Site icon ETHIO12.COM

የነጻ አውጪ ድርጅቶችን ያካተተ የተቃዋሚ ፓርቲዎች የምክክር ቤት (caucus) ተቋቋመ-በምርጫ ዜሮ ድምጽ ያገኘ ፓርቲም አለበት

በኢትዮጵያ ውስጥ በነጻ አውጪነትና በብሄር ድርጅትነት የሚታወቁ ሙሉ በሙሉ የተካተቱበት አዲስ የፓርቲዎች የምክክር ቤት (caucus) መቋቋሙ ተገለጸ። በስም ከተዘረዘሩት የምክክር ቤት አባል ድርጅቶች ውስጥ ከአፋር ሁለት፣ ከኦሮሚያ ሁለት፣ ከትግራይ አረና፣ የወላይታና የዶንጋ ሕዝቦች ይገኙበታል። በፓርቲ ደረጃ መድረክ ሲገኝ፣ በቅርቡ በተካሄደው ምርጫ አዲስ አበባ ላይ ዜሮ ድምጽ ያገኘው ህብርም አለበት።

መንግስት ከትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር ጋር ሙሉ ውጊያ ገብቶ በነበረበት ወቅት ጡንቻ ያበቀሉ ያላቸውን እያጸዳና የህግ ማስከበር እያካሄደ ነው በሚባልበት ወቅት ላይ፣ በተለይም በኦሮሚያና አማራ ክልል ይቀሰቀሳል የተባለው ውጊያ መልኩን እንደቀየረ ምልክቶች በሚታዩበት ወቅት ይህ ህብረት መመስረቱ በርካቶችን ከጅምሩ አወያይቷል።

ትህነግ የፌደራል ሃይሎች ሲል መስርቶት ከነበረው ጥምረት ጋር በግልጽና በህቡዕ ግንኙነት እንዳላቸው በስም ሲጠቀሱ የነበሩ ፓርቲዎችን ያካተተው የምክክር ቤት ትህነግን በስም አላካተተውም። ከኦሮሚያ ኦፌኮን ኦነግ አባላት ናቸው። የኦፌኮ ስራ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ ጃዋር መሐመድ ይህንን የምምክር ቤት ዜና ” ሰበር” ብሎ ከዘገበው ኡቡንቱ ጋር የመጀመሪያ ውይይት ሲያደርጉ ” ከማንም ጋር ለሰላም እሰራለሁ” ማለታቸው ይታወሳል። ህበረቱም ይፋ የሆነው እሳቸው ለፖለቲካ ስራ ወደ ጀርመን ማቅናታቸውን ተከትሎ መሆኑም “ግጥምጥም” አስብሎታል።

ብልጽግና የአገራዊ የምክክር መድረኩ ፓርቲው በተመረጠበት የኮንትራት ዘመኑን አስመልክቶ የሚነጋገረው ነገር እንደሌለ ማስታወቁ አይዘነጋም። ምክከር ቤት የተባለው የአስር ፓርቲዎች ስብስብ ገና ከጅምሩ ያስቀመጣቸው ሃሳቦች ቀደም ሲል እነ አቶ ልደቱ ” የሽግግር መንግስት” ከሚሉት አካሄድ ጋር መዛመድ እንደሚታይበት ዜናውን ተከትሎ በማህበራዊ ገጾች ከወዲሁ እየተገለጸ ነው። መድረኩ ነጻ አውጪ ድርጅቶችን ሙሉ በሙሉ ካካተተ ለምን ትህነግን እንደዘለለ ግልጽ አለመሆኑም ተመልክቶበታል። ከስር ኡቡንቱ ያሰፈረውን ዜና እንዳለ አትመነዋል።

በሀገራዊ የምክክር መድረክ አካሄድ ላይ መሰረታዊ ቅሬታ አለን ያሉ 10 የሚደርሱ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች “እውነተኛ የዴሞክራሲ ስርአትን የሚያስገኝ ሀገራዊ ውይይት አማራጭን ለማቅረብ የሚያስችል የምክክር ቤት (Caucus) አቋቁመናል” ሲሉ በዛሬው ዕለት ባወጡት መግለጫ አሳውቀዋል።

ሀገራዊ ምክክር በምን መልኩ ይካሄድ በሚለው ላይ ክርክሮች እየተደረጉ ባለበት ወቅት ” መንግስት ሂደቱን የሚቆጣጠር ረቂቅ ህግ በማዘጋጀት በአንድ ፓርቲ የበላይነት ባለው ፓርላማ በኩል የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጥያቄ እና የግብአት ሀሳብ ችላ በማለት እንዲፀድቅ ማድረጉን ያስታወሰው የፓርቲዎቹ መግለጫ የኮሚሽነሮቹን ምርጫም “የተድበሰበሰ” ነበር ሲል ኮንኗል።
በትጥቅ እየተፋለሙ የሚገኙ አካላትን ወደ ምክክሩ ለመጋበዝ የተቀመጠ ድንጋጌ አለመኖሩን የነቀፈው የምክክር ቤቱ መግለጫ “አማራጭ” በተባለው አዲስ የምክክር ቤት (Caucus) በኩልም ለመንግስት በርከት ያሉ ምክረሀሳቦችንም አቅርቧል።

በምክረሀሳቦቹም ላይ:-
-አፋጣኝ እና አለም አቀፍ ተቋማት የሚቆጣጠሩት የተኩስ ማቆም በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች ላይ እንዲደረግ
-የምክክር ኮሚሽኑ በድጋሜ እንዲቋቋም እና ኮሚሽነሮቹም ገለልተኛ በሆነ መንገድ እንዲመረጡ

የምክክር ቤቱን የመሰረቱት ፓርቲዎችም
1- መድረክ
2- ህብር ኢትዮጵያ
3- የአፋር ህዝብ ፓርቲ
4- የአፋር ፍትህ እና ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ
5- የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)
6- የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ
7-የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር
8- የዎላይታ ብሄራዊ ንቅናቄ
9- ዓረና ትግራይ
10- የዶንጋ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት
መሆናቸው ተገልፃል።

ስለ ምክክር ቤቱ ለሚዲያችን አስተያየታቸውን የሰጡት የአፋር ህዝብ ፓርቲ መሪ እና የምክክር ቤቱ ሊቀመንበር ሆነው የተመረጡት አቶ ሙሳ አደም
“ፓርቲዎቹ በተለያየ ጉዳይ ላይ የተለያየ አቋም ቢኖራቸውም ሀገራዊ ምክክሩ በሀቀኛ መንገድ መከናወን አለበት የሚለው ላይ ግን የማያወላዳ የጋራ አቋም አላቸው፤ አማራጭ የምክክር ቤት ለማቋቋም የወሰነውም ለዚህ ነው”
ብለዋል።

UbuntuNews

Get new recipes delivered to your inbox.

Exit mobile version