Site icon ETHIO12.COM

የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዜጎች ራሳቸውን እንዲጠብቁ ማሳሰቢያ ተሰጠ

በየጊዜው እየተባባሰ ከመጣው የማህበራዊ ሚዲያ አጭበርባሪዎች ሰለባ ላለመሆን ዜጎች ማንነታቸው ከማይታወቁ ግለሰቦች ጋር በበይነመረብ በሚደረጉት ግንኙነት ላይ ጥንቃቄ እንዲወስዱ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት እና የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ጥምር ግብረ- ኃይል አሳሰበ።

ግብረ-ኃይሉ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ማህበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም የሚፈጸሙ የማጭበርበር ወንጀሎች በይዘትም ሆነ በአፈጻጸም ስልታቸው ውስብስብ እየሆኑ ከመምጣታቸው ባሻገር በርካታ ግለሰቦች የጉዳቱ ሰለባ እንዲሆኑ እያደረገ ነው።

የማጭበርበር ወንጀሎቹ በዋናነት የሚፈጸሙት በውጭ ሀገር የሚኖሩ፣ በቱሪስት ቪዛ ወደ አገር ውስጥ በሚገቡ የተለያዩ ሀገራት ዜግነት ባላቸው ግለሰቦች መሆኑንም በመግለጫው ተጠቅሷል።

ኢትዮጵያዊያን በስፋት የሚጠቀሟቸው ማህበራዊ ሚዲያዎች ማለትም ፌስቡክ፣ ኢ-ሜይል፣ ዋትስአፕ፣ ቴሌግራም፣ ኢንስታግራም፣ ኢሞና ቫይበርን በመጥለፍና ወዳጅ መስሎ በመቅረብ ወንጀሎቹ እንደሚፈጸሙ ከተደረገው ክትትል ማወቅ እንደተቻለም ተገልጿል።

የማጭበርበር ተግባሩን የሚፈጽሙ ግለሰቦችም ሀሰተኛ የሆኑ በአገር ውስጥና በውጭ አገር የሚገኙ ድርጅቶችን ሰነድ፣ የፋይናንስ ተቋማትና የጉምሩክ ሰነዶች የተቋም መለያዎችና ሎጎዎችን፣ የኃላፊዎችን ፊርማ፣ መታወቂያ እንዲሁም የተለያዩ ውሎችን ጭምር ለማጭበርበሪያነት እንደሚጠቀሙ አመልክቷል፡፡

የወንጀሉ ፈጻሚዎች የሚጠቀሙባቸው ስልቶች በየጊዜው የሚለዋወጡ መሆኑን ያመለከተው መግለጫው፤ በውጭ አገራት በኢንቨስትመንት ሥራ ላይ የተሰማሩ በማስመሰል በኢትዮጵያ ውስጥም በዚህ ሥራ ላይ ለመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸውና አብሯቸው የሚሰራ ሰው እንደሚፈልጉ በመግለጽ፣ ለተማሪዎች በዉጭ አገር የትምህርት ዕድል አመቻችተናል በማለትና ሌሎች ተመሳሳይ የማጭበርበሪያ መንገዶችን እንደሚጠቀሙ ተገልጿል።

የተለያዩ የጽህፈት መሳሪያዎችና ላፕቶፖች እንደላኩ በመግለጽ፤ ዉጭ አገር ቤተሰብ ያላቸዉን ግለሰቦች ከቤተሰቦቻቸዉ ጋር የሚደረግን የማህበራዊ ሚዲያ ግንኙነት በመጥለፍ ቤተሰቦቻቸዉ ዕቃ እንደላኩላቸዉ በማስመሰልና በጠለፉት መስመር እንደ ቤተሰብ ሆነዉ በመጻፍ ማረጋገጫ በመስጠት ጭምር እንደሚያታልሉም ተመልክቷል።

በተጨማሪም በፍቅር እንደወደቁና አግብተዉ ወደ ዉጭ ሃገር መውሰድ እንደሚፈልጉ በማሳመን፣ በሰላም ማስከበር ሥራ ላይ ተሰማርተዉ የሚገኙ የዉጭ ሃገራት ወታደሮች ነን በማለት ከአሸባሪዎች በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር እንደያዙና ገንዘቡን ወደ ሃገራቸዉ ይዘው ለመግባት አስቸጋሪ ስለሆነ ዶላሩን ወይም የውጭ አገር ገንዘቡን በስማቸዉ ልከንላችኋል በማለትም በርካታ ዜጎችን እንዳጭበረበሩ ተጠቅሷል።

በሌላ መልኩም በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚንቀሳቀሱ እንደ አንዳንድ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች እድለኛ ሆነዉ እንደመረጧቸዉ እና የድርጅቱ ዋና መስሪያ ቤት ከዉጭ ሀገር ሽልማት እንደላኩላቸዉ በማስመሰል እና ሌሎች የተለያዩ የማጭበርበሪያ መንገዶችን በመጠቀም በከፍተኛ ሁኔታ ጉዳት እያደረሱ ይገኛሉ ብሏል መግለጫው፡፡

ግለሰቦቹ የተለያዩ የማጭበርበሪያ መንገዶችን ተጠቅመዉ ካሳመኑ በኋላ ዉድ እቃዎችን ማለትም የወርቅ ሰዓት፣ ብራስሌት፣ ሃብል፣ ሽቶ፣ ጫማ፣ ቦርሳ፣ የተለያዩ አልባሳት፣ ስማርት ስልኮች፣ ላፕቶፕ እንዲሁም የዉጭ ሃገር ገንዘብ እንደላኩ በማስመሰል እንደሚያታልሉ ተገልጿል።

ለዚህም የላኪና የተቀባይ ስም እና አድራሻ የተጻፈበትን ማሸጊያና የጉምሩክ ሂደቱን በቪዲዮ ቀርጸዉ በመላክ እቃዉን በተጓዦች በኩል በዲፕሎማት፣በጉምሩክ፣ በፖስታ ቤት፣ በዲኤች ኤል፣ ስካይ ወርልድ ወይም በሌሎች አማራጮች ልከንላችኋል በማለት እቃው ለተላከበት ክፍያ የሚሆን ገንዘብ ሃገር ውስጥ በሚገኙት ተባባሪዎቻቸዉ አማካኝነት ሃሰተኛ መታወቂያ በመጠቀም የተከፈተ የሂሳብ ቁጥር ውስጥ ገቢ እንዲያደርጉ ካሳመኗቸዉ በኋላ የገባዉን ገንዘብ ወዲያውኑ ወጪ በማድረግ ወንጀሉን ይፈጽሙታል ብሏል መግለጫው፡፡

በዚህ የማጭበርበር ድርጊቶች ላይ የተሰማሩት ግለሰቦች በተጨማሪም ሀሰተኛ የብር ኖቶችን ማተም፤ሀሰተኛ ሰነድ ማዘጋጀትና መገልገል እንዲሁም የአደንዛዥ እፅ ዝዉዉር ወንጀል ጭምር ላይ ተሳታፊ ሆነዉ የተገኙ ሲሆን፤ በተደረገው ክትትል የውጭ አገር ዜጎች እንዲሁም ኢትዮጵያዊያን በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ ተጣርቶባቸዉ በማረሚያ ቤት የሚገኙ፤ ከአገር እንዲወጡ የተደረጉ እና ጉዳያቸው በምርመራ ሂደት ላይ የሚገኙም እንዳሉ ተጠቅሷል፡፡ 

ይህ የማጭበርበር ድርጊት ግለሰቦች ለረዥም ጊዜ ያፈሩትን ቋሚና ተንቀሳቃሽ ንብረት በመሸጥ ለዚሁ ክፍያ በማዋል ከሚደርስባቸዉ ኢኮኖሚያዊ ጉዳት በተጨማሪ ባለትዳሮች ከትዳር አጋራቸው እውቅና ውጭ የጋራ ንብረትን መሸጥና በዚህ ምክንያት ለትዳር መፍረስ እና ለቤተሰብ መበተን መንስኤ በመሆን ላይ መሆኑም በመግለጫው ተመላክቷል፡፡

በተጨማሪም ከፋይናንስ ተቋማትና ከግለሰቦች በአራጣ ጭምር ገንዘብ በመበደር ከፍተኛ ወለድ እንዲከፍሉ በመደረጋቸዉ በግለሰቦች ህይወት ላይ ጫና እንዲፈጠርና ህይወታቸው አጣብቂኝ ውስጥ መግባቱ ዜጎች በድንገት ሀብት ንብረታቸውን በማጣታቸው የጤና መታወክ ብሎም የስነ-ልቦና ችግር እንዲደርስባቸው በማድረግ ቀውስ እንዲፈጠር እያደረገ እንደሚገኝም መግለጫው አመልክቷል፡፡

ይህን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን ማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ለመከላከል ዜጎች የማህበራዊ ሚዲያን ሲጠቀሙ ማንነታቸው ከማይታወቁ ግለሰቦች ጋር የሚደረጉ ግንኙነትን በጥንቃቄ ማየት እንዳለባቸው ግብረ-ኃይሉ አሳስቧል፡፡ 

በማንኛውም መንገድ እቃ ተላከላችሁ ሲባሉም እቃውን አይተው ሳያረጋግጡ ምንም አይነት ክፍያ አለመፈጸም፤ እቃው ተላከ ወደተባለበት ተቋም በአካል በመሄድ በስማቸው የተላከ እቃ ስለመኖሩ ማረጋገጥ እንዳለባቸውም አሳስቧል፡፡

እንዲሁም በጉምሩክ፣ በፖስታ ቤት፣ በዲኤች ኤል ወይም በሌሎች ድርጅቶች በኩል የተላከ እቃ ወጪ ለማድረግ ገንዘብ ገቢ የሚደረገው በተቋማቱ ስም በተከፈተ የሂሃብ ቁጥር እንጂ በግለሰቦች ስም በተከፈተ የሂሳብ ቁጥር አለመሆኑን ማወቅና በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ምንም ገንዘብ ገቢ ከማድረግ መቆጠብ እንደሚገባ መግለጫው አስገንዝቧል።

እንዲህ ያለ ድርጊት ሲያጋጥምም በቅርብ ለሚገኙ የሕግ አስከባሪ አካላት ሪፖርት በማድረግ የዜግነት ግዴታን መወጣትና ራስንም ከጉዳት መከላከል እንደሚገባ ግብረ-ኃይሉ አሳስቧል፡፡

Exit mobile version