Site icon ETHIO12.COM

የረሀብ ተጋላጭነቷን ለመቀነስ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እየሰራ መሆኑን ግብርና ሚኒስቴር ገለጸ

ኢትዮጵያ የረሀብ ተጋላጭነቷን ለመቀነስ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የሀገራት የረሀብ ተጋላጭነቷ መረጃ ከሰጡ 116 አገራት መካከል 90ኛ ደረጃ ላይ መቀመጧን ዓለም አቀፍ የሀገራት የረሀብ ተጋላጭነት ደረጃ ሪፖርት  አመላክቷል።  

የግብርና ሚኒስቴርና የጤና ሚኒስቴር ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመሆን እኤአ 2021 ዓለም አቀፍ የሀገራት የረሀብ ተጋላጭነት ደረጃ ሪፖርት ይፋ ተደርጓል።በመድረኩ ላይ የተገኙት የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር መለስ መኮንን እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ የረሀብ ተጋላጭነቷን ለመቀነስ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እየሰራች ነው፡፡በተለይ የግብርና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ሥራዎች እየተከናወኑ በመሆኑ የርሀብ ተጋላጭነቷ ደረጃ እየቀነሰ ምጥቷል፡፡

ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ ከ2000 ጀምሮ እስካሁን ድረስ የርሃብ ተጋላጭነቷ  ደረጃ እየቀነሰ መምጣቱን አመልክተው፤የተትረፈረፈ ምርት ሳይኖር የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ስለማይቻል የግብርና ሚኒስቴር ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በትኩረት ይሰራል ብለዋል ፡፡  

ከርሃብ ተጋጭነት እየወጣ ያለው የሕዝብ ቁጥር እያደገ መጥቷል ያሉት ሚኒስትሩ፤ይህ መልካም ውጤት የተገኘውም  የኢትዮጵያን የምግብ ሥርዓት  ለማሻሻል  መንግሥት ፈርጀ ብዙ  ጥረቶች በማድረጉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ 

በጤና ሚኒስቴር የእናቶች፣ የሕጻናትና የአፍላ ወጣቶች ጤና እና የሥርዓተ ምግብ  ዳይሬክተር ዶክተር መሰረት ዘላለም  በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ የርሀብ ተጋላጭነት ደረጃ ከባለፉት ዓመታት አንጻር ብዙ ለውጦችና መሻሻሎች  ቢኖሩም አሁንም ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ረገድ ከፍተኛ ሥራ ይጠይቃል ፡፡ምርትን መጨመር፣ ከአቅርቦት ጋር ተያይዞ ያሉ ችግሮችን ማሻሻል፣ ከ5 ዓመት በታች ያሉ የሕጻናት  ሞትን መቀነስ፣ ከ5 ዓመት በታች ለሆኑ ሕጻናት  የምግብ አቅርቦትን በማሳደግ ረገድና የሀገራችንን የሥርዓተ ምግብ  ማሻሻል ላይ ከፍተኛ ሥራ መስራት ይጠበቅብና ብለዋል፡፡

የምግብና የሥርዓተ ምግብ ጉዳይ ለመንግሥት ብቻ የሚተው ባለመሆኑ  በዋናነት ከምርታማነትና ከአቅርቦት ጋር በተያያዘ ያለውን የግብርና ሚኒስቴር  ትልቁን ድርሻ መውሰድ ይኖርበታል፡፡ የዜጎችን ጤና ለማሻሻል የምግብና የሥርዓተ ምግብ ጉዳይን ማሻሻል አስፈላጊ  መሆኑን ዳይሬክተሯ አብራርተዋል፡፡  

ሞገስ ጸጋዬ 

አዲስ ዘመን መጋቢት 28/2014

Exit mobile version