Site icon ETHIO12.COM

የሜቴክ የቀድሞ የስራ ሀላፊዎች ላይ የጥፋተኝነት ፍርድ ተላለፈባቸው

በሜቴክ የቀድሞ የስራ ሀላፊዎች ብ/ጀነራል ጠና ቁሩንዲ እና
ሌ/ኮነሬል አሰፋ ዮሐንስን ጨምሮ በሶስት ተከሳሾች ላይ የጥፋተኝነት ፍርድ ተላለፈባቸው።

ተከሳሾች ስልጣንን ያላግባብ በመገልገል፣ የመንግስት ስራን በማያመች አኳኋን መምራት እና የህዝብ እና የመንግስትን ጥቅም የጎዳ ተግባር በመፈጸም የወንጀል ህግ አንቀፅ 32(1)(ሀ)፣ 33 እና 407 (1)(ሀ)፡ (2) ፡(3) ፤ 411 (1) (ሀ)(ሐ) እና (3) ላይ የተመለከተውን በመተላለፍቸው ነው ክስ ተመስረቶባቸው ጥፋተኛ የተባሉት።

ተከሳሾቹ የቀድሞው የብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ዳይሬክተር እና የኮርፖሬት ሲቪል ምርቶች ኦፕሬሽን ኃላፊ የነበሩት ብ/ ጀነራል ጠና ቁሩንዲ߹ የብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የኢትዮጵያ ፓወር ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ ዋና ስራ አስኪያጅ የነበሩት ሌ/ኮረኔል አሰፋ ዮሃንስ እና የብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የኢትዮጵያ ፓወር ኢንጅነሪንግ ኢንዱስትሪ ምክትል ዋና ስራ አስኪያጅ ሻለቃ ክንዲያ ግርማይ አንዲሁም በቻይና ህዝባዊት ሪፑብሊክ ቲምስ ኢንተርናሽናል (ሆ.ኮ) ኩባ. ሊሚትድ ምክትል ዋና ስራ አስኪያጅ የነበሩትና (ያልተያዙት) ሚ/ር ዩዋን ሃን ናቸው ።

ተከሳሾች በኢ.ፌ.ዲ.ሪ የብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ውስጥ በሃላፊነት ደረጃዎች ላይ የመንግስት ሰራተኞች ሆነዉ ሲሰሩ ለጣና በለስ ቁጥር አንድ ስኳር ማምረቻ ፋብሪካ የሚያገለግል ግዥ ሲፈፀም በግልፅ ጨረታ መፈጸም እያለበት የግዥ አፈፃፀም መመሪያ ስር የተቀመጠውን ግዴታ ወደ ጎን በመተው ከጨረታ ውጪ በመመሪያው የተመለከቱት ቅድመ ሁኔታዎች ሳይሟሉ ግዥዉን ያለ ግልፅ ጨረታ በመፈፀምና እንዲሁም ፕሮጀክቱ “ተርን ኪይ” (ስራዉ ተጠናቆ ከሙከራ በኋላ ርክክብ የሚደረግበት) ሆኖ እያለ በውሉ የተመለከተው የስራ አፈፃፀም የባንክ ዋስትና ባልቀረበበት ሁኔታ ክፍያ ፈጽመዋል።

በዚህም ከጠቅላላ የዉሉ ዋጋ 10% በሪቴንሽን (ዋስትና) መልክ መያዝ የነበረበትን አምስት ሚሊዮን አምስት መቶ ስድሳ አራት ሺህ የአሜሪካን ዶላር ገንዘብ ባለመያዝና ስራው ሣይጠናቀቅ ጠቅላላ ክፍያው ሙሉ በሙሉ (100%) እንዲከፈል አድርገዋል ተብሏል።

4ኛ ተከሳሽ ስራውን ሣይጨርስ ፕሮጀክቱ ገና በ 63.14% ደረጃ ላይ እያለ በራሱ ጊዜ አቋርጦ በመውጣቱ ላልተሰራ ሥራ በኢትዮጵያ ብር 422 ሚሊዮን 791 ሺህ 908 ብር ከ 47 አላግባብ በመክፈል ጉዳት አድርሷል።

እንዲሁም መንግስት ስራውን ለማጠናቅቅ ዩናይትድ ኢንተርናሽናል ከተባለ ድርጅት ጋር በገባዉ ውል መሰረት አላግባብ ስድስት ሚሊዮን 400 ሺህ ዶላር ተጨማሪ ወጪ የሚያስወጣው ሆኖ በመገኘቱ ወይም ጉዳት የደረሰበት በመሆኑ በስልጣን አላግባብ መገልገል የሙስና ወንጀል በመፈፀም በጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዘርፍ የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጄነራል ዐቃቤ ህግ ክስ እንደተመሰረተባቸው ይታወሳል፡፡

ካልተያዘው 4ኛ ተከሳሽ ውጭ ያሉት ሌሎች 3 ተከሳሾች በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ ወንጀል ቸሎት ቀርበው የወንጀል ድርጊቱን አለመፈፀማቸውን በሰጡት የእምነት ክህደት ቃልን ተከትሎ ዐቃቤ ህግ ዝርዝር የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎችን አቅርቦ በማስረዳቱና ፍርድ ቤቱ የዐቃቤ ህግ ማስረጃዎችን መርምሮ ተከሳሾች አንዲከላከሉ ብይን ሰጥቶ ነበር ።

ተከሳሾቹ ያቀረቡት የመከላከያ ማስረጃ በዐቃቤ ህግ በኩል የቀረበባቸውን ክስና ማስረጃዎች ያላስተባበለ መሆኑን የተቸው ችሎቱ በዐቃቤ ህግ የቀረበው ማስረጃ ተከሳሾቹ የወንጀል ድርጊቱን ስለመፈጸማቸው በበቂ ሁኔታ ያስረዳ በመሆኑን መርምሮ የጥፋተኝነት ፍርድ ሰጥቷል።

በዚህም መሰረት ቅጣት ለመወሰን ተከሳሾችና ዐቃቤ ህግ የቅጣት አስተያየታቸውን ለሚያዝያ 07/2014 ዓ.ም እንዲያቀርቡ ቀጠሮ በመስጠት የዕለቱ ችሎት ተጠናቋል ሲል ዐቃቤ ህግ አስታውቋል።

ENA

Exit mobile version