«ውሳኔው የኢትዮጵያን ዘርፈ ብዙ ጠላቶች የሚቀንስ፣ኢትዮጵያን ለማጽናት የተውሰደ ነው» አብይ 7ተኛው ጥፋ እንዳይደገም አሳሰቡ

ውሳኔው “ለኢትዮጵያ የሚበጅ፣ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ጥቅም የሚያግዝ፤ የኢትዮጵያን ዘርፈ-ብዙ ጠላቶች የሚቀንስ በአውደ ውጊያ ያገኘንውን ድል በሰላሙም መንገድ እንድንደግም የሚያደርግ የአባቶቻችን ልጆች መሆናችንን የሚያረጋግጥ ነው” ሲሉ ነው ያስታወቁት። ይህን ያሉት ውሳኔውን ተከትሎ ለተሰማው ተቃውሞ ምላሽ ሊሆን እንዲሆን ነው።

ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ “በግራ በቀኝ ሊነካካን ይሞክራል” ላሉት ህወሓት “አትንኩን፣ እረፉ” የሚል ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል። ማሽነፍ በማይችልበት ጦረነት በዚህ መነካካት ከቀጠለ የትግራይን ልጆች ከማስጨረስ የዘለለ ውጤት እንደማይኖር ጠቁመው የተለመደው ቅጣት እንደሚከናወን አሳስበዋል። ጥፋቱም ሰባተኛው የትህነግ ጥፋት እንደሚሆንም አመልክተዋል።

ተቃውሞ የተሰነዘረበትንና ቅሬታ የተነሳበትን ክስ በማቋረጥ ፖለቲከኞችን የመፍታት ውሳኔ “እየመረረን የዋጥንው እውነት ነው” ሲሉ ገልጸውታል። “የኢትዮጵያን ዘርፈ-ብዙ ጠላቶች የሚቀንስ” መሆኑን ጠቅሰው የተቃወሙ እንዲቀበሉ ጠይቀዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል በቃል አይናገሩ እንጂ ጫና እንዳለ ማብራሪያቸው ያመልክታል።

በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ ለጦር መኮንኖችና ከፍተኛ አመራሮች ሽልማት ሲሰጥ ባደረጉት ንግግር ነው መንግሥታቸው የህወሓት አመራሮችን ከእስር በመፍታቱ ተከትሎ ለተነሳው ቅሬታ አጽኖት ሰጥተው ማብራሪያ የሰጡት። “ብናሸንፍ” አሉ ” ብናሸንፍ የይቅርታ ልብ እንዳለን ፈጣሪ ያውቅ ነበርና ድልን ሰጥን” ያሉት አብይ አሕመድ ” ይህ የአሸናፊነት ይቅርታ ወደፊት ልጆቻችን ቀና ብለው እንዲሄዱ ያደርጋል። ያኮራቸዋል ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ዛሬ ጥር 1 ቀን 2014 ዓ.ም. ባስመረቀው ዋና መሥሪያ ቤት በተካሔደው ሥነ-ሥርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር ባለፉት አመታት ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ሰራቸው ያሏቸውን ስድስት ስህተቶች ዘርዝረው አቅርበዋል። ህወሓት “ለሁለት ተከፍሎ ከፊሉ ብልጽግና [ፓርቲ] ጋር መቆየት ቢችል ኖሮ በርካታ ዜጎቹን መታደግ ይችል ነበር” ሲሉ ተደምጠዋል።

ህወሓት ከኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት በሚቃረን መንገድ “የምርጫ ኮሚቴ በመሰየም ምርጫ ለማድረግ የዳዳበት ሁኔታ እጅግ ዋጋ አስከፍሎታል” ያሉት ዐቢይ በሰሜን ዕዝ ላይ የተፈጸመውን ጥቃትም ጠቅሰዋል። የኢትዮጵያ ጦር ከትግራይ ክልል ሲወጣ “ወጡልኝ ብሎ ከሚከተል ደጋግሞ ቢያስብ ኖሮ የብዙ ወጣቶች ሕይወት ከመቀጠፍ ያድን ነበር” በማለት ተናግረዋል።

“አሁንም ህወሓት በግራ በቀኝ ሊነካካን ይሞክራል” ያሉት ዐቢይ “ለሰባተኛ ስህተት የሚጓዘው ህወሓት በፍጹም ድል የማግኘት እንኳ ቢሆን በወጣት የትግራይ ልጆች ላይ በሕይወት የመቀጠፍ፣ የመቁሰል አደጋ የሚያስከትል ስለሆነ ሰባተኛው ስህተቱ መስመር ስቶ ሳይሄድ መማር የሚችልበት ዕድል መፍጠር የራሱ ቢሆንም እንኳ እንደ ባላንጣ አትንኩን፣ እረፉ ለማለት እወዳለሁ” ሲሉ ተደምጠዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ “የነካካችሁን እንደሆነ በተለመደው መንገድ የከፋ ቅጣት ይደርስባችኋል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ዐቢይ ረዘም ባለ ንግግራቸው የኢትዮጵያ መንግሥት በእስር ላይ የነበሩ ፖለቲከኞችን ክስ በማቋረጥ ለመፍታት የደረሰበት ውሳኔ ለገጠመው ተቃውሞ ምላሽ ሰጥተዋል። ከትናንት በስቲያ መንግሥት የኦሮሞ ፌድራሊስት ኮንግረስ፣ የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ አመራሮችን እና በሰሜን ኢትዮጵያ ውጊያ ከተቀሰቀሰ በኋላ በምርኮ ተይዘው የታሰሩ አንጋፋ የህወሓት አመራሮችን ክስ በማቋረጥ እንዲፈቱ ወስኗል።

“ትናንት ክስ አቋርጠን ከእስር ቤት እንዲፈቱ ያደረግናቸው ግለሰቦች ሁሉም በሚባል ደረጃ የመንግሥት ሥልጣን ይዘው በዚህ ሁኔታ ውስጥ የተሳተፉ፣ በቀጥታ የሚወስኑ የሚያዙ አይደሉም” ያሉት ዐቢይ በውሳኔው ላይ የተሰነዘረው ተቃውሞ ከሁለት ጎራ እንደተቀሰቀሰ ጠቅሰው “ቅን” ላሉት ምላሽ ሰጥተዋል።

የታሰሩ ፖለቲከኞችን ክስ አቋርጦ የመፍታት ውሳኔ የተቃወሙ ወገኖች “እኛም መጀመሪያ ስንሰማው ያስደነገጠን መሆኑን” እንዲገነዘቡላቸው ጠይቀዋል። ውሳኔው “ለኢትዮጵያ የሚበጅ፣ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ጥቅም የሚያግዝ፤ የኢትዮጵያን ዘርፈ-ብዙ ጠላቶች የሚቀንስ በአውደ ውጊያ ያገኘንውን ድል በሰላሙም መንገድ እንድንደግም የሚያደርግ የአባቶቻችን ልጆች መሆናችንን የሚያረጋግጥ” ሲሉ ገልጸውታል። “እየመረረን የዋጥንው እውነት ነው” ያሉትን ውሳኔ የተቃወሙ ወገኖች “እናንተም ለሀገራችሁ ዘላቂ ድል ስትሉ፤ ለሀገራችሁ ክብር እና አሸናፊነት ስትሉ ደጋግማችሁ በማሰብ ይኸንን ውሳኔ እንድትቀበሉ በትህትና እጠይቃችኋለሁ” የሚል መልዕት አስተላልፈውላቸዋል።

የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በጥቅምት 2013 ዓ.ም. ከተጀመረ በኋላ ከታሰሩ የህወሓት አመራሮች መካከል አቶ ስብሐት ነጋ፣ ወይዘሮ ቅዱሳን ነጋ፣ አቶ አባይ ወልዱ፣ አቶ አባዲ ዘሙ፣ ወይዘሮ ሙሉ ገብረ እግዚዓብሔር እና አቶ ኪሮስ ሐጎስ ተቃውሞ በገጠመው የኢትዮጵያ መንግሥት ውሳኔ ይፈታሉ።

ከህወሓት አመራሮች በተጨማሪ የኦሮሞ ፌድራሊስት ኮንግረስ አመራሮች የሆኑት አቶ ጃዋር መሐመድ እና አቶ በቀለ ገርባ፤ የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ አመራሮች አቶ እስክንድር ነጋ እና አቶ ስንታየሁ ቸኮልን ጨምሮ በርከት ያሉ ፖለቲከኞች ተፈተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ክስ የተቋረጠላቸው እና ከእስር የተፈቱ ፖለቲከኞች “እናንተን ሳይሆን ከእናንተ ጀርባ ያለውን ሕዝብ አክብረን የወሰንን መሆናችንን አውቃችሁ ይኸን ዕድል ሳታበላሹ እንድትጠቀሙበት” ብለዋል። “ክስ ማቋረጥ ምህረት አይደለም” ያሉት ዐቢይ መንግሥታቸው የክስ መዝገብ መልሶ ሊመዝ እንደሚችል ጥቆማ ሰጥተዋል።

ዜናው ከጀርመን ሬዲዮ ተወስዶ የተቀየረና የተቀላቀለ ነው።

አዲሱ የመከላከያ ሚኒስቴር ዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ የምረቃ ሥነ-ሥርዓት እየተካሄደ ነው

በግዙፍነቱም ሆነ በኪነ-ሕንፃ ውበቱ እጅግ ዘመናዊ እንደሆነ የተነገረለት የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር ዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ የምረቃ ሥነ-ሥርዓት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት እየተካሄደ ነው።

የኢፌዲሪ መከላከያ ሠራዊት የመዘከሪያ፣
የአውደ ውጊያ ውሎ የሜዳሊያ ሽልማት እና የአዲሱ የመከለከያ ጠቅላይ መምሪያ ህንጻ ምረቃ ሥነ ስርአት እየተካሄደ ነው።

በሰፊ አረንጓዴ ግቢ ውስጥ በ13 ሺህ ካሬ ላይ ያረፈው ባለ 5 ወለል ሕንፃ ከ700 በላይ ቢሮዎች ያሉት ሲሆን የተለያየ ደረጃ ያላቸው የስብሰባ አዳራሾች፣ ቤተ-መጽሐፍት፣ የምርምር ማዕከላት እና የተደራጀ የመረጃ ማዕከል በውስጡ አካትቷል።

ሔሊኮፕተር እና መጠነኛ የጦር ጄቶቸን ማሳረፍ የሚችል 36 ሺህ ካሬ ቦታም ይዟል።

ጦር ኃይሎች አሮጌው አውሮፕላን ማረፊያ አካባቢ የሚገኘው ዋና መሥሪያ ቤቱ ግንባታ የተጀመረው ከዘጠኝ ዓመታት በፊት ነበር።

እንደ ኢቢሲ ዘገባ፤ በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ከፍተኛ የመንግሥት እና ወታደራዊ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

በዚህ የምረቃ ሥነ-ሥርዓተ ላይ ምድር ጦር እና አየር ኃይል ወታደራዊ ትዕይንት እንደሚያሳዩ ተገልጿል።

You may also like...

Leave a Reply