Site icon ETHIO12.COM

የስንዴ ምች ዓለምን እያሻት ነው – የዩክሬኑ ጦርነት

የቬልትሁንገር ሂልፈ ቃል አቀባይ ዚሞን ፖት እንደሚሉት እነዚህ ሀገራት አሁን የሚገኙበት ሁኔታ አሳሳቢ ነው።ከዚህ ሌላ በርሳቸው አስተያየት በዓለማችን የምግብ እጥረት የለም። «ሁሉንም ዓለም ሊመግብ የሚችል  በቂ ምግብ በዓለማችን እየተመረተ ነው።ይሁንና የሚመረተው ሰዎች በአጣዳፊ ምግብ በሚያስፈልጋቸው ቦታዎች አይደለም።

በዩክሬኑ ጦርነት ምክንያት የስንዴና የነዳጅ ዘይት ዋጋ መናር በበርካታ ሀገራትን ረሀብን እንዳያባብስ አስግቷል።በአካባቢው ጦርነቱ በተጋጋለበት በአሁኑ ወቅት የአውሮጳ ኅብረት፣ የዳቦ ቅርጫት ከሚባሉት ከምርቱ አቅራቢዎቹ ከዩክሬንና ሩስያ የሚጎድለውን መተካት ይችል ይሆን?

ዩክሬንና ሩስያ ከዓለም የስንዴ ምርት የውጭ ንግድ ከ28 በመቶው በላይ የሚሆነውን ይሸፍናሉ። ሩስያ ከሳምንት በፊት የተለያዩ እህሎችን ለውጭ ገበያ ማቅረብ እንደምታቆም ካሳወቀች በኋላ የምርቶቹ ዋጋ እንደገና እያሻቀበ ነው። ይህም በበርካታ ሀገራት የምግብ እጥረትን በማስከተል ረሀብና ተቃውሞን ሊቀሰቅስ ይችላል የሚል ስጋት አሳድሯል። ሞስኮ ስንዴ ፣ገብስና ሌሎች የእህል ዓይነቶችን ወደ ውጭ መላክን እስከ መጪው ሰኔ መጨረሻ ድረስ ልታግድ ትችላለች ተብሎ ይጠበቃል። ይህን የሩስያ ፕሬዝዳንት የቭላድሚር ፑቲን ከፊል የእህል ሽያጭ እገዳም ማርቲን ሆይስሊንግ የተባሉ የጀርመን የአረንዴዎቹ ፓርቲ የግብርና ፖሊሲ ቃል አቀባይ «እህልን እንደ መሳሪያ መጠቀምና በተለይም በደቡቡ የዓለም ክፍል የምግብ ይዞታ አደጋ ላይ እንዲወድቅ ማድረግ ነው» ሲሉ ተችተዋል።የፌደራል ጀርመን  የኤኮኖሚ ጉዳዮችና የውጭ ንግድ ቁጥጥር መስሪያ ቤት እንደሚለው ዩክሬን ለዓለም ገበያ ከሚቀርበው ስንዴ 11.5 በመቶውን የምትሸፍን ሀገር ናት ። የሩስያ ድርሻ ደግሞ 16.8 በመቶ ነው። ከዚህ ሌላ ለዓለም ገበያ ከሚቀርበው በቆሎ 17 በመቶው ከዩክሬን የሚመጣ ነው። ከዚህ በመነሳት የዩክሬኑ ጦርነት በድሀ ሀገራት ላይ ቀጥተኛ ተጽእኖ እያደረገ መሆኑን ቬልትሁንገርሂልፈ የተባለው  የጀርመን ግብረ ሰናይ ድርጅት ገልጿል። የድርጅቱ ቃል አቀባይ ዚሞነ ፖት እንደሚሉት ትንሽ የሚባል ጭማሪም ቢሆን የሚያደርሰው ተጽእኖ በቀላሉ የሚታይ

አይደለም። 
«ተጽእኖው የበረታባቸው የድሀ ደሀ የሚባሉት ሀገራት ህዝቦች ናቸው።ምክንያቱም እነዚህ በቀን ሦስት ዶላር እንኳን የማይሞላ ገቢ ያላቸው ሰዎች ትንሹ የዋጋ ጭማሪ እንኳን ብዙ ተጽእኖ ሊያሳድርባቸው ይችላል።»
የተመድ፣ የዩክሬን ጦርነት በንግድና ልማት ላይ የሚያሳድረውን ተጽእኖ በተመለከተበት በቅርቡ ባወጣው ዘገባ ስንዴ ገብስ እንዲሁም ሱፍን ጨምሮ የሌሎች የዘይት እህሎች የውጭ ንግድ ድርሻ ፣የዩክሬን 25.9  የቱርክ 23 በመቶ የቻይና ደግሞ 13 በመቶ ነው። በዘገባው የእህል የነዳጅ የማዳበሪያ የትራንስፖርት ዋጋ ንረት የጎተራዎች መራቆት እና የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ተዳምረው በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሰዎች የምግብ አቅርቦት አደጋ ላይ እንዲወድቅ አስተዋጽኦ ያደረጉ ጉዳዮች መሆናቸው ተጠቅሷል። እነዚህም ወደ ረሀብና የዋጋ ግሽበት ሊወስዱ እንደሚችሉ ያሰጋል እንደ ዘገባው። የቬልትሁንገር ሂልፈ ቃል አቀባይ ዚሞን ፖት እንደሚሉት እነዚህ ሀገራት አሁን የሚገኙበት ሁኔታ አሳሳቢ ነው።ከዚህ ሌላ በርሳቸው አስተያየት በዓለማችን የምግብ እጥረት የለም።
«ሁሉንም ዓለም ሊመግብ የሚችል  በቂ ምግብ በዓለማችን እየተመረተ ነው።ይሁንና የሚመረተው ሰዎች በአጣዳፊ ምግብ በሚያስፈልጋቸው ቦታዎች አይደለም።»
የአሁኑ የምግብ ቀውስ በሩስያና በዩክሬን ምርቶች ላይ ጥገኛ የሆኑት ሀገራት ምርትን ለማሳደግ አለመጣራቸውና የገጠር ልማትንም ሳያስፋፉ መቅረታቸውን አሳይቷል እንደ ጀርመኑ የእርዳታ ድርጅት በአብዛኛዎቹ ቦታዎች ምንም ዓይነት መጠባበቂያ ምግብ የለም ። የምግብ ቀውሱ ወትሮም የኤኮኖሚ ችግሮች ውስጥ በሚገኙት በነዚህ ሀገራት ላይ ተጨማሪ ተጽእኖ በማድረግ ላይ ባለበት በአሁኑ ወቅት የአውሮጳ ኅብረት የእህል ጎተራዎች ግን እንደሞሉ ነው።የአረንጓዴዎቹ ፓርቲ ፖለቲከኛ ሆይስሊንግ የአውሮጳ ኅብረት አባል ሀገራት  ከዓለም በስንዴ ምርት ቀዳሚውን ስፍራ እንደመያዛቸው ከዩክሬን ምርት ማግኘት ያልቻሉ የደሀ ሀገራት ፍላጎቶችን እንዲያሟላ ጠይቀዋል። ምንም እንኳን ጀርመንን በመሳሰሉ ሀገራት አሁን የዳቦ ዋጋ መጠነኛ ጭማሪ ቢደረግበትም በሌሎች ሀገራት ግን ሰዎች የሚበሉት አጥተው ይሞታሉና ሲሉ ሞግተዋል።
ሁኔታው በተለይ ከዩክሬንና ከሩስያ በሚመጣ እህል ላይ ጥገኛ ለሆኑ የአፍሪቃ ሀገራት ህዝብ አሳሳቢ  እንደሆነ ይገመታል። የተመድ ዘገባ እንደሚለው ከሩስያ እና ከዩክሬን ወደ አፍሪቃ ይገባ የነበረውን እህል በአፍሪቃ ሀገራት መካከል በሚካሄድ ንግድ መተካት አይቻልም።ለዚህም አንዱ ምክንያት በክፍለ ዓለም የስንዴ ምርት በንጽጽር ሲታይ አነስተኛ መሆኑ ነው።ቀልጣፋ የትራንስፖርት መሰረተ ልማት አለመኖርና የማከማቻ ስፍራ ችግርም ሌላ ማነቆ ነው። የነዳጅ ዋጋ ሲጨምር የምርት ዋጋ ከፍ ይላል ይህም የነዚህ ሀገራት ሌላው ተግዳሮት ሆኗል።

ከዲ ድሊው ዘገባ የተወሰደ

Exit mobile version