በሀረሪ ክልል የምስራቅ ዞን የሸኔ የሽብር ቡድን አዛዥ ጃል ኦዳ ቀብሶ በቁጥጥር ስር ዋለ

በሀረሪ ክልል የምስራቅ ዞን የሸኔ የሽብር ቡድን አዛዥ ጃል ኦዳ ቀብሶን ጨምሮ በርካታ የሽብር ቡድኑ አባላት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል።

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ጃቢር አሊዪ እንደገለፁት በሰሜን የመጀሪያው ምዕራፍ የህልውና ዘመቻ ከተጠናቀቀ ወዲህም በክልሉ የአሸባሪዎችን ሴሎች የመከታተልና የመቆጣጠር ስራ በተጠናከረ መልኩ እየተከናወነ ይገኛል።

ለዚህም የመረጃና ደህንነት ከክልሉ እና ከፌዴራል የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ውጤታማ ተግባራት እያከናወኑ መሆኑን ጠቁመው በዚህም አሸባሪዎቹ ህወሓትና ሸኔን በተለያዩ አግባቦች ይደግፋሉ ተብለው የተጠረጠሩ አካላት እና አባላት በቁጥጥር ስር እየዋሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በተከናወነው የተቀናጀ ስራም በምስራቁ የሀገሪቱ ክፍል የሸኔ የሽብር ቡድን ጦር መሪ ጃል ኦዳ ቀብሶን ጨምሮ የሽብር ቡድኑ አደራጆችና አባላት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልፀዋል።

በአሁኑ ወቅትም ተጠርጣሪዎች ምርመራቸው እየተጣራ ስለመሆኑ አንስተዋል።

ከዚህ በተጨማሪም በክልሉ ህገወጥ የጦር መሳሪያዎች በቁጥጥር ስር እየዋሉ መሆኑን ጠቅሰው በዚህም ሽጉጦች፣ ክላሾች፣ የተለያዩ ጥይቶች፣ እና የፀጥታ አካላት አልባሳት መያዛቸውን ገልፀዋል።

የተያዙት መሳሪያዎችም ተገቢው ምርመራ ተደርጎባቸው ወደ ኮሚሽኑ ገቢ ተደርገዋል ብለዋል።

በቀጣይም የሽብር ቡድኖቹን በተለያዩ መንገዶች የሚደግፉ አካላትን እና አባላትን በቁጥጥር የማዋል እና ግንኙነታቸውን የመበጣጠስ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው ያብራሩት።

እየተከናወኑ በሚገኙ ተግባራትም ህብረተሰቡ ከፍተኛ ድጋፍ እያደረገ ስለመሆኑ አንስተው በቀጣይም ህዝቡ ከፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር እያከናወናቸው የሚገኙ ተግባራትን እንዲያጠናክር መጠየቃቸውን ከሀረሪ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። EBC

Leave a Reply