ናቸው፡፡ አሁን ባለንበት የዝግጅት ምእራፍ ሲሆን ከዚህ አንፃር አዋጁ ያካተተው ጉዳይ የኮሚሽኑን ተግባርና ሀላፊነት በሚመለከት ኮሚሽኑ በአላማ የተመለከተውን ጉዳይ ለማሳካት በገለልተኛነት እና በነፃነት መስራት እንደሚጠበቅበት ያስቀምጣል፡፡ በዝርዝርም የምክክር አጀንዳዎችን፣ አወያዮች አመራረጥን፣ የምክክር ስነ ስርአትን፣ የተወያዮች አመራረጥን እና ሌሎች መሰል ጉዳዮችን በነፃነትና በገለልተኝነት በራሱ እንደሚወስን ይጠበቃል፡፡ ምክክር የሚደረግባቸው ደረጃዎች፣ ሂደቶች፣ አካባቢዎችን መወሰን እና ምክክሩንም በአመቻችነት መምራት ይጠበቃል፡፡ ለዚህ አላማ ኮሚሽኑ በአጠቃላይ አስራ አንድ ኮሚሽነሮች ያሉት ሲሆን ከነዚህ ውስጥም አንድ ዋና ኮሚሽነር እና ምክትል ዋና ኮሚሽነር አለው፡፡ ኮሚሽኑ ፅሀፈት ቤት፣ አስፈላጊ ኮሚቴዎች እና አስፈላጊ ሰራተኞች እንደሚኖሩት አዋጁ ይገልፃል፡፡ ይህን የማደራጀት ተግባሩም የሚጠበቅ ነው፡፡ ይህን ለመፈፀም የሚያስችለው የፋይናንስ ነፃነቱንም ለማስጠበቅ በጀት ከመንግስት እና ከሌሎች ህጋዊ ምንጮች ማግኘት እንደሚችል ወጪዎቹንም የመንግስት ፋይናንስ መርሆች መሰረት በኮሚሽኑ በሚፀድቅ ውስጠ ደንብ መሰረት የመፈፀም ሙሉ ነፃነት እንዳለው ተመልክቷል፡፡

በአጠቃላይ የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክርን ተግባራዊ ለመድረግ እና አላማዎቹን ስኬታማ ለማድረግ የመንግስት አካላት፣ የተለያዩ ማህበራዊ እና የግል አደረጃጀቶች፣ ህዝቡ፣ ግለሰቦች፣ አለምአቀፍ ተቋማት ትልቅ ሀላፊነትና ድርሻ አላቸው፡፡ ህጉም ኮሚሽኑ ለሚያቀርባቸው ህጋዊ ጥያቄዎች መተባበር ግዴታ እንደሆነ ይደነግጋል፡፡ ከዚህ አንፃር ሂደቱ ካለው ፋይዳ አንፃር ሁሉም የበኩሉን ድጋፍ፣ ትብብር፣ ተሳትፎ እንዲያደርግ ይጠበቃል፡፡

በንቃተ ሕግ፣ ትምህርት እና ስልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ

Source ministry of justice

Exit mobile version