Site icon ETHIO12.COM

ከ1.1 ሚሊዮን ተመረቂዎች ከመቶ ሺህ በላዩ የሃሰት መረጃ ባለቤት ናቸው፤ ተመራቂዎችና አስመራቂዎች ላይ እርምጃ ይወሰዳል

ከ1995 ጀምሮ እስከ 2014 ዓ.ም መረጃቸውን ለተቋሙ ካስገቡ የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላይ ክትትል አድርጓል። በእነዚህ ተቋማት እስካሁን ከተመረቁ 1 ነጥብ 1 ሚሊየን ተማሪዎች መካከል ከ100 ሺህ በላይ የሚሆኑት ተማሪዎች ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ የያዙ መሆኑን ነው የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አንዱዓለም አድማሴ የሚናገሩት።

በኢትዮጵያ ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ባሏቸው ግለሰቦችና አስመራቂ የትምህርት ተቋማት ላይ ሕጋዊ እርምጃ ለመውሰድ እየተሰራ መሆኑን የትምህርትና ሥልጠና ባለሥልጣን ገለጸ።

የትምህርትና ሥልጠና ባለሥልጣን የትምህርት ጥራትን ከመቆጣጠር ባሻገር የትምህርት ማስረጃ ትክክለኛነትን የማረጋገጥ ሥራን ያከናውናል።

በዚህም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማቱ የተማሪዎቻቸውን ዝርዝር መረጃና የትምህርት ማስረጃ ከምዝገባ እስከ ምረቃ ድረስ ለባለሥልጣኑ የመላክ ግዴታ አለባቸው።ይህንንም ተከትሎ የትምህርትና ሥልጠና ባለሥልጣን ከ1995 ጀምሮ እስከ 2014 ዓ.ም መረጃቸውን ለተቋሙ ካስገቡ የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላይ ክትትል አድርጓል።

በእነዚህ ተቋማት እስካሁን ከተመረቁ 1 ነጥብ 1 ሚሊየን ተማሪዎች መካከል ከ100 ሺህ በላይ የሚሆኑት ተማሪዎች ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ የያዙ መሆኑን ነው የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አንዱዓለም አድማሴ የሚናገሩት።

ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃውን የያዙት ግለሰቦች የብቃት ማረጋገጫ ሳይኖራቸው፤ በ10+1 እና በ10+2 የዲግሪ የምስክር ወረቀት ከማግኘት እስከ እውቅና በሌለው የትምህርት መስክ እስከተመረቁ ይገኙበታል ነው ያሉት።

እርምጃ መውሰድ ቢጀመር አንዳንድ ክልሎች ቢሮዎቻቸው ሊዘጉ ይችላሉ ያሉት ዶክተር አንዱዓለም፤ በአስመራቂ ተቋማትና የሐሰተኛ ትምህርት ማስረጃው ባለቤቶች ላይ እርምጃ ለመውሰድ ዝርዝር ማጣራት እየተደረገ ነው ብለዋል።

በዚህም የወንጀል ጉዳዮችን በሚመለከት ከፍትህ ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር ላይ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ባለሥልጣኑ ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ የሰጡ ተቋማትን በሕገ-ወጥ መንገድ ዲግሪ ያገኙ ተመራቂዎችን ለማጋለጥ ወደ ኋላ እንደማይልም ነው የተናገሩት።

እንደ አገር መወሰድ በሚገባቸው እርምጃዎች ላይ መንግሥት አቅጣጫ እንዲያስቀምጥ የተለያዩ የውሳኔ ሐሳቦችን በማካተት እንደሚቀርብ ተናግረዋል።

“ለ20 ዓመታት የተንከባለሉ ብልሹ አሰራሮችን ለማስተካከል እየሞከርን ነው” ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በቀጣይም የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማቱ የተመራቂዎቻቸውን ሙሉ መረጃ እንዲልኩ የማድረግ ሥራ ይከናወናል ብለዋል።

በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በርካታ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በ129 ከተሞች ከ2 ሺህ 500 በላይ ቅርንጫፎችን ከፍተው ከ3 ሺህ 315 በላይ የትምህርት መርሃ-ግብሮችን በማስተማር ላይ መሆናቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

Exit mobile version