Site icon ETHIO12.COM

በጂንካና አካባቢው በተፈጠረ የፀጥታ ችግር 133 ተጠርጣሪዎች ተያዙ፤ ፖሊሶችና የመንግስት ኃላፊዎች አሉበት

ከሰሞኑ በደቡብ ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን ጂንካ ከተማ እና አካባቢው ተፈጥሮ በነበረው የፀጥታ ችግር ተሳትፈዋል ተብለው የተጠረጠሩ 133 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ።

የደቡብ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አለማየሁ ማሞ ከዋልታ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ በቁጥጥር ስር ከዋሉት ግለሰቦች መካከል 4 የፖሊስ አባላት ይገኙበታል ብለዋል።

በመንግሥት መዋቅር ስር ያሉ የአመራር አካላት፣ ራሳቸውን የሕዝብ ወኪል አድርገው በማኅበራዊ አንቂነት ስም በህገ ወጥ መንገድ የሚንቀሳቀሱ አካላትም በፀጥታ አካላት እና በኅብረተሰብ ተሳትፎ በህግ ጥላ ስር እንደሚገኙ ገልጸዋል።

የክልሉ እና የፌዴራል የፀጥታ አካላት ኅብረተሰቡን በማሳተፍ ባደረጉት የህግ ማስከበር እንቅስቃሴ አሁን ላይ በአካባቢው አንፃራዊ ሰላም ሰፍኗል ብለዋል።

በደቡብ ኦሞ እና ሌሎች የደቡብ ክልል ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች የአስተዳደራዊ መዋቅር ጥያቄዎች ይነሳሉ ያሉት ኮሚሽነሩ ጥያቄዎቹ በሁከት እና ግርግር ሳይሆን ህግና ሥርዓትን ብቻ በተከተለ መልኩ የሚመለሱ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በክልሉ በኮንሶ ዞን፣ በአሌ፣ በደራሼ እና በአማሮ ልዩ ወረዳዎች ተከስተው የነበሩ የፀጥታ ችግሮችን በዘላቂነት ለመቅረፍም እየተሰራ መሆኑን ኮሚሽነሩ አብራርተዋል።

በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ጉጂ ዞን እና አማሮ ልዩ ወረዳ አዋሳኝ አካባቢዎች እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው አሸባሪው ሸኔ በኅብረተሰቡ  እና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ይገኛል ያሉት ኮሚሽነር አለማየው የሽብር ቡድኑን ጥቃት ለመከላከል እና ቡድኑን ለማጥፋት ከሁሉም አጎራባች ክልሎች እና ከፌዴራል መንግሥት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል።

በተያያዘ መረጃ የደቡብ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሚያዝያ 2/2014 ዓ.ም በሰጠው ማብራሪያ “በክልሉ በኮንሶ ዞን፣ አሌ፣ ደራሼ እና አማሮ ልዩ ወረዳዎች የጸጥታ ችግሮች መኖራቸውን ለሕዝብ ይፋ እንዲሆን አድርገናል።” ማለቱ ይታወሳል።

በኮንሶ ዞን እና በአሌ ልዩ ወረዳ የወሰን ጉዳይን አስመልክቶ የተከሰተ የጸጥታ ችግር ነው ያለው ቢሮው ቀደም ሲል የግጭት መንስኤ የሆነውን የወሰን ማካለል ጉዳይ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለመፍታት እየተሰራ ነበር ብሏል።

በደራሼ ልዩ ወረዳም የተከሰተው የጸጥታ ችግር ከመዋቅር ጥያቄ ጋር የተያያዘ መሆኑን ቢሮው መገለፁ የሚታወስ ነው።

የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የክልሉ መንግሥት ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል ነው የተባለው።

በኃይሉ ጌታቸው (ከሀዋሳ)

Exit mobile version