Site icon ETHIO12.COM

« የትግራይ ህዝብ የማዳበርያና የምርጥ ዘር ዕዳ ክፈሉ ማለት ጭካኔ ነው»

ህወሓት የትግራይ ህዝብ ችግር ውስጥ እንደሆነ እያወቀ የማዳበርያና የምርጥ ዘር ዕዳ ካልከፈላችሁ እርምጃ እንወስዳለን በማለት በህዝቡ ላይ ያለውን ጭካኔ ያስመሰከረ ነው ሲሉ የትግራይ ብልጽግና ቅርንጫፍ የሴቶች ሊግ ኃላፊ ወይዘሮ አበባ በርሀ ገለፁ::

ወይዘሮ አበባ በርሀ ከወጋሕታ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደገለፁት ፤ የትግራይ ህዝብ በዚህ ሰዓት በችግር ውስጥ እያለ የማዳበሪያና የምርጥ ዘር እዳ ክፈሉ ማለት ተገቢ አይደለም ::ጭካኔ ነው::

ህዝቡ ባለበት ችግር ተደራቢ እዳ መክፈል አለብህ እያሉ እያስጨነቁት ስለሆነ ህዝቡ ለመሰደድ ተገዷል ያሉት ወይዘሮ አበባ ፣ ህወሓት የራሱን ስልጣን ለማራዘም እንጂ ለትግራይ ህዝብ ርህራሄ እንደሌለው እየሰራ ባለው ሥራ ማረጋገጥ ይቻላል ብለዋል::

ፈጣን የሆነ መፍትሄ ካልተሰጠና የትግራይ ህዝብ የገባበት ችግር ካልተፈታለት ወደ ሌሎች ክልሎችና አጎራባች ሃገራት መሰደዱ ግዴታ ነው ያሉት ወይዘሮ አበባ፣ የትግራይ ህዝብ ላለፉት ዓመታት የተጨቆነ እና የታፈነው አልበቃ ብሎት በቡድኑ ምክንያት በዚህ ወቅት ምግብና መድኃኒት በማጣት ለችግር መዳረጉን አብራርተዋል:: ከዚህ የባሰ እንዳይመጣ ፌዴራል መንግሥት ጣልቃ በመግባት ማረጋጋት ካልቻለ ብዙ ህዝብ ህይወቱን ለማዳን መሰደዱ የማይቀር መሆኑን ጠቁመዋል ::

በጦርነት መጀመሪያ ተጠቂ የሚሆኑት ሴቶችና ህፃናት እንደሆኑ ይታወቃል ያሉት ወይዘሮ አበባ፣ በትግራይ በከፋ መልኩ የሴቶች መብት አይከበርም፣ ከህወሓት መንገድ ውጪ በሌላ ፖለቲካ የሚሳተፉ ሴቶች ተቀባይነት የላቸውም ፤ ጫናውን ፈንቅለው የወጡ ሴቶች ብዙ ፈተና እንደሚደርስባቸው ገልፀዋል::

ከትግራይ ውጭ ያለነው ሴቶች ከኢትዮጵያውያት ሴቶች ጋር በመሆን የተጨቆኑ የትግራይ ሴቶች ድምጽ ልንሆን ይገባል፣ የትግራይ ሴቶችም ራሳቸውን በማብቃትና በአመራር ቦታ በመቀመጥ ግፈኞችን መቃወም አለባቸው ሲሉ አሳስበዋል::

ማህበራዊ ረድኤት ትግራይ/ማረት/ በትግራይ ክልል ለአርሶ አደሮች ለማዳበሪያና ምርጥ ዘር ብድር የሚሰጥ ተቋም ነው::

መሰረት ገ/ዮሃንስ

አዲስ ዘመን መጋቢት 15 ቀን 2014 ዓ.ም

Exit mobile version