Site icon ETHIO12.COM

ድርቅና ረሃብ ከፍቷል – ለጋሽ አገራት ድጋፋቸውን በአጥፍ አንዲያሳድጉ ጥሪ ቀረበ

ለጋሽ ሀገራት ለኢትዮጵያ የሚያደርጉትን ሰብዓዊ ድጋፍ በእጥፍ መጨመር አለባቸው- ድርጅቱ

በኢትዮጵያ እርዳታ የሚሹ ሰዎች ቁጥር በመጨመሩ ለጋሽ ሀገራት የሚያደርጉትን የሰብዓዊ ድጋፍ በእጥፍ እንዲያሳድጉ የዓለም የምግብ ፕሮግራም ጥሪ አቀረበ።

የድርጅቱ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ተወካይ ሜተክ ማጅ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ በሰሜን ኢትዮጵያ በነበረው ጦርነት እና በኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች የተከሰተውን ድርቅ ተከትሎ በርካታ ሰዎች የሰብዓዊ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው መሆኑን ገልጸዋል።

በጦርነቱና በድርቁ ተጎጂ የሆኑ ከ11 ሚሊየን በላይ ኢትዮጵያዊያን እና ከ700 ሺህ በላይ የተለያዩ አገራት ስደተኞች አሁን ላይ የለጋሾችን አስቸኳይ ድጋፍ ይፈልጋሉ ብለዋል።

የዓለም የምግብ ፕሮግራም ለእነዚህ ተጎጂዎች የሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረስ ከ600 ሚሊየን ዶላር በላይ ያስፈልገዋል ሲሉም ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች የሰብዊ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን በማንሳት፤ እስከ ፈረንጅቹ ዓመት መጨረሻ ድረስ የሰብአዊ እርዳታ የሚፈልጉ ተጎጂዎች ቁጥር በትንሹ 20 ሚሊዮን እንደሚሆን ይገመታል ብለዋል።

ለተጎጂዎቹ የሚያስፈልገው ሰብዓዊ እርዳታ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በእጥፍ መጨመሩን ጠቅሰው ለጋሽ ሀገራት ለኢትዮጵያ የሚያደርጉትን ሰብዓዊ እርዳታ በእጥፍ እንዲጨምሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የተረጂዎች ቁጥር በማሻቀቡ ምክንያት የዓለም የምግብ ፕሮግራም በሶማሌ ክልል ለእያንዳንዱ ተረጂ ሲሰጥ የነበረውን የ15 ኪሎ ግራም ወርሃዊ የጥራጥሬ ድጋፍ ወደ 12 ኪሎ ግራም መቀነሱን ጠቅሰዋል።

ላለፉት ሦስት ተከታታይ ወራት ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚገኙ ስደተኞች የሚሰጠው የምግብ ድጎማ ከ18 በመቶ ወደ 16 በመቶ መቀነሱንም በማከል።

ድርጅቱ በአማራ፣ አፋርና ትግራይ ክልሎች ለ3 ነጥብ 4 ሚሊየን ሰዎች አስቸኳይ የሰብዓዊ ድጋፎችን እያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።

በተመሳሳይ በሶማሌ ክልል ለሶስት ተከታታይ የዝናብ ወቅቶች ባጋጠመው ድርቅ 3 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዜጎች ተጎጂ መሆናቸውን ጠቁመው፤ ከነዚህ ውስጥ ላለፉት ወራት ለ2 ነጥብ 4 ሚሊየን ተጎጂዎች ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ክልል የሰብዓዊ ድጋፍን ለማጠናከር የወሰደው የግጭት ማቆም ውሳኔንም አድንቀዋል።

የሀገር ውስጥ ግብረሰናይ ድርጅቶች፣ የእርዳታ ሰራተኞችና የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪዎች ውሳኔውን በመልካም እንደተቀበሉትም ጠቅሰዋል።

ከግጭት ማቆም ውሳኔ በኋላ የሰብዓዊ እርዳታ የጫኑ 20 ተሽከርካሪዎችና አንድ ነዳጅ የጫነ ቦቴ ትግራይ ክልል መግባታቸውን ተናግረዋል።

ሌሎች ተጨማሪ 35 ተሽከርካሪዎችም የአፋር ክልል ሰሜናዊ ምዕራብ ጫፍ መድረሳቸውን አረጋግጠዋል።

የዓለም የምግብ ፕሮግራም በጦርነቱ በተጎዱ የአማራና የአፋር ክልል ዞኖች ውስጥ ባደረገው የምግብ ዋስትና ዳሰሳ በአካባቢው ከሚኖሩት 98 በመቶ ያህሉ ለከፋ የምግብ ዋስትና ችግር መዳረጋቸውን አረጋግጠናል ብለዋል።

Exit mobile version