Site icon ETHIO12.COM

…የሌብነት እጆች ሁሉ ይቆረጡ!

ብቁ፣ ገለልተኛና ነጻ የሕዝብ አገልግሎት ሥርዓት መገንባት፤ የሕዝብ አገልጋዮችን እሴት መገንባትና ሥነምግባርን በማሻሻል ውጤታማ የህዝብ አገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓት መዘርጋት፤ በሲቪል ሰርቪስ ዘርፉ መሠረታዊ ለውጥ በማምጣት በአገራዊው የልማት ጉዞ ጉልህ ሚና መጫወት የብልጽግና መንግስታዊ የቀጣይ ዓመታት መሰረታዊ የትኩረት አቅጣጫዎች መካከል ጎልተው የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

በተመሳሳይ “የመንግስት አካላት ተጠያቂነትን ማረጋገጥ የዴሞክራሲ ግንባታችን ቁልፍ ጉዳይ መሆን እንዳለበት ፓርቲያችን ያምናል፤ ፓርቲያችን ማንኛውም ፖለቲካዊ፣ ርዕዮተ-ዓለማዊ፣ ሕጋዊ ወይም ሌሎች እንቅስቃሴዎች ሁሉ ሕገ መንግስትን የተከተሉ እንዲሆኑ ያደርጋል፤” ሲል ብልጽግና ፓርቲ በምርጫ ወቅት በመሃላ አረጋግጦ ለሕዝብ ቃሉን ሰጥቷል፡፡ ሕዝቡም ቃሉን አምኖ በድምጹ ይሁንታን ሰጥቶ የአምስት ዓመት የመንግስትነት ሥልጣኑን ከትልቅ አደራ ጋር እነሆ ብሎታል፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ደግሞ ለቃል ያለው ቦታ ከፍ ያለ፤ ቃልም የእምነት እዳ ከመሆኑም በላይ በምንም በማይደራደርበት በወለደው ልጁ የሚምልበት ታላቅ ኪዳኑ የሆነ ሕዝብ እንደመሆኑ፤ የተገባለት ቃል እንዲፈጸም ይጠብቃል፡፡ ከዚህ የማንነት ስሪቱ ከፍ ያለ የሞራል ልዕልናው በተጓዳኝ ለሕግ ተገዢ መሆንን ስለሚያውቅ ፓርቲው የገባለት ቃል ባይፈጸም በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 12 ተራ ቁጥር 2 ላይ “ማንኛውም ኃላፊና የሕዝብ ተመራጭ ኃላፊነቱን ሲያጓድል ተጠያቂ ይሆናል፡፡ ሕዝብ በመረጠው ተወካይ ላይ እምነት ባጣ ጊዜ ከቦታው ለማንሳት ይችላል፤” ሲል በተቀመጠው መብቱ ሊጠቀም እንደሚችል በመገንዘብ ነው፡፡

እናም ይሄን ቃሉን በተግባር መግለጥ ተስኖት የሚዳክር፤ የመረጠውን ሕዝብ ረስቶ በራስ ማበልጸግ ተግባር ላይ የሚማስን፤ ይሄን ተቸግሬያለሁና ችግሬን አድምጠህ ፍታልኝ ብሎ ደጋግሞ ሲነግረው ጆሮ የሚነሳው ሲኖር ደግሞ፤ በዛ አካል ላይ እምነት ስለሚያጣ እንደእስካሁኑ ሁሉ ከጫንቃው ላይ አሽቀንጥሮ መጣልን ያውቅበታል፡፡ እናም ብልጽግና ይሄን ቃል የመጠበቅም የመፈጸምም ግዴታ እንዳለበት ልብ ይሏል፡፡

ከሰሞኑ ታዲያ በዚህ ቃልኪዳን ላይ የተመረኮዘ የመራጭ ተመራጭ ሕዝባዊ ውይይት እየተካሄደ ይገኛል፡፡ ይሄም መራጩ ሕዝብና ተመራጩ የሕዝብ እንደራሴ ቃላቸውን እያሰቡ የሚነጋገሩበትና የሚመካከሩበት፤ ችግሮቻቸውን አውጥተው የሚያስረዱበት እና ለችግሮቻቸው ተጨባጭ ምላሽ የሚሰጡበት፤ ምላሹን ተከትሎ ሕዝቦች የሚታይ እርምጃን የሚጠብቁበትን ውል የሚያድሱበት የቃል ሰጪና ተቀባይ ቃልኪዳን ማጽኛ መድረክ መሆኑ እሙን ነው፡፡

ይህ ሕዝባዊ መድረክ አሁን ካለንበት ተጨባጭ አገራዊ ሁኔታ አኳያ ትርጉሙ ትልቅ ነው፡፡ ምንም እንኳን ምስጢር ባይሆንም ሕዝቡ ያሉበትን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና የመልካም አስተዳደር ችግሮች፤ በተለይ ደግሞ የኑሮ ውድነት ከሙስናው መንሰራፋት ጋር ተዳምሮ ስለፈጠረበት ሁሉን አቀፍ ቀውስ የሚናገርበት መድረክ እንደሚሆን ይታሰባል፡፡ ከአወያዩም አካል ይሄን የሕዝብ ጥያቄና ብሶት ተገንዝቦ እንደየ ጥያቄውና ቅሬታው አይነት ተገቢውን ምላሽና እርምት ለመውሰድ ዳግም ቃሉን የሚያጸናበት ብቻ ሳይሆን ቃሉን በተግባር የሚገልጥበት እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡

ይሁን እንጂ ከዚህ ቀደም እንደተለመዱት ሁሉ የመድረክ ንግግርና ውጤት የለሽ ጉንጭ አልፋ ምልልሶች ሆነው የቀሩበትን መካን መድረኮች መድገም አይገባም፡፡ ምክንያቱም እነዚያ መድረኮች ሕዝብ የተናገረባቸው፤ ነገር ግን አድማጭ አጥተው የተነሱ ችግሮች ምላሽ ሳያገኙ ዘመን የተሻገሩበት ነበርና፡፡ በተለይ ከአመራሩ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮችና የሕዝብ ጥያቄዎች በደምሳሳው የታለፉ፤ ለውጥ በማያመጣ (እንደውም እድገት በሚመስል) ቦታ ቅየራ የተድበሰበሱ፣ ሕዝቡንም ለተስፋ መቁረጥ የዳረጉ፤ ብልሹ አሰራርና ሌብነትን የበለጠ እንዲስፋፋ የልብ ልብ የሰጡ ስለመሆናቸው የተነገረላቸው ነበሩ፡፡

በመሆኑም በቅዱስ መጽሐፍ “አሁን ግን ወንድሞች ከሚባሉት አንዱ ሴሰኛ ወይም ገንዘብ የሚመኝ ወይም ነጣቂ ቢሆን ከእርሱ ጋር አትተባበሩ፤” እንዲል፤ ይሄኛው መድረክ ለሕዝብ ጥያቄና ብሶት ተገቢውን ምላሽ መስጠት የሚያስችል ዝግጁነት የሚደረግበት፤ የሕዝብ ብሶት ምንጭ የሆኑ አመራሮችም እንደ ሥራቸው ተመዝነው ተጠያቂ የሚሆኑበትን አሰራር መፍጠር እንጂ፤ በቦታ ቅየራ አሽሞንሙኖ የሚታለፍበት ሊሆን አይገባም፡፡ ከእንደዚህ አይነት አመራር ወይም የሕዝብ አገልጋይ ተብሎ ከተሾመ አካል ጋር መተባበር ደግሞ በእጅጉ ነውር ብቻ ሳይሆን ሃጢያትም ነው፡፡

እናም ነገሩ “ለብልህ አይመክሩም፤ ለአንበሳ አይመትሩም” ነውና፤ በእነዚህ ሕዝባዊ መድረኮች ላይ የሚነሱ የሕዝብ ጥያቄዎች ተለቅመው ሊያዙና ተገቢው ምላሽ ሊሰጣቸው፤ ቅሬታዎችም ተገቢ ጆሮ ተሰጥቷቸው የቅሬታዎቹን ምንጭ ከመሰረቱ ለይቶ ዘላቂ የእርምት ርምጃና ማስተካከያ ሊደረግበት ይገባል፡፡ ሕዝብ “እኔን ሊያገለግል በተቀመጠበት ወንበር ላይ ሆኖ እኔኑ ሲበዘብዝና ሲያንገላታ ማየት አልፈልግም፣ ወንበሩን ሊለቅቅ፣ ለሌብነት የተዘረጉ እጆቹም እንዲሰበሰቡ ሊደረጉ ይገባል፤” ብሎ ተቃውሞውን የሚያነሳባቸው አካላት ሲገኙም እንደ ቀድሞው ከቦታ ቦታ በማቀያየር ከሚፈጸም አመራርን የማሽሞንሞን አካሄድ ካስከተለው ቀውስ ተምሮ የችግሩን ባለቤት ማንሳትና ተገቢውን እርምት መስጠት የብልህ መንግስትም፣ ድርጅትም ተግባር መሆኑን ተገንዝቦ መፈጸም ያስፈልጋል!

አዲስ ዘመን መጋቢት 15 ቀን 2014 ዓ.ም

Exit mobile version