Site icon ETHIO12.COM

አፓርታማዎችን በሳምንት የሚያጠናቅቅ የፈጠራ ውጤት ይዞ በፋይናንስ የሚፈተነው ወጣት

ኢትዮጵያ በኮንስትራክሽን ዘርፍ 60 በመቶ ያህሉን ዋና ዋና የግንባታ ዕቃዎቿን ከውጭ አገራት ነው የምታስገባው። ለዚህም ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወጪ ታደርጋለች። ይህን የውጭ ምንዛሪ ለማደን በአገር ልጆች የሚሠሩ የፈጠራ ውጤቶችን ከመጠቀም ይልቅ ከውጭ የሚመጡ ግብዓቶችን መጠቀም የተለመደ ተግባር ሁኗል። 

በዚህ ምክንያትም የአገር ውስጥ የፈጠራ ባለቤቶችን ደግፎ ለቁም ነገርና ለውጤት ማብቃት አልተለመደም። ወንድማገኝ ገለታ ከእነዚያ የፈጠራ ባለቤቶች መካከል አንዱ ነው። የዜጎችን ሕይወት ይቀይራሉ፤ የኑሯቸውንም ሁኔታ ያሻሽላሉ ያላቸውን የተለያዩ ፈጠራዎችን ወልዶ ስሟል። 

ወጣት ወንድማገኝ የመጀመሪያ ዲግሪውን ከአዳማ ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛ ዲግሪውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በአርክቴክቸራል ኢንጅነሪንግ ተመርቋል። ወጣቱ በአሁኑ ጊዜ በባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ አርቴክቸር ትምህርት ክፍል በመምህርነት እያገለገለ ይገኛል።

ይህ ወጣት በእጁ በርካታ የፈጠራ ሥራዎች ቢኖሩትም በኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት የተወደደና ኢኒስቲትዩቱ የተለያዩ አጋር ተቋማትን ሰብስቦ ይህን ድንቅ ሥራ ተመልከቱልኝ ብሎ መርጦ ካሳያቸው ሥራዎች አንዱ የሆነውን ነው። 

የወጣቱ የፈጠራ ሥራ በሌሎች አገራት እንዲህ ይደረጋል እየተባለ ጭምጭምታቸውን የምንሰማላቸውን ተገጣጣሚ የመኖሪያ ቤቶች በኢንዱስትሪ ውስጥ ተመርተው የትም ሄደው እንዲገጣጠሙ የሚያስችል ነው።

እንደ ወጣቱ ፈጠራ መኖሪያ ቤቶቹ ከኮንክሪትና ከብረት ግብዓትነት ይመረታሉ፤ አስፈላጊው ቦታ ላይ ሄደው በብሎን ይገጣጠማሉ። እያንዳንዱ ቤት ሲገጣጠም ምን ያህል እንደሚሸከም ታሳቢ ተደርጎ የተሠራ ስለሚሆን ጥንካሬው በሳይንሳዊ መንገድ የተረጋገጠ ነው። በተገጣጣሚ ክፍሎቹ እስከ ጂ ፕላስ 7 ድረስ መሥራት እንደሚቻል በተለያዩ አካላት መፈተሹን ወጣት ወንድማገኝ ይናገራል።

የፈጠራ ሥራ አንድ ጊዜ ተፈጥሮ የሚያቆም እንዳልሆነ የተረዳው ወጣቱ፤ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሥራውን እንደከለሰለት ይገልጻል። ወደ ትግበራ የሚገባበትን መንገድም በመነጋገር ላይ እንገኛለን ብሏል። የኮምፒውተር ሲሙሌሽን ሥራውንም አጠናቋል። በፈጠራ ሥራው ባለቤትነት ጉዳይ ላይ ከአዕምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት ለዚሁ ፈጠራ ማረጋገጫ ለማግኘት ወደ ማጠናቀቁ ላይ ይገኛል። 

ይህ ፕሮጀክት ተግባራዊ ቢደረግ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የበርካታ ዜጎችን የመኖሪያ ቤት ጥያቄ ሊመልስ የሚችል ስለመሆኑ ወጣት ወንድማገኝ በልበ ሙሉነት ይገልፃል። ከዋጋ አንፃርም በጣም የተሻለ ነው ይላል። የመኖሪያ ቤቶች ሽያጭ በጊዜ ልክ የሚለዋወጥ ቢሆንም ለዚህ ፕሮጀክት ተብሎ ታኅሳስ 2014 ዓ.ም ላይ በተጠናው መሠረት በካሬ ሜትር 17 ሺህ ብር ቅናሽ አለው። ይህም በሕንፃ ደረጃ ሲሰላ ከፍተኛ የዋጋ ልዩነት ያለው መሆኑን ወጣቱ ያስረዳል። 

እንደ ወጣት ወንድማገኝ ገለፃ፤ ፕሮጀክቱን ወደሥራ ለማስገባት እንደመነሻ ለማሽንና ለኢንዱስትሪው ሼድ ግንባታ 28 ሚሊዮን ብር ያስፈልጋል። 28 ሚሊዮን ብር ፋይናንስ አድርጎ ፈጠራዬን የሚደግፍልኝ ስላጣሁ በቀላሉ ሊፈታ የሚችለው የከተሞች የቤት ችግር አሁንም አንገብጋቢ እንደሆነ ቀጥሏል ይላል ወጣት ወንድማገኝ።

 እንዲያውም ስለተገጣጣሚ ቤቶች ሲታሰብም የአገር ውስጥ የፈጠራ ውጤቶችን መጠቀም ሳይሆን የውጭ ቴክኖሎጂዎችን የማምጣት አዝማሚያ ነው የሚታየው በማለት ትዝብቱን ያክላል። በርካታ የመንግሥት ተቋማትን በር ቢያንኳኳም ፊት የሚሰጠው አለማግኘቱ እንዳሳዘነውም ይናገራል። 

የተገጣጣሚ መኖሪያ ቤት ፋብሪካው ሙሉው ግንባታ ላይ ሲደርስ በሳምንት እስከ 7ኛ ወለል ያላቸውን አራት አፓርታማዎችን መገንባት የሚችልበት ደረጃ ላይ ይደርሳል። የመኖሪያ ቤት አንዷን ክፍል ለመሥራት የሚወስደው ስድስት ሰዓታትን ብቻ ነው። በየ24 ሰዓቱ ሦስት ክፍሎችን መሥራት እንደሚቻል ነው የነገረን። 

ሆኖም እዚህ ፈጠራ ላይ ደፈር ብሎ ኢንቨስት ማድረግ የሚችል አካል በመጥፋቱ በየቀኑ ብዙ የመኖሪያ ቤት ጥያቄዎች እንዲፈጠሩ ከማድረጉም ባሻገር ገቢ ሊሆኑ የሚችሉ ገንዘቦችም በከንቱ እየቀሩ ነው ሲል ስሜቱን በቁጭት ይገልፃል።

ይህ የቤት ግንባታ ፈጠራ ከአገር ውስጥ ምርቶች ወደ 70 በመቶ የሚሆነውን ግንባታ መጠቀሙም ሌላው መልካም ጎኑ መሆኑን ገልጸዋል። አገሪቱ እስካሁን ባለው መረጃ ከውጭ እያስገባቻቸው የምትገኘው ዋና ዋና የግንባታ ግብዓቶች በመቀነስ ረገድ ተስፋ ሰጭ ነው።

ፋይናንሱ ከተገኘ በማግስቱ ለመጀመር ሁሉም ነገር ዝግጁ አድርጌ እየጠበቅሁ ነው የሚለው ወጣት ወንድማገኝ ከመከላከያ ኢንጅነሪንግ ኮሌጅ የመሞከሪያ ቦታ ፈቃድ ማግኘቱንም ይናገራል።

ውብሸት ሰንደቁ 

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 10 /2014

Exit mobile version