Site icon ETHIO12.COM

አቢሲኒያ ባንክ 60 ወለል ሰማይ ጠቀስ ሕንፃ ሊያስገነባ ነው

– ከምስራቅ አፍሪካ ቀዳሚ ይሆናል

አቢሲኒያ ባንክ 60 ወለል ሰማይ ጠቀስ ሕንፃ ሊያስገነባ ነው

አቢሲንያ ባንክ በመዲናችን አዲስ አበባ ለሚያስገነባው የባንኩ ዋና መ/ቤት ሕንፃ ግንባታ ጨረታውን ካሸነፈው ቻይና ስቴት ኮንስትራክሽን ኢንጂነሪንግ ኩባንያ ጋር የግንባታ ውል ስምምነት ፊርማ ዛሬ ግንቦት 04 ቀን 2014 ዓ.ም በሃያት ሪጀንሲ ሆቴል በደማቅ ስነ-ስርዓት አከናዉኗል፡፡

የአቢሲኒያ ባንክ የወደ ፊት ዋና መ/ቤት ሕንፃ መገንቢያ ቦታ በአዲስ አበባ ከተማ ልደታ ክ/ከተማ ሜክሲኮ አደባባይ ዋቢ ሸበሌ ሆቴል ጎን የሚገኝ ሲሆን አጠቃላይ ስፋቱ 9,763 ካሬ ሜትር ነው፡፡ በዚህ ይዞታ ላይ እስከ 60 ወለል የሚደርስ ሕንፃ ለመገንባት ዓለም ዓቀፍ ተቋራጮች በጨረታ ተወዳድረው አሸናፊው ቻይና ስቴት ኮንስትራክሽን ኢንጂነሪንግ ኩባንያ ጋር ስምምነት ላይ መድረስ ተችሏል።

26 ስኬታማ ዓመታትን ያሳለፈው አቢሲኒያ ባንክ አዲስ የሚያስገነባው ሕንፃ 270 ሜትር የሚረዝምና ከምስራቅ አፍሪካ ቀዳሚው ሰማይ ጠቀስ ሕንፃ የሚሆን ሲሆን፣ የሚገነባው ሕንፃ የጠቅላላ ወለሎቹ ስፋት 174 ሺህ ስኩዌር ሜትር ይሆናል።

በአጠቃላይ የሰማይ ጠቀሱ ሕንፃ የወለል ብዛት 56+4 ፎቅ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 4 ቱ ከምድር በታች የሚሰራ ነው።

ቻይና ስቴት ኮንስትራክሽን ኢንጂነሪንግ ኩባንያ በመላው አለም ወደ 6 ሺህ የሚጠጉ ፕሮጀክቶችን ሰርቶ ያጠናቀቀ ግዙፍ ኩባንያ ሲሆን፣ በአዲስ አበባም የአፍሪካ ህብረት ዋና ጽ/ቤት፣ የኖክን እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ዋና መ/ቤትን ገንብቶ ለማጠናቀቅ የቻለ ነው።

የአቢሲንያ ባንክ አ.ማ 2.05 ቢሊዮን ብር ያልተጣራ ትርፍ ማግኘቱን ይታወቃል። ይህም ባለፈው ዓመት ከተመዘገበው ትርፍ ጋር ሲነጻጸር የ90 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡

በ2013 በጀት አመት 97 አዳዲስ ቅርንጫፎችን በመክፈት የቅርንጫፎቹን ቁጥር ወደ 700 ከፍ ለማድረግ መቻሉ ተገልጿል፡፡

ባለፈው አመት ሰኔ ወር 2013 ዓ.ም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት አጠቃላይ የሀብት ክምችቱን ከነበረበት 56.89 ቢሊዮን ብር በ82.5 በመቶ በማሳደግ ወደ 103.85 ቢሊዮን ብር አድርሷል።

ባንኩ የተከፈለ ካፒታል መጠኑን ከ5.68 ቢሊዮን ብር በ52 በመቶ በማሳደግ ወደ ብር 8.65 ቢሊዮንብር ከፍ ማድረግ መቻሉን አስታውቋል። እንዲሁም አጠቃላይ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑን በ 86.6 በመቶ በማሳደግ 88.88 ቢሊዮን ብር ማድረሱ ተነግሯል፡፡

የባንኩ የብድርና ቅድመ ክፍያዎች መጠን 76.6 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ይህም ካለፈው በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ105.9 በመቶ ወይም የብር 39.4 ቢሊዮን የእጥፍ ጭማሪን አሳይቷል፡፡አቢሲኒያ ባንክ በበጀት አመቱ ያገኘው የውጭ ምንዛሪ መጠን 753.16 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን፣ ይኸ አኀዝ ባንኩ ባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት አስመዝግቦት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር የ352.85 ሚሊዮን ዶላር ወይም የ88 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡

Via hausing in Addis Ababa

Exit mobile version