Site icon ETHIO12.COM

ሩሱያ ማሪፖልን ሙሉ በሙሉ እጇ አስገባች፤ ጀርመንና ጣሊያን በሩብል ለመገበያየት ተስማሙ

ሩሲያ ወታደሮች የዩክሬን የወደብ ከተማ የሆነችውን ማሪፖል ሙሉ በሙሉ መቆጣጠራቸውን የአገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡ ጀርመንና ጣሊያን ነዳጅ በሩብል ለመግዛት ተስማምተዋል።

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ኢጎር ኮናሸንኮቭ እንደገለጹት÷ ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታዋ ከፍተኛ የሆነችውን የዩክሬን ወደብ ከተማ ማሪፖልን ለመቆጣጠር ለአንድ ወር ያክል ጊዜ የተደረገው ውጊያ በድል ተጠናቋል፡፡

ቃል አቀባዩ በማሪፖል ከተማ አቅራቢያ በሚገኘው አዞቭስታል የተሰኘው ብረት ፋብሪካ ውስጥ መሽገው ሲዋጉ የቆዩ 531 የዩክሬን የመጨረሻ ወታደሮች ለሩሲያ እጅ መስጠታቸውን አረጋግጠዋል፡፡

ይህን ተከትሎም የሩሲያ ወታደሮች የዩክሬን የወደብ ከተማ የሆነችውን ማሪፖል እና አዞቭስታል የብረት ፋብሪካን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር መቻላቸውን ነው የገለጹት፡፡

የዩክሬን ፕሬዚዳን ቮሎድሚር ዘለንስኪ በአዞቭስታል የብረት ፋብሪካ የሩሲያን ጦር ሲመክቱ የነበሩ የአገሪ ወታደሮች ስፍራውን ለቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ ሰጥተው እንደነበርም ሞስኮ ታይምስ በዘገባው አስፍሯል፡፡

የሩሲያ ጦርም አካባቢውን በአስተማማኝ ሁኔታ ሙሉ ለሙሉ ለመቆጣጠር በአየር አና በምድር ጦር የታገዘ ዘመቻ ማካሄዱ ተመላክቷል፡፡

ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ቃልኪዳን ጦር ወይም ኔቶን እቀላቀላለሁ ማለቷን ተከትሎ ከሩሲያ ጋር ወደ ይፋዊ ጦርነት ካመራች ሶስት ወር ሊሞላው ጥቂት ቀናት ብቻ ቀርተውታል።

ጦርነቱን ተከትሎ በሩሲያ ላይ ከ6 ሺህ በላይ ማዕቀቦች የተጣሉባት ሲሆን ከ300 በላይ ዲፕሎማቶቿ ደግሞ ከተለያዩ ሀገራት ተባረዋል፡፡

ሩሲያም የአጻፋ እርምጃ በመውሰድ ላይ ስትሆን ነዳጅ ገዢ ሀገራት በሩብል እንዲገዙ ውሳኔንም አሳልፋለች፡፡

የአውሮፓ ህብረት በሩሲያ ነዳጅ ገበያ ላይ ጠንካራ ማዕቀቦችን የጣለ ቢሆንም የህብረቱ አባል ሀገራት ግን በተናጥል ነዳጅ ከሩሲያ በሩብል ለመግዛት በመስማማት ላይ ናቸው፡፡

ሩሲያ 40 በመቶ የአውሮፓ ሀገራትን የነዳጅ ፍላጎት የምታሟላ ሲሆን ከዩክሬን ጋር ጦርነት መጀመሯን ተከትሎ ማዕቀቦች ቢጣሉም እነዚህ ሀገራት የነዳጅ ፍላጎታቸውን ከሌላ ሀገር ማግኘት አልቻሉም፡፡

የአውሮፓ ህብረት ዋነኛ አጋር የሆኑት የጀርመን እና ጣልያን ነዳጅ አከፋፋይ ኩባንያዎች ነዳጅ ከሩሲያ ጋር በሩብል ለመግዛት አካውንት ሊከፍቱ መሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡እንደ ዘገባው ከሆነ የሁለቱ ሀገራት ኩባንያዎች የአውሮፓ ህብረት የጣለውን ማዕቀብ ሳይጥሱ የሩብል አካውንት ለመክፈት ወስነዋል፡፡

ይሁንና ፖላንድ፣ፊንላንድ እና ቡልጋሪያ ግን የሩሲያን ነዳጅ በሩብል ላለመግዛት በመወሰናቸው ሩሲያ ነዳጇን ለነዚህ ሀገራት መሸጥ አቁማለች፡፡የጣልያኑ ጋዝ አከፋፋይ ኢናይ የጠሰኘው ኩባንያ የሩሲያን ነዳጅ ለመግዛት የሩብል እና የዩሮ አካውንት ለመክፈት እንቅስቃሴ ላይ መሆኑን አስታውቋል፡፡

የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት የምግብ እና ሸቀጦችን ዋጋ በማናር የዓለምን ኢኮኖሚ ሊያቃውስ እንደሚችል የዓለም ባንክ ከሁለት ወር በፊት ማስጠንቀቁ ይታወሳል፡፡

ጦርነቱ አሁንም የቀጠለ ሲሆን ከ6 ሚሊዮን በላይ ዩክሬናዊያን ሀገራቸውን ጥለው ወደ ጎረቤት ሀገራት ሲሰደዱ የዓለም ምግብ ዋጋ በመናር ላይ ይገኛል፡፡

የምርቶች ዋጋ መናር በአውሮፓ በታሪክ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰ ሲሆን በእንግሊዝ የዋጋ ግሽበቱ ከ40 በመቶ በላይ ሲሆን በሌሎች የአውሮፓ ሀገራት ላይም በመጨመር ላይ ይገኛል፡፡

አል አይንና ፋና

Exit mobile version