በቀድሞው አመራር ዘመን ከሜቴክ 65 ቢሊዮን ብር የት እንደገባ አይታወቅም – አምባሳደር ሱሌማን ደደፎ

በቀድሞ አጠራሩ የኢትዮጵያ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) በአዲሱ አወቃቀር ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ላይ የሒሳብ ምርመራ አገልግሎት ኮርፖሬሽን ባደረገው የሒሳብ ኦዲት ምርመራ፣ 65 ቢሊዮን ብር የት እንደደረሰ እንደማይታወቅ ተገለጸ፡፡

በአገሪቱ ከሚገኙ ትልልቅ ድርጅቶች መካከል አንዱ የነበረው ሜቴክ ከተመሠረተ ከ2002 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ 2012 ዓ.ም. ድረስ የነበረው የሒሳብ ኦዲት ከተሠራ በኋላ ከፍተኛ ኪሳራ መገኘቱን የግሩፑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው የተሾሙት ሱሌማን ደደፎ (አምባሳደር) ለሪፖርተር ጋዜጣ ተናግረዋል።

” የሒሳብ ምርመራ አገልግሎት ኮርፖሬሽን በሠራው ሪፖርት መሠረት 65 ቢሊዮን ብር የት እንደደረሰ ስለማይታወቅ፣ የኦዲት ሪፖርቱን መሠረት በማድረግ መንግሥት እንዲሽረው (Write off) ተጠይቆ ውሳኔ አግኝቷል ” ብለዋል፡፡

በዚህም መሠረት የተገኘው የኪሳራ ገንዘብ በዕዳ እንዳይመዘገብ መንግሥት ሽሮታል (Writeoff) ሲሉ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገልጸዋል፡፡

በኦዲት የተገኘው ገንዘብ ምንም ሥራ ላይ ያልዋለና በወቅቱ የነበሩ አመራሮች ተከፋፍለው የወሰዱት በመሆኑ በዚህ ተቋም አማካይነት የአንድ ህዳሴ ግድብ መሥሪያ ብር መዘረፉን ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ለውጥ ከተደረገ በኋላ ወታደራዊ ምርቶች ለብቻ እንዲሆኑ በመክፈል እንደ አዲስ የተዋቀረው ግሩፑ፣ የደረሰበትን ሀብትና ዕዳውን የመለየትና ጥፋቶችን በመመርመር በሕግ የሚገዛ አገራዊ ተቋም ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የቀድሞው ሜቴክ ከተመሠረተበት ጀምሮ እስካሁን ያለውን አጠቃላይ ሒሳብ ኦዲት መደረግ የተጀመረ መሆኑን፣ እስከ 2012 ዓ.ም. ድረስ ያለውን በማጠናቀቅ ከ2012 ዓ.ም. በኋላ ያለው በሒደት ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በኦዲት ሪፖርቱ ግኝት መሠረት ከኪሳራው በተጨማሪ፣ በሀብት ደረጃ የተመዘገቡት እንዲሸጡ በማድረግ ለግሩፑ ገቢ እንዲሆን እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

በዚህም መሠረት በአሁኑ ወቅት ያለ አገልግሎት የተቀመጡ 5 ቤቶችን ወደ ገንዘብ ለመቀየር በቅርቡ ለሽያጭ እንደሚቀርቡ ገልጸዋል፡፡

” የቀድሞ የድርጅቱ አመራሮች የዝርፊያ ሥልት አሁንም ድረስ በተለያዩ መንገዶች እየቀጠለ በመሆኑ፣ ከኪሳራ እንዳይላቀቅ ማነቆ እየሆነ ነው ” ብለዋል፡፡

በቅርቡ ይፋ የተደረገው የፓወር ኢኪዩፕመንት ፋብሪካ ውስጥ የሚገኙ ስምንት አመራሮች #ከብረት_ስርቆት ጋር በተገናኘ መያዛቸው አንዱ ማሳያ መሆኑን፣ ሌሎች አመራሮችም ቀስ በቀስ ተጠያቂ እንደሚደረጉ አሳውቀዋል።

See also  የፍትህ ጥያቄው እነማንን አቅፎ እነማንን እንዲገፋቸው ነው የሚፈለገው? ፍትህ ለእገሌ ...

መረጃው የሪፖረተር ጋዜጣ ነው።


Leave a Reply