ETHIO12.COM

አብይ አሕመድ “ጠላትም፣ ባንዳም ይወቅ” ሲሉ አስተማማኝ ሰራዊት መግንባቱን አስታወቁ

ዋር ኮሌጅ ከፍተኛ የጦር መኮንኖችን አብቅቶ አስመረቀ፣ ቀለም የተነከሩ ወጣት መኮንኖች መከላከያ እያዘጋጀ ነው

የመከላከያ ዋር ኮሌጅ በደህንነት እና ስትራቴጅ ጥናት የትምህርት መስኮች ዙሪያ ያሰለጠናቸውን 38 ከፍተኛ አመራሮች አስመርቋል። ከተመራቂዎቹም መካከል አስሩ በሁለተኛ ዲግሪ የተመረቁ መሆናቸው ተገልጿል። ” የኢትዮጵያን ህልውና በአስተማማኝ መልኩ የሚያስጠብቅ ሰራዊት መገንባታችንን ባንዳዎችና ጠላቶቻችን ሊያውቁት ይገባል” ሲሉ አብይ አሕመድ አስታወቁ።

ተመራቂዎቹ ከመከላከያ፣ ከፌደራል መስሪያ ቤቶች፣ ከክልሎች እና ከጎረቤት ሀገራት የተውጣጡ ወታደራዊ እና ሰቪል አመራሮች ናቸው።

በቤተ መንግስት በተካሄደው የምረቃ ስነ-ስርዓት ላይ የተገኙት፣ የዕለቱ የክብር እንግዳ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚንስትር እና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ዶክተር አብይ አህመድ ከብዙ ጥረት እና ድካም በኋላ ለምረቃ ለበቁት ተመራቂዎች እና ቤተሰቦቻቸው የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ተምሮ መመረቅ የመጨረሻ ግብ አለመሆኑን የገለፁት ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ ተመራቂዎቹ እውቀታቸውን ሁልጊዜም በቀጣይነት በማሳደግ ለሀገር መስራት ይጠበቅባቸዋል። እውቀትና ልምዳችሁንም ለሌሎች ልታካፍሉ ይገባል ብለዋል።

መከላከያ ራሱን በሰው ኃይል እና በቴክኖሎጅ በማዘመን ኢትዮጵያን ለማስቀጠል በሚያስችል አስተማማኝ የዝግጁነት ደረጃ ላይ እንደሚገኝም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልፀዋል።

ጠላቶቻቸን ከፀብ አጫሪነት ድርጊታቸው ሊቆጠቡ ይገባል ያሉት ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ካልሆነ ግን እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ አስተማሪ የሆነ እርምጃ ይወሰዳል ሲሉ ገልፀዋል።

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ በበኩላቸው ሰራዊታችን ህገ መንግስታዊ ተልዕኮውን መሰረት በማድረግ፣ ከሌሎች የደህንነት እና የፀጥታ ኃይሎች ጋር በመቀናጀት የሀገርን ሉዓላዊነት እና የህዝብን ሰላም የማስጠበቅ ግዳጁን በአኩሪ ተጋድሎ በመፈፀም የተጋረጠብንን የህልውና አደጋ ስጋት ዳመና እንዲገፈፍ ማድረግ መቻሉን ገልፀዋል።

ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ ሰራዊታችን ዛሬም በየአቅጣጫው የተነሱብንን ፀረ ኢትዮጵያ ኃይሎችን በመፋለም ላይ ይገኛል ብለዋል።

የኢፌድሪ መከላከያ ዋር ኮሌጅ ዋና አዛዥ ብ/ጀኔራል ቡልቲ ታደሰ ባቀረቡት የስልጠና ሪፖርት ተመራቂዎቹ በህልውናና የህግ ማስከበር ዘመቻ እና በዘመቻ ለህብረ ብሄራዊ አንድነት ወቅት አኩሪ ጀግንነት መፈፀማቸውን ገልፀዋል።

ብ/ጀኔራል ቡልቲ እንዳሉት ተመራቂዎቹ በትምህርት ቆይታቸው አካባቢያዊ እና አለማቀፋዊ የደህንነት ምህዳርን፣ የሀገራችንን የደህንነት ስትራቴጅዎች፣ በፖሊሲዎች እና በብሄራዊ ጥቅም ማስፈፀሚያ አቅሞች ዙሪያ ጥልቅ እውት ማገኘታአውን ገልፀዋል።

ውስን የሀገር ሀብትን በአግባቡ አቀናጅቶ በውጤት መምራትን እና የጦርነት ምንነትን እና ግጭቶችን ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ እንዴት መከላከል እና መፍታት እንደሚቻል እንዲያውቁ መደረጉንም ተናግረዋል።

ተመራቂዎቹ በሰጡት አስተያየት በትምህርት ቆይታቸው የሀገራችንን ሰላም እና ደህንነት ለማረጋጋጥ በሚደረገው ጥረት ውስጥ በእውቀት ላይ የተመሰረተ አስተዋፅኦ ለማበርከት የሚያስችል አቅም መፍጠራቸውን ገልፀዋል።

በምረቃ ስነ -ስርዓቱ ላይ ጀነራል መኮንኖች፣ የሀገራት አምባሳደሮች እና ወታደራዊ አታሼዎች፣ የተመራቂ ቤተሰቦች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

በላቸው ክንዴ
ፎቶ ግራፍ ተሰማ ኡርጌሳ ENDF

Exit mobile version