Site icon ETHIO12.COM

ባለጸጋ ኤሎን ትዊተርን በ44 ቢሊዮን ዶላር ጠቀለለ

ትናት ምሽት ትዊተር ወደ ግል ይዞታነት መዛወሩ እውን ሆኗል፣ ኩባንያውን በ44 ቢሊዮን ዶላር የጠቀለለው ደግሞ የዓለማችን ቁጥር አንድ ባለጸጋ ኤሎን መስክ ነው!

በቅድመና በድህረ ዝውውሩ “ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ ድንበርን” የተመለከቱ ሙግቶች ከገንዘብ ነክና ከቴክኖሎጂ ጉዳዮች በላቀ ጎላ ብለው ታይተዋል። ትዊተር ወደ መስክ የግል ንብረትነት መዛወሩን ያልደገፉ ግለሰቦች አካውንታቸውን እስከመዝጋት የሚደርስ እርምጃ እንደሚወስዱ ሲገልጹ የተስተዋሉ ሲሆን በአንጻሩ ትዊተር ወደ ግል ይዞታነት መዛወሩን የሚደግፉ ወገኖች ክስተቱ “በጥቂት የቦርድ አባላት ጫና ስር ወድቆ ነበር” የሚሉትን ሀሳብን የመግልጽ ነጻነት እንደሚያፍታታው ያላቸውን ተስፋ አስነብበዋል።

ወደ ግል የመዛወሩ ተቃውሞ መነሻ አዲሱ የትዊተር ባለቤት ኤሎን መስክ ባለፉት ዓመታት ሀሳብ በነጻነት መግለጽን በተመለከተ ያስነበባቸው የትዊተር መልዕክቶች ነበሩ። የመስክ መልዕክቶች ማጠንጠኛ “ሀሳብን በነጻነት መግለጽ ከኛ የተጻረር እይታ ያላቸውን ግለሰቦች እይታ ማክበርና መታገስን ይጨምራል” የሚል ነው።

መስክ የማህበራዊ ሚዲያ ኩባንያዎች ሀሳብን በነጻነት ከመግለጽ አንጻር ቁመዋል፣ እንዲሁም ፕላትፎርማቸውን የሚያስተናብሩበት መርህና አሰራር ጨቋኝ ነው የሚሉ ሙግቶችን በተደጋጋሚ በማስነበብም ይታወቃል። የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ከትዊተርና ከፌስቡክ በታገዱበት ወቅት ትችት ያቀረበበት መንገድ ለዚህ በምሳሌነት ይጠቀሳል።

የመስክን ሀሳብን በነጻነት የመግልጽ እይታ የሚተቹ ግለሰቦች ቢሊየነሩ “ሀሳብን በነጻነት በመግለጽ ካባ ስር ለሀሠተኛና የተዛቡ መረጃዎች እንዲሁም ለጥላቻ ንግግር አሰራጮች ፕላትፎርሙን ያጋልጠዋል” የሚል ስጋት እንዳላቸው ይገጻሉ። ተቺዎቹ ትዊተር ቀደም ባሉት ዓመታት በተከተለው የላላ ቁጥጥር ምክንያት ዓለማችን በርካታ ፈተናዎችን ማስተናገዷን የሚገልጹ ሲሆን “የነጻ ሀሳብ አክራሪነት” ተፈትሾ መውደቁን ያብራራሉ። ዝውውሩን ተከትሎም በትዊተር የታገዱ እና የላላ ቁጥጥር ይደረግባቸዋል ወደሚባሉት የማህበራዊ ሚዲያዎች ያፈገፈጉ ግለሰቦች ይመለሱ ይሆን የሚል ስጋት እንዳላቸውም ሲገልጹ ተስተውሏል።

ሆኖም መስክ በትዊተር አካውንቱ በተለያየ ጊዜያት ካሰነበባቸው ቁርጥራጭ ሀሳቦች ባለፈ በፕላትፎርሙ ላይ ምን አይነት ለውጥ ማድረግ እንደሚፈልግ የተብራራ መግለጫ እስካሁን አልሰጠም። ትዊተር የአብርሆት አደባባይ የመሆን ትልቅ አቅም እንዳለው የሚገልጸው መስክ ሀሳብን በነጻነት ከመግለጽ ባሻገር መሻሻል አለባቸው ብሎ ካስነበባቸው ጉዳዮች መካከል የትዊተር አልጎሪዝም ግልጽነኝነት የተመለከተ እንዲሁም ቦቶች በፕላትፎርሙ ቦታ እንዳይኖራቸው መስራት ይገኝበታል።

ከትዊተር መስራቾች መካከል አንዱ የሆነው ጃክ ዶርስየ ከዝውውሩ በኃላ ባስነበበው የትዊተር መልዕክት ፕላትፎርሙ ከገባበት ማነቆ እንዲወጣ መስክ ሁነኛ መፍትሄ እንደሚሆን ያለውን ተስፋ ገልጿል።

ትዊተር በመስክ የግል ይዞታነት ስር ሆኖ ሀሳብን በነጻነት በመግለጽና በሀሠተኛና የተዛባ መረጃ እንዲሁም በጥላቻ ንግግር መካከል ያለውን ቀጭን ገመድ ይሻገረው ይሆን የሚለውን አብረን የምናየው ይሆናል። via – EthiopiaCheck Explainer

Exit mobile version