Site icon ETHIO12.COM

አንድ ኢትዮጵያ! “የትግራይ ሕዝብ በጨለማና በችግር ይኑር” አይሰራም

ራሱን ለግማሽ ክፍለ ዘመን የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ ግንባር በሚል ሲጠራ የኖረው ተገንጣይ ቡድን ኢትዮጵያን በዚሁ በመረጠው የውንብድና ስም እየተጠራ ከሃያ ሰባት ዓመት በላይ የመራት ሃይል በለውጥ ሃይሎች ሲገፋ ትግራይ ሄዶ ሕዝብ ጉያ መሸሸጉ አይዘነጋም። እዛም ሆኖ አርፎ አልተቀመተም። ፓርቲ፣ ተቃዋሚና መንግስት ሲያደራጅ ቆይቶ ሳይሳካ መከላከያን በክህደት አርዷል። አሳርዷል። ማረዱና ማሳረዱን በግልጽ ቋንቋ በራሱ ቲቪ፣ በኩራት፣ በታላቅ ጀብድ ” መብረቃዊ ጥቃት” ሲል ነግሮናል።

ሕዝብ እንደ ሕዝብ ያበደው፣ እሳት ጎርሶና ፍም ሆኖ ከዳር እሰከዳር የተነሳው እንደ ዓይኑ ብሌን የሚሳሳለት መከላከያው በክህደት ስለተነካበት ነበር። ዛሬ ድረስ ሲታወስ የሚያም፣ የሚያንገበግብ፣ የሚቆጭ፣ ታሪክ የማይረሳው የትህነግ የገለማ የክህደት መዝገቡ ነው። ዕድሜውን ሁሉ በበረሃ እየኖረ የአገር ድንበር፣ የትግራይን ኢትዮጵያዊ ሕዝብ ሲያገለግልና ሲጠብቅ በኖረ የኢትዮጵያዊያን ሁሉ ልጆች ላይ የተፈጸመው የክህደት በትር፣ የክፋት ቢላ፣ የጭካኔ ማማ፣ ጉዳቱ በገባበት ቤት ብቻ ሳይሆን በሁሉም ኢትዮጵያዊያን ልቡና የሚቀመጥ ስለመሆኑ ጥርጥር የለም። በርካታ መጽሃፍት፣ ፊልሞች፣ የማስታወሻ ሃውልቶች፣ወዘተ ስለሚቀመጡ ይህን ሃቅ መካድና ማስተባበል የሚቻለው ሃይልም አይኖርም። ዛሬም ባይሆን ውሎ ሲያድር፣ ወደ ቀልብ መመለስ ሲቻል አንገት የሚያስደፋ ታሪክ ባለቤት ለሆኑ ሁሉ በግል አዝናለሁ።

ገና ክጅምሩ ጥላቻንና መከፋፈልን መሰረቱ አድርጎ በኢትዮጵያና በክብሯ ላይ እየተዛበተ ስልጣኑንን ያመቻቸው ተላላኪ ቡድን፣ ከተመሸገበት ሆኖ ከግብጽና ከሌሎች ታሪካዊ ጠላቶችቸን ጋር በገሃድ እያበረ እንደ አገር ሊያፈርሰን፣ እንደ ሕዝብ ሊበትነን፣ እንደ ዜጋ ሊያከስመን፣ እንደ ሰው ሊያዋርደን አቅዶና ተልሞ ሰርቶ ነበር። ተዓምር፣ የምስኪኖች ጸሎትና የአምላክ ፍርድ ረድቶን እንደ አገር እየተለበለብንም ቢሆን አለን። እየደማንም ቢሆን አለን። ዝለን ነበር ግን አገግመን ዛሬ ላይ ደርሰናል።

ይህ የክፋት ሁሉ ኩያሳ የሆነ፣ በክፋት ተረግዞ፣ በክፋት ገንግኖ፣ በክፋት ጎርምሶ፣ በሴራ አርጅቶ አገሪቱን መልኩን እየቀያየረ መከራ ያበላት ትህነግ፣ ምንም እንኳን የሚምለው በትግራይ ሕዝብ ስም ቢሆንም ኢትዮጵያዊያን ሁለቱን አካላት ለያይተን ልናይ።

የትግራይ ሕዝብ በትህነግ አመራር ከተረጂነት ተላቆ አያውቅም። ትህነግ አራት ኪሎ ሲፏልልና በሃብት ሲንበሸበሽ ከሁለት ሚሊዮን በላይ የትግራይ ሕዝብ የስንዴና ዘይት ተጧሪ ነበር። መስራት የሚችል ህዝብ እያለ የአራት ኪሎ ቅምጥል ኑሮ አይኑንን የዘጋው ትህነግ ሕዝቡ ሰርቶ ራሱን እንዲችል አላደረገውም። በቀበሌና በቤተሰብ ተቧድኖ ሃብት ሲያግበሰብስ የኖረው ትህነግ ለትግራይ ሕዝብ እንደ ሕዝብ ያደረገው ነገር እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም። እናም የትግራይ ሕዝብ እንደ ሕዝብ የትህንግ ዘመን ተጠቃሚ አልነበረም። ይልቁኑም ጠላት እየተበጀለት ጎረቤትና ወዳጅ አልባ እንዲሁን የተፈረደበት ነበር። አሁንም ነው። ወደፊት ግን መሆን የለበትም።

ይህ እውነት እያለ ነው እንግዲህ ትህነግ ወደ ጦርነት፣ ጦርነቱም በሚታወቀው መጠን ሰፊ ጉዳትና ክስረት ካደረሰ በሁዋላ ዳግም ወረራ በማካሄድ አማራ ክልልን አመድ ያደረገ እጅግ አሳፋሪ ስራ ተፍጽሟል። ይህንን መካድ አይቻልም። በትግራይም ንጹሃን ላይ በሻዕቢያ አማካይነትና ባለጌ አካላት በደል መፈጸሙ ማስተባበያ አይቀርብበትም።

ለውጡ ይፋ ከሆነ ጊዜ ጀምሮ በሴራ፣ ይህ ጦርነት ከተጀመረ በሁዋላ በመሳሪያ፣ ጦርነቱ ያደረሰውን አድርሶ ከቆመ በሁዋላ በዳግም ወረራና ወረራውን በመቀልበስ ስንት ዜጎች አለቁ? ስንት የሚገመት ነብረት ወደመ? ምን ያህል ዜጎች የቁም ሞት ሞቱ? ስንት ዓመት ወደ ሁዋላ ተመልስን? የሚሉት ጉዳዮች ሲነሱ “ፍትህ ያለበት ዕርቅ” ግድ ነው። አለያ መቆሚያ የሌለው አዙሪት ውስጥ ተነክረን እዛው መከራ ውስጥ እየዳከርን እንከስማለን እንጂ ትርፍ የለውም።

ወገን ወገኑን እየገደለ ” በሰበር ዜና” አየር ማመቅ ድንቁርና ነውና “አንድ ኢትዮጵያ” እያልን፣ የትግራይ ህዝብ ላይ ልንፈርድ አይገባም። ምንም እንኳ ትህነግ የትግራይን ሕዝብ በማስፈራራት ከጎኑ እንዳስለፈ ተደርጎ ቢታሰብም፣ ንጋትና ጥራ እንዲሉ ሁሉም ገሃድ የሚወጣበት ወቅት ስለሚመጣ የትግራይን ሕዝብ እንደ ዜጋና አካላችን ለንወደው ግዴታ አለበን።

“ትግራይ በመከራና በጨለማ ውስጥ ትኑር” የሚለው ፉከራ ለትህነግ መሪዎች እንጂ ለትግራይ ሕዝብ ስለማይሰራ ለሕዝቡ ሲባል ዋጋ መክፈል ይገባናል። ሰላም ከጦርነት በላይ ሰፊ ዋጋ የሚያስከፍል ነውና ሕዝብ ይህንን የሰላም ጅማሮ ያድንቅ። መከላከያችንን ያረዱና ያሳረዱ ለፍርድ መቀርባቸው ድርድር የሚያሻው ጉዳይ ባይሆንም በዛሬ ኢትዮጵያ እርቅና ሰላም ከምን ጊዜውም በላይ አስፈላጊ እንደሆነ መረዳት ብልህነት ይሆናል። ዳር ሆነው ጦርነትን የሚሰብኩና የሚያነሳሱትን “ዘወር በል” ልንል ይገባል።

ትህነግን ገምግሞ መታገልና መፍትሄ መፈለግ የትግራይ ሕዝብ ውሳኔና አቋም ስለሆነ፣ በትህነግ ቆዳ መገነዝ የሚፈልጉ ካሉ ምርጫቸውን ማክበርና ጎን ለጎን ሌላ አማራጭ ማሳየት ይጠበቃል።

የትግራይ ሕዝብም ለግማሽ መዕተ ዓመት ውጊያ እንደማይጠቅምህ አይተሃልና “በቃ” በል። የትግራይ ልሂቃንም “ይብቃ” በሉና በሰጥቶ መቀበል መርህ ትህነግ ያምን ዘንድ ግፉት። “ታላቅ ነህ፣ ጦርነት ፈጣሪ ነህ፣ ልዩ ነህ …” የሚባሉ የምናብ ስብከቶች ውድቀትንና ከሌሎች መነጠልን እንጂ ሌላ ያተረፈ ነገር ስለሌለ ሁሉም በልክ እንዲሆን ዛሬ ነገ ሳትሉ ስሩበት።

“የተለየሁ ነኝ፣ ጦርነትን እሰራዋለሁ…” የሚሉት ዜማዎች ዴሞክራሲያዊ ያልሆኑ፣ ሌሎችን ለሌላ አሳብ የሚያነሳሱ ከመሆናቸው በላይ የዜማዎቹ መነሻ ተራ የበታችነት ስሜት ነውና በኢትዮጵያ ሁሉም አፈር ገፍቶ የሚኖር እኩል ሕዝብ መሆኑንን በመቀበል ለሰላም ስሩ።

የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሰላም ይሰፍን ዘነዳ የበኳላችሁን አበርክቱ። ዓለምን ያዛለውን የነዳጅ፣ የዘይት፣ የዳቦ፣ የስንዴ፣ የብረት፣ የሲሚንቶ ተወደደ ዜና ልክ ኢትዮጵያን እንደ አንድ ደሴት ቆጥራችሁ እኛ ጋር ብቻ እንደሆነ በማስመሰል ጊዜ ከምታባክኑ ሰላም እንዲሰፍን ትጉ። በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ያልደረሰ ግፍና የግፍ አይነት የለምና እንዲያበቃ ስሩ እንጂ ስልጣን ካልያዝኩ በሚል የአቋራጭ መንገድ ስሌት አቁሙ።

ነጋ ጠባ እየተነሳችሁ መርዶና ችግር ከምታቀርቡ የትግራይን ሕዝብ ሂዱና አናግሩ። የትግራይን ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ወገኖች በማቀራረብ አብረው እንዲኖሩ አስችሉ። በውጭ ሆናችሁ እሳተ ጎሞራ የምታፈነዱ ወገኖችም በቃ በሉ። እሳካሁን የሰበሰባችሁትን ብሉ። ካሁን በሁዋላ ሰላምን ስበኩ።

መንግስትም ሁሉን አቀፍ ንግግር አትፍራ። በርህን በጥበብ ከፍተህ ለሰላም ስራ። ሰላም አስፍነህና የአገሪቱን የኖረ ችግር ቀርፈ ስልጣን ብትልቀ ከደም ታሪክ በተቃራኒ ሌላ ታሪክ ይመዘገብልሃል። ዛሬ በቅቶናል። ኢትዮጵያ የምትባል አገር ሰው በድንጋይ ተወግሮ መሞት አይበቃም ተብሎ ሲሰቀል፣ ተሰቅሎ ዳግም ሲወገር፣ ይህ ሁሉ ሲሆን በምስል እንደ ጀብዱ የተቀዳባት አገር ሆናለች። የድሆችን ቤት እያነደዱ ሲገለፍጡ መስማት፣ ነብሰጡርን ማረድና ሰውን እሳት ውስጥ መጣል፣ አባትን ልጅ ፊት መሰየፍ ላይ ተደርሷል። ከዚህ በላይ ውድቀት የለምና በእርቅ ሰላምን አውርደን አረታችን ላይ እንስራ። አዲስ ትውልድ እንገናባ።

ሳሙኤል ተፈሪ – በፌስ ቡክ የተላከ

ዘግጅት ክፍሉ – በጽሁፉ በርካታ ሃይለ ቃላት ቢካተቱም ለማስተካከል ከመሞከር ውጭ የተጨመረ አሳብ የለም።

Exit mobile version