Site icon ETHIO12.COM

ሥርዐት አልባው ንግድ እና ስጋት የፈጠረው የኑሮ ውድነት!

ዓለም አቀፍ የንግድ ነባራዊ ኹኔታ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል፡፡ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ያዳከመው የዓለም የገበያ ሥርዐት የምሥራቅ አውሮፓን ግጭት ተገን አድርጎ ሲሽመደመድ እያስተዋልን ነው፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ ድሃ ሀገራት ከመቼውም ጊዜ በላይ የሚፈተኑበት ወቅት የተቃረበ ይመስላል፡፡ ወትሮውም ኅልውናቸው በእርዳታ እና ብድር ላይ የተንጠለጠለ ሀገራት መጪው ጊዜ የፈተናዎቻቸው ጅማሮ እንደኾነ ፍንጮች ያሳያሉ፡፡

ወትሮውንም በዋጋ ንረት ስትፈተን የቆየችው ኢትዮጵያ ግጭት፣ ኮሮና፣ የአንበጣ መንጋ፣ የዜጎች መፈናቀል እና ጦርነት ተደራርበው የኑሮ ውድነቱን ከዜጎች አቅም በላይ ከፍ አድርገው ሰቅለውታል፡፡ ሕግና ሥርዐትን ሳይጠበቅ የሚነግድ ነጋዴ በበዛባት ኢትዮጵያ በየደረጃው ያለው የመንግሥት መዋቅር የንግድ ሥርዐቱን ፈትሾ ለማስተካከል መጠነ ሰፊ እርምጃ ባልወሰደበት፤ ሕዝቡም በየቤቱ ከማማረር ያለፈ ሕገ-ወጦችን በማጋለጥ ሥርዐትን በማስፈን መተባበርን አልለመደም፡፡

ይህን ተከትሎም ምክንያት አልባ የዋጋ ጭማሪ የሀገሪቱ የገበያ ሥርዐት ዓርማ መኾን ከጀመረ ውሎ አድሯል፡፡ ብዙ ገፊ ምክንያቶች እና ያደሩ ችግሮች ያበረቱት ወቅታዊው የኑሮ ውድነት እና የዋጋ ጭማሪ የግብይት ሥርዐቱን ሥር ነቀል ለውጥ ከሚፈልግበት የመጨረሻ ደረጃ ላይ አድርሰውታል፡፡ ሕዝቡ ከዚህ በላይ የኑሮ ውድነቱን የሚቋቋምበት እና የዋጋ ጭማሪውን አይቶ እንዳላየ የሚያልፍበት አቅም ያለው አይመስልም፡፡

1 ዓመት ከ8 ወራት በላይ በጦርነት እና ግጭት የዘለቀችው ኢትዮጵያ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችል አሠራር እና ሕጋዊ ንግድን የሚከተል የገበያ ሥርዐት እስካልተገበረች ድረስ ችግሩ አኹን ካለው የከፋ እንደሚኾን መገመት አያዳግትም፡፡ ወቅታዊውን የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ተከትሎ በዓመት ከ18 ቢሊየን ዶላር በላይ የውጭ ግዥ ለምትፈጽመው ድሃ ሀገር የውስጥ አቅምን ከማጠንከር የተሻለ አማራጭ ያላት አይመስልም፡፡

የኑሮ ውድነቱ አስቸጋሪ ደረጃ ላይ ደርሷል ያሉት የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሐሰን መሐመድ የችግሩ ምንጮች አንድ እና በአንድ ጊዜ የተፈጠሩ አይደሉም ነው ያሉት፡፡ ለዓመታት የዘለቀው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ፣ የአንበጣ መንጋ መከሰት፣ ድርቅ፣ የዜጎች መፈናቀል እና ጦርነት አቅርቦት እና ፍላጎት እንዳይጣጣም አድርገውታል ነው ያሉት ሚኒስትር ዲኤታው፡፡ ወቅታዊው የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነትም በዓለም አቀፍ ደረጃ ለችግሩ መባባስ ምክንያት ኾኗል ይላሉ፡፡

ችግሩን ለመቅረፍ የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ እንደኾነም ሚኒስትር ዲኤታው ጠቁመዋል፡፡ አምራቾችን መደገፍ፣ የሀገር ውስጥ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ፣ በውጭ ሀገር የባንክ ሒሳብ ያላቸው ኢትዮጵያዊያን ከቀረጥ ነጻ እንዲያስገቡ ማድረግ፣ አከፋፋዮችን መደገፍ እና ብልሹ አሠራርን ማስተካከል እየተወሰዱ ካሉት የመፍትሔ አማራጮች መካከል ጠቅሰዋል፡፡ ችግሩን መንግሥት ብቻውን የሚወጣው አይደለም ያሉት አቶ ሐሰን ሕዝቡ ያለአግባብ ክምችት የሚፈጥሩ እና ዋጋ የሚሰቅሉ ነጋዴዎችን ማጋለጥ ይጠበቅበታልም ነው ያሉት፡፡

በክልሉም ኾነ እንደ ሀገር ለተፈጠረው የዋጋ ጭማሪ እና የኑሮ ውድነት ምክንያቹ በርካቶች ናቸው ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ኅላፊ አቶ ቀለመወርቅ ምሕረቴ ናቸው፡፡ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በክልሉ ያለው አለመረጋጋት በክልሉ ምርታማነት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል ያሉት ኅላፊው የሽብር ቡድኑ የፈጠረው ጦርነት ችግሩን “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” የሚባለው ዓይነት አድርጎታል ብለዋል፡፡

ትርፍ አምራች የነበሩ አካባቢዎች፣ መንግሥት እና አምራች ድርጅቶች ሳይቀር ሙሉ ትኩረታቸውን የኅልውና ዘመቻውን በመቀልበስ ላይ አድርገው እንደቆዩ አቶ ቀለመወርቅ አንስተዋል፡፡ ውድመቱ፣ ዘረፋው እና የተፈጠረው መፈናቀል የኑሮ ውድነቱን እና ምክንያት አልባ የኾነውን የዋጋ ጭማሬ አባብሰውታል ይላሉ፡፡ ችግሩን ለመቅረፍ መንግሥት የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ መኾኑን የጠቆሙት አቶ ቀለመወርቅ ከዓለም አቀፍ ነባራዊ ኹኔታው አንፃር በአንድ ጊዜ ሊፈቱ የማይችሉ እንደኾኑም ጠቁመዋል፡፡

አቶ ቀለመወርቅ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ግን በሀገሪቱ ዘመናዊ የንግድ ሥርዐት እና ዘመናዊ ነጋዴ መፍጠር ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡ የገበያ ሥርዐቱን ሕጋዊነት ለማጠናከር የሚያስችሉ የተለያዩ እርምጃዎች እየተወሰዱ እንደኾነም ነግረውናል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው – (አሚኮ)

Exit mobile version