Site icon ETHIO12.COM

ከ12 ሺህ 400 በላይ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ገለጸ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ፣ ፍትሕ እና ዴሞክራሲ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ በአማራ ክልል የተካሄደውን የሕግ ማስከበር ርምጃ እና የተጠርጣሪዎችን አያያዝ እየገመገመ ነው።

የክልሉን ሁለንተናዊ ሰላምና ደኅንነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ ሲባል በሕገወጥ ተግባራት ላይ ተሰማርተዋል የተባሉ ተጠርጣሪዎችን በሕግ ቁጥጥር ሥር የማዋል ርምጃ ሲከናወን ቆይቷል። በዚህም በፋኖ ስም የሚነግዱ እና በተለያዩ ኢ-መደበኛ አደረጃጀቶች ተደራጅተው በግድያ፣ በዝርፊያ፣ በአስገድዶ መድፈር፣ ከአሸባሪ ቡድኖች ጋር ተልዕኮ ወስደው የክልሉን ሰላም በማናጋት ወንጀሎች የተጠረጠሩ ከ12 ሺህ 400 በላይ ተጠርጣሪዎች በሕግ ቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ተኮላ አይፎክሩ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ፣ ፍትሕ እና ዴሞክራሲ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ አስረድተዋል።

በቁጥጥር ሥር ከዋሉ ተጠርጣሪዎች መካከልም 3 ሺህ 746 የሚኾኑት የመከላከያ፣ የልዩ ኀይል እና በመደበኛ ፖሊስ አባላት የነበሩ ሲኾን ከ8 ሺህ 700 በላይ የሚኾኑት ደግሞ ከፀጥታ መዋቅር ውጭ የኾኑና በልዩ ልዩ ወንጀሎች የተጠረጠሩ መኾናቸውን ኮሚሽነሩ አብራርተዋል።

በሕግ ማስከበር ርምጃው በቁጥጥር ሥር ከዋሉት ተጠርጣሪዎች መካከልም ከ3 ሺህ 750 በላይ የሚኾኑት በዋስ እና በመሰል የማጣራት ሥራ የተለቀቁ መኾናቸው ተገልጿል።

በኬላ በተደረገ ቁጥጥር እና ፍተሻም ወደ ለአሸባሪው ትህነግ ሊተላለፍ የነበረ ከ37 ሚሊዮን ብር በላይ በቁጥጥር ሥር ውሏል ተብሏል።

የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ተኮላ አይፎክሩ በተወሰደው የሕግ ማስከበር ርምጃ ክልሉ ላይ ከሕገወጥ ተኩስ ጀምሮ በርካታ ወንጀሎች መቀነሳቸውን ጠቅሰው አበረታች የሰላም ለውጥ እንደታየ ተናግረዋል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት የሕግ፣ ፍትሕ እና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ እፀገነት መንግሥቱ የሕዝብን ሰላም በዘላቂነት ለማረጋገጥ የሕግ ማስከበር ርምጃው መተግበሩ የሚያበረታታ መኾኑን ጠቅሰዋል። በተለያዩ የፖሊስ ጣቢያዎች እና ማረሚያ ቤቶች የሚገኙ ተጠርጣሪዎች አያያዝን የሕግ፣ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ተዘዋውረው የሚመለከቱ እና በቀጣይ ግብረ መልስ የሚሰጡ ይኾናል።

(አሚኮ)

Exit mobile version