Site icon ETHIO12.COM

ከህወሓት ጋር የገጠመንን ግጭት በድርድር ለመፍታት የተጀመሩ ጥረቶች የሚደገፉ ናቸው

ከህወሓት ጋር የገጠመንን ግጭት በጠረጴዛ ዙርያ ለመፍታት የአፍሪካ ህብረት ተወካዮች ጀምረናል ያሉት ጥረት የሚደገፍና ተመራጭ መንገድ መሆኑን ዶ/ር ተመስገን ቶማስ የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ኘረዝደንትና የሰላም ተመራማሪ ተናገሩ።

አለመግባባትን ወይንም ጦርነት የምትቋጭበት አማራጭ ብዙ ነው። በያዝነው ክፍለዘመን ግጭትን በጦርነት ለመቋጨት አዳጋች ነው። ጦርነት በሁለት አካላት መካከል ቢካሄድም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ፍላጎት ያላቸው ሀገራትና ቡድኖች የሚያሳድሩት ተፅዕኖ በቀላሉ የሚታይ አይደለም ብለዋል። በዚህም ምክንያት ግጭት ውስጥ የገቡ አካላት በቀላሉ ሰላምና መረጋጋትን ለማምጣት ሊቸገሩ እንደሚችሉ ዶ/ር ተመስገን ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ በሰሜኑ ክፍል ባጋጠማት ግጭት ሩቅ ሳንሄድ ጎረቤት የኢትዮጵያ ወዳጅ ናቸው ተብለው የሚገመቱት እንደኡጋንዳ እና ሩዋንዳ ያሉ ሀገራት ሰልፋቸውን ከጠላት ጋር ያደረጉበትን ክስተት በአስረጅነት አንስተዋል።

በአለም አቀፍ ደረጃ በራሽያና በዩክሬን ጦርነት የአፍሪካ ሀገራት ሳይቀሩ በአስታራቂነት ስም የጣልቃ ገብነት ዝንባሌ ያሳዩት ፍላጎት ስላላቸው ነው። ምክንያቱም ሀገራቱ በነዳጅ፣ በስንዴና በማዳበሪያ ላኪነት የሚታወቁ በመሆኑ የሚያሳድሩት አሉታዊ ተፅእኖ ከባድ በመሆኑ ነው።

ሰላምን በሰጥቶ መቀበል ወይንም በድርድር ለማምጣት ረጅም ርቀት መጓዙ እንደተጠበቀ ሆኖ እንደአሜሪካና አውሮፓ ሀገራት በሒደቱ አዎንታዊ ሚና እንዲጫወቱ የዲኘሎማሲው ትግል ጎን ለጎን ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስረድተዋል።

የአፍሪካ ህብረት የአደራዳሪነት ሚና ምን ድረስ ሊያስኬድ ይችላል የሚለው በሁለቱም ወገኖች በጥንቃቄ መታየትና መተማመንን መገንባት በሚያስችል መልኩ መጓዝ እንዳለበት ሙያዊ ምክረ ሃሳብ ያቀረቡት ዶ/ር ተመስገን በአንድ ወገን መጠራጠር ካለ ሒደቱን ቆም አድርጎ ሌላ አደራዳሪ አካል መፈለጉ አዋጭ እንደሚሆን ጠቁመዋል።

ሰላም ጦርነት የሌለበት (Lack of war or Lack of violence ) ማለት አይደለም። ምክንያቱም የሰላም እጦት መዋቅራዊ በሆነ መልኩም ሊከሰት ይችላል። እኩልነት፣ ፍትህን የማያረጋግጥ፣ የህግ የበላይነትን የማይቀበል፣ አግላይ አካሄድ የነገሰበት፣ የመልካም አስተዳደር ችግር የሰፈነበት ሁኔታ ካለ መዋቅራዊ ጭቆና አለ ይባላል። ይህ በእርግጥም ተከስቶ ከሆነ መታገል ያስፈልጋል ብለዋል። በዚህም ረገድ ዩኒቨርሲቲዎች ሰላም ወዳድ አምራች ዜጋን በማፍራት ረገድ ብዙ መሥራት እንደሚጠበቅባቸው ዶ/ር ተመስገን ጠቅሰዋል።

Ethio tube

Exit mobile version