ETHIO12.COM

ውሃ ሲወስድ እያሳሳቀ … “አማራ ወደ አራት ኪሎ አምራ” የተከበሩ አቶ ክርስቲያን አዘዙ

ባስበው ባልመው አልገባህ ያለኝ ነገር በአማራ እና በኦሮሞ ህዝብ መካከል ጦርነት እንዲካሄድ የሚፈለግበት ሁኔታ ነው። ጥቂት ጋጠወጦች በሚያደርጉት ያልተገባ አካሄድ የተነሳ በአማራ እና በኦሮሞ ህዝብ መካከል መካረር እንዲኖር የሚካሄደው ቅስቀሳ በጊዜ ገደብ ሊበጅለት ይገባል። የሁለቱ ህዝቦች አለመግባባት ብሎም ወደለየለት ጦርነት መግባት ህዝቡም ህዝብ፣ ሀገሩም ሀገር እንዳይሆን የሚያደርግ ነው። በጊዜ ተው መባል ያለበት አካል ተው መባል አለበት። “ውሃ ሲወስድ እያሳሳቀ ነው” እንዲሉ ቀስ በቀስ በአንድነት የቆምንባቸውን አምዶች መነቅነቅ ትርፉ ተያይዞ ገደል መግባት ነው። ይታሰብበት…!

የአብኑ አመራር አቶ ጋሻው መርሻ Gashaw Mersha

“አስተዋይ” በጠፋበት ዘመን፣ የሃይማኖት ድርጅቶች የፖለቲከኛ መናኸሪያና የፖለቲካ ፓርቲ መጋለለቢያ በሆኑበት ወቅት ላይ “ምራቃቸውን የዋጡ” የሚል ክብር ከሚሰጣቸው እጅግ ጥቂት የሃይማኖት አባቶች መካከል ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር ኢድሪስ ግንባር ቀደሙ ናቸው። ለዚህም ነው ሙስሊሙ ብቻ ሳይሆን መላው ሕዝብ ክብርን የሚሰጣቸው።

የኢትዮጵያ ትልቅ እሴት የሆነውን የሃይማኖት ክብረት በፖለቲካና ፖለቲከኞች በመተብተብ አገሪቱ ሽማግሌ፣ መካሪ፣ ፈሪሃ አምላክ ያለው፣ በሞራል የታነጸ፣ ታላቁን የሚያከብር ትውልድ እንዲመክን በማድርገ አንጻር ሁሉም መንግስታት እጃቸው ቢኖርበትም እንደ ትህነግ ግን ሃይማኖትን ያራከሰና የካድሬ መናኸሪያ ያደረገ የለም። ለዚህም ማስረጃው በግልጽ አሁን ላይ እየታየ ነው።

የታላላቅ እምነት መሪዎች ዛሬ ሰሚ አጥተዋል። ጆሮ የሚሰጣቸው ማጣታቸው ሳይሆን ራሳቸው የመረጡት መንገድ መንፈሳዊነታቸውን በልቶት ንግግራቸውም ሆነ አስተምሯቸው ደርቆባቸዋል። አማትበውና የወላዲት ማሪያምን ስም ጠርተው ቀን በቀን አገር ለማተራመስ መርዝ የሚረጩ፣ “ኢየኡስ ፍቅር ነው” ብለው ጠዋት “ሃሌሉያ” በሚል ሰብከው ረፋዱ ላይ የግድያ ዕቅድና የማተራመስ ዶሴ የሚያከፋፍሉ በበረከቱበት በዚህ ዘመን እንደ ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር ኢድሪስ ያሉ ሚዛናቸውን የጠበቁ የዕምነት መሪ ማግኘት በማስተዋል ለሚከታተሉ ድንቅ ነው። ተዓምርም ነው። ይህ ለምን ሆነ ብለው የሚንጫጩም አሉ። ለምን እሳቸውም በፖለቲካ ቢጫ ወባ አለተነደፉም በሚል የሚያወግዟቸውም አልጠፉም።

“የየትም ፍጪው” ፖለቲካ ኢትዮጵያን ሊበላ ዙሪያውን እየዞራት ባለበት በዚህ ወቅት፣ ” እኔ ከሌለሁ ሰርዶ አይብቀል” እንዲሉ “አገሪቱን ካልበላናት እናጥፋት፣ካልመራናት እናፍርሳት” የሚሉ ጽንፈኛና የጽንፈኞች ተላላኪዎች የእስስት ሴራ በሁሉም ዓይነት አግባብ መልኩን እየቀያየረ እልቂት በሚያመርትበት ጊዜ ቸግሮችን በውይይት ለመፍታት የተጀመረ እንቅስቃሴን ለማጨናገፍ ዘመቻው ተጧጡፏል።

“እስካሁን የጠፋው ጥፋት ይብቃ ከአሁን በኋላ ችግሮቻችንን በምክክርና በውይይት እንፍታ” የሚሉ እንደ ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር ኢድሪስ ያሉ አባቶችን ሳይቀር በመሳደብ ለዳግም እልቂት ከበሮ እየመቱ ያሉ “ኢትዮጵያዊያን” ፍላጎት እጅግ ግራ የሚያጋባ ሆኗል። ምን እንደሚፈለግ፣ ማንን ማንገስ እንደሚመረጥ፣ እንደ እስራኤላዊያን የግብጽ ሽንኩርት ፍቅር ወደ ሁዋላ ለመመለስ ታስቦ ይሆን ግልጽ የሆነላቸው ዜጎች የሉም። የአብን አመራር የሆኑት አቶ ጋሻው መርሻ ግራ እንደገባቸው ገልጸው “ያታሰብበት” ሲሉ ሃሳባቸውን ሰንዘረዋል።

የጨነቃቸው አቶ ጋሻው ” ባስበው ባልመው አልገባህ ያለኝ ነገር በአማራ እና በኦሮሞ ህዝብ መካከል ጦርነት እንዲካሄድ የሚፈለግበት ሁኔታ ነው። ጥቂት ጋጠወጦች በሚያደርጉት ያልተገባ አካሄድ የተነሳ በአማራ እና በኦሮሞ ህዝብ መካከል መካረር እንዲኖር የሚካሄደው ቅስቀሳ በጊዜ ገደብ ሊበጅለት ይገባል። የሁለቱ ህዝቦች አለመግባባት ብሎም ወደለየለት ጦርነት መግባት ህዝቡም ህዝብ፣ ሀገሩም ሀገር እንዳይሆን የሚያደርግ ነው። በጊዜ ተው መባል ያለበት አካል ተው መባል አለበት። “ውሃ ሲወስድ እያሳሳቀ ነው” እንዲሉ ቀስ በቀስ በአንድነት የቆምንባቸውን አምዶች መነቅነቅ ትርፉ ተያይዞ ገደል መግባት ነው። ይታሰብበት…!”

የአብን ከፍተኛ አመራር የሆኑትና “ስትራቴጂስት” የሚባሉት አቶ ክርስቲያን ( የተከበሩ ናቸው) በበኩላቸው ‘ጠላትን በቀኝ እጄ የምታገለው፥ በግራ እጄ የወንድሞቼን በትር እየመከትሁ ነው’ ያለው ማን ነበር? «ግራ እጃችን» ሲያሻው በበትር ብዛት ይሥለል፥ ይልሞስሞስ እንጂ ‘ቀኝ እጃችንን’ ከዒላማችን ላይ አናነሳም። ሰናይ ሌሊት! ” ሲሉ ከባልደረባቸው አቶ ጋሻው የተለየ ጥሪ እያሰሙ ነው። ቅኔም ይመስላል። ማን ጠላት እንደሆነ፣ ማን ወዳጅ እንደሆነ በኮድ የተነገራቸው ብቻ ቢገባቸውም ጥሪው ግን ግልጽ ነው።

ከአንድ ድርጅት የተቀዱት አቶ የሱፍና አቶ ጋሻው እንደ ፖለቲካ መሪና አታጋይ እጅግ የበስለ መረጃና ጥንቃቄ የተሞላበት ሃሳብ ሲያሰራጩ፣ በተከበረ ማዕረግ የተጠቀለሉት የጎጃሙ አቶ ክርስቲያን አንድንዴም አጀንዳ አከፋፋይ፣ አጀንዳ ቀርጪና አቅጣጫ አሳይ በመሆን ሚዲያው ምን ላይ ማተኮር እንዳለበት መረጃ ሲያጋሩ ይታያሉ። አንዳንዶች እንደሚሉት አቶ ክርስቲያን ውጭ ካሉ ሃይሎች ጋር ይናበባሉ። ሰሞኑንን ይህን ብለው ነበር””

“አማራ ሆይ፥ ትግልህን አራት ኪሎ ላይ ብቻ አነጣጥረህ ታገል። ያን ጊዜ ሰላም ታገኛለህ። ያን ጊዜ እጅግ አነሰ ቢባል ሳትጠይቅ ምላሽ ታገኛለህ። ከፍ ሲል ጠያቂ አትሆንም። መልካም ሰኞ!”

ምን ማለት ነው? አማራውን ምን እያሉት ነው? በየክልሉ ተበትኖ በሰላም እየኖረ ላለው አማራ ምን የሚሉት ገጸ በረከት እያዘጋጁለት ነው? “አማራ ሆይ አራት ኪሎ ግባ” ሲሉት ሌሎችን ምን እንዲያድርግ እየጠየቁ ነው? ይህ ንግግር በሌሎች ሚዲያዎችና አክቲቪስት ነን ባዮች መልኩን ቀይሮ ሲሰበክ ነበር። ጉዳዩ እጅግ አደገኛ በመሆኑ በብልጽግና የክልል ፓርቲዎች ዘንድ መነጋገሪያ ሆኗል። አማራውን ለስልጣን ሲባል በሌሎች በጠላትነት እንዲታይ ማድረግ፣ በተለይም አሁን ላይ ትህነግ ሰይፉን እየሳለ ባለበት ወቅት አማራውን አጋር አልባ አድርጎ ከሌሎች ክልሎች ጋር እንዲናከስ መቀስቀስ ምን ያህል ያዋጣል? ይህ እሳቱ ዳር ላለው የጎንደር ሕዝብ ይጠቅማል? ለወልደያና ለዋግ ሕዝብ ዋስትና ይሰጣል? አራት ኪሎ መግባት እንዲሁ በዋዛ የሚሆን ነው? ለዚህም ይመስላል የትግል አጋራቸው አቶ ጋሻው መርሻ ” ይታሰብበት” ያሉት። መንግስት ብቻ ሳይሆን የአብን አመራሮችም የአቶ ክርስቲያንን አካሄድ ሊያርቁ ይገባል።

አማራ ወደ አራት ኪሎ ማምራቱና አራት ኪሎ ለመግባት መታገሉ እጅግ ጤነኛ ነው። በአቶ ክርስቲያን ጥሪ ግን ጣጣው ብዙ ነው። በየትኛውም መስፈርት አምራን ተጠቃሚ አያደርግም። ምን አልባትም አቶ ክርስቲያን ከአቶ በረከት መንፈስ ጋር እርቅ ፈጥረው ካልሆነ በቀር።

እዚህ ላይ መንግስት ቀበቶውን ሊያጠብቅ ግድ ነው። ስብሰባና ህዝብ ባለበት ሁሉ እንደ እሳት እራት እየተነከሩ ዓመጽ የሚያሰራጩትን መላ ሊል፣ ገድብ ሊያሲዝ፣ ራሱ ውስጡንም ቢሆን ከሚታማበት የማጽዳት ስራ ሊያከናውን ይገባል። ሕዝብ በበዙ መልኩ ቅሬታ እያሰማ ነውና መንግስት ሆይ ፍጠን። ሕዝብን ስማና ሕዝብ ጉያ ግባ።

ሕዝብ ይህ አሁን ያለው ቅጥ አንባሩ የማይታወቅና ግራ የሚያጋባ ምስቅልቅል ሲዘራ የኖረው የበቀል ፖለቲካ ውጤት መሆኑን ጠንቅቆ እንደሚያውቅ ያልተረዱ ሃይሎች በጅምላ እባካችሁን እረፉ።ሕዝብ ይህን ባይረዳ ኖሮ እንደ ቀውስ ጠማቂዎቹ ጥረት ድሮ በጠፋን ነበር። አቶ ጋሻው መርሻ ” ውሃ ሲወስድ እያሳሳቀ” እንዲሉ የአቶ ክርስቲያን ሲጽፉትና ሲጠምቁት የሚቀል ጥሪ ገድብ ይበጅለት።

በኤፍሬም ለገሰ

Exit mobile version