Site icon ETHIO12.COM

ይድረስ ለወዳጄ ሐብታሙ ኪታባ

መቼም ላንተ ያለኝ ክብር እንዴት ትልቅ መሆኑ አይጠፋህም፤ አንዱዓለምን ደግሞ አንተ ከምትወደው በላይ እወደዋለሁ፡፡ ስለ ትይዩ ካቢኔው በቢቢሲ አማርኛ የተናገረው ትንሽ ቅር እንዳሰኘኝ ግን ንገርልኝ፡፡ ስራዬን ትቼ በሙሉ ጊዜ የሰራሁትን ገና በጅምር ነው ማለቱ አልተዋጠልኝም፤ ለዚህና ለሃሳባቸው ልዕልና የነ ካሱን ስብስብ መደገፌም ይታወቅልኝ፡፡

ማክሰኞ ምሽት በፋና ቴሌቭዥን ያደረከውን ጥያቄና መልስ ተመልክቼ ግን የእናንተ አካሄድ በጥቅሉ ብዙ ህጸጾች ያሉበትና በቂ የፖለቲካ ትንታኔ ያልዘለቀው ሆኖ ታይቶኛል፡፡ እንደ አጋጣሚ ሆኖ የቃለ መጠይቁ ስህተቶችህም ሰባት ዋና ዋና ሆነው አገኘኋቸው(የካሱ ነጥቦችም ሰባት መሆናቸው ገጠመኝ ብቻ ነው)፤ ስህተቶቻችሁን ለማረም ጊዜው የረፈደ ቢሆንም በቅዳሜና እሁዱ ምርጫ እንደምትሸነፉ ስለምገምት (ይህንን አስቀድሜ በስልክም ነግሬህ እንደነበረው) ለወደፊት የፖለቲካ ህይወትህ ይጠቅምህ ዘንድ እነዚህን ነጥቦች በአደባባይ ላስጣልህ

  1. “ኢዜማ እነዚህን ሰባት ነጥቦች ሊያሳካ የሚችለው ተመርጦ መንግስት ሲሆን ነው፤”

ይህን ስትናገር ጋዜጠኛው ይበልጥ በሞገተህ ነበር ያልኩት፤ እንደ አለማወቅም ይሁን ከክህሎት ማነስ አገዘህ እንጂ፡፡ እነዚህ ነጥቦች መንግስት ሳንሆን መሳካት ከቻሉ ያናደናል እንዴ? እሰየው ነው እንጂ፡፡ የሰላምና ደህንነት መፈጠር፣ ሙስናን መዋጋት፣ የዘር ፖለቲካን ወደ ማክሰም መሄድ፣ የተረጋጋ ኢኮኖሚ መፍጠርና ሌሎቹም ሃሳቦችን ብልጽግናንም ሆነ ሌላ ፓርቲን በማገዝ ከቀረፍን እልል በቅምጤ አይደለም ወይ ?
ይህ ባለፉት 9 ወራት በምን ያህልም ተፈጽሞ ቢሆን የኢዜማ ሚና ቀላል ሊሆን አይችልም፡፡ በካቢኔ ውስጥ ባለን አንድ ወንበር ሳይሆን ለሰላም ብለን በከፈልናቸው ብዙ ዋጋዎች፡፡ ከመንግስት ጋር በመስራታችን ሳይሆን፤ ህዝብን ለሉዓላዊነትና ለአንድነት በማንቃታችን፡፡ እናም ኢዜማ ኢኮኖሚውን ማረጋጋትም ሆነ ሰላም ማምጣት ላይ ውቅያኖስን በጭልፋ ቢሆንም አስተዋጽዖ አድርጓል፤ ወደፊትም ያደርጋል፡፡ ይህ ደግሞ በብርሀኑ መሪነት ሳይሆን በስትራቴጂክ ዕቅዳችን አስገዳጅት የሚሆን ነው፡፡ መንግስት ሳንሆንም 7ቱ ነጥቦች ይሳካሉ፤ ለዚህም ከመንግስት ጋር አብረን መስራታችን (ብልጽግና ቀሽም ፓርቲ ሆኖ ያዘገየን ይሆናል እንጂ) ስኬቱን ያፈጥነዋል፡፡

  1. “ስትራቴጂክ ግቦቹ እንዳይሳኩ ተጠያቂው ማነው?”

ይህንን ለምን ማድበስበስ እንደፈለክ ይገባኛል፡፡ ዋናው ተጠያቂ ግለሰብ እንዳልሆነ አንተም ታውቀዋለህ፤ የማይነበበው አመራር በተለይም በሊቀመንበር መዋቅር ያለው የዕውቀት ማነስና መሪውን የመጠርጠር ከንቱ ፍራቻ ትልቁን ድርሻ ወሳጅ ነው፡፡ የአንዱዓለምን ተጠያቂነት የወሰድክለትን ያክል ለብርሀኑም ብትሸፍንለት አከብርህ ነበር፡፡ አንተም ሆንክ የቅርብህ ሰዎች ብርሀኑን ባለመስራት አትከሱትም፤ ማልዶ ስራ ላይ መሽቶም ከስራው ነው፡፡ ግቦቹ እንዳይሳኩ ያደረገው አለመናበብ ከምርጫው ማግስት ሲነሳ ግን ምክትል መሪነት ያለው የስራ ብዛት ፍንትው ብሎ እንዳያሳጣህ ማሰብ ነበረብህ፡፡

  1. “የምክትሉ ስራ መሪው ሳይኖር ተክቶ መስራት ነው” ያልከው አባባል

የምክትሉ ስራ መተካት አይደለም፡፡ ይህ ቢሆንማ አንተም ደፍረህ ለምክትልነት ባልተወዳደርክ፡፡ እኔን የትይዩ ካቢኔ አባል እንድሆን የጠራኝ አንዱዓለም ነው (ምክትሉ አንዱዓለም)፡፡ በምርጫ ማኔጅመንት ኮሚቴው የሐብት አሰባሰብ ቡድን መሪው አንዱዓለም ነበር፡፡ ይህ ሁሉ ቢቀር እንደ አንድ የስራ አስፈጻሚ አባል የፓርቲው ከፍተኛው ስልጣንን በጋራም ሆነ በቡድን ይይዝ የለም እንዴ
መሪው ደግሞ ሚኒስትር ናቸው፤ ስራ ቢደራደብባቸው ያለ ውክልና ያለውን ስልጣን መጠቀም የሚችል፣ የቼክ ፈራሚ አድራጊና ፈጣሪው አንዱዓለም አራጌ ነበር የሚሆነው፡፡ ይህ ተሰውሮብህ አይሆንም፤ እንኳን ይሄን ስንቱን ገላልጠህ የምታሳይ የበራልህ መሆንህ አውቃለሁ፡፡ ለመቀስቀሻና ከኃላፊነት ለመራቅ ማድረግህ ግን አሳዝኖኛል፡፡

  1. በፓርቲው መሪ የተወሰነ ቅቡልነት የሚያሳጣ ተግባር አለ? ተብለህ ለተጠየከው

እዚህ ላይ የግርማ ሰይፉን ሹመት አንስተህ ነበር፡፡ መሪው ይወስን እንጂ፤ ይምረጥ፣ ያሹም፣ ኃላፊነቱንም ይወጣ፡፡ መሪ ያደረግነው እንዲሰራና እንዲያሰራ አይደለም እንዴ? በቡድን እከሌ ይሂድ እንዲባል ጠብቀህ ከነበረም ስህተት ነው፡፡ በኢዜማ መተዳደሪያ ደንብ መሰረት የመንግስት ነክ ሹመቶችን የሚሰጠው መሪው መሆኑ በአንቀጽ 7.1 ተቀምጧል፡፡

  1. አብረን በመስራታችን ውጤት አልመጣም ያለው ማነው? ብዬ ልጠይቅህ

ከንግግርህ ድምጸት ያስተዋልኩት ትልቅ ነጥብ ከመንግስት ጋር በመስራታችን ለኢዜማም ሆነ ለአገር የመጣ ለውጥ የለም፤ ከሰባቱም ዜሮ ነው ማለትህ ያለው ስህተት ነው፡፡ ይህንን በስፋት ፕሮፍ በጠቅላላ ጉባዔው ላይ ያቀርባል ያልከውም እራስህ ነህ (በዚሁ ቃለ ምልልስ) ታዲያ ከቀረበ በኋላ ብናነሳው አይሻልም፡፡ ለእኔ ግን ኢዜማ ከመንግስት ጋር በመስራቱ ያተረፈው የትየለሌ ቁምነገሮች አሉ፤ ቀዳሚው ነገር ከጥቂት ዓመታት በኋላ መንግስት ስንሆን የተቋም አመራር ልምድ ያላቸው ሰዎች ይዘን መጀመራችን ሲሆን ፕሮፍ Learn how it works የሚለን ማለት ነው፡፡ ቀጣዩ ትርፍ ሁለተኛው የስትራቴጂክ ግባችን ነው፤ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር የመስራታችን ግብ፡፡ ሌሎቹን ከቡባዔ በኋላ አንተም ታጋራኛለህ፡፡

  1. የሰባቱ ነጥቦች ግምገማ ለምን ለውይይት አልመጣም?

ይህ እንኳን በግልጽ የካድረከው ነው፡፡ ስራ አስፈጻሚው የነጥቦቹ ግምገማ የሚሰራበትን መለኪያ ካበጀ በኋላ መድረኩ እንዲፈጠር የማይፈልጉ ስራ የማይሰሩ አመራሮች ከአንት ጋር ነበር ስራ አስፈጻሚ ሆናችሁ ስትሰሩ የነበረው፡፡ ግምገማ በየጊዜው እየተከወነ ክትትል ማድረግ የማን ስራ ሆነና ነው ለውይይት ይመጣ ዘንድ ከፕሮፌሰር የሚጠበቀው?

  1. ከእኛ በተቃራኒው ያለው ካምፕ የኮንደሚኒየሙ ጥናት እንዳይወጣ ይፈልግ ነበር፤ የጦርነቱ ትንተና ተጠንቶ እንዳይተላለፍ ሆኗል፤(ያንን የከለከለው ማነው)

ይህ ደግሞ ፈጽሞ ስህተት ነው፡፡ ራስህን እንዲህ ብለህ ካሳመንክ ወይም መላምት ከወሰድክ ተታለሀል፡፡ ካስታወስክ የብልጽግና ጉባዔን በተመለከተ የታዩ አሳፋሪ ጉዳዮችን በተለይም ዶክተር ዐቢይ መድረክ ላይ ሆኖ ራሱን ማስመረጡንና ጉባዔውን በህዝብ ብር ከመንግስት ካዝና ማድረጉን አስመልክተን መግለጫ እንድናወጣ ያዘዘን ፕሮፌሰር ብርሀኑ አልነበረም? ብርሀኑ ታዲያ በተራ የኮንዶሚኒየም ሪፖርት ላይ ሸብረክ የሚለው በምን አግባብ ነው፡፡ የጦርነቱን ትንተና ማን እንዳፈነውም ስትጠየቅ ዝም አልክ፡፡ ለምንድን ነው ለፕሮፌሰር የመዘዝከው ሰይፍ ለሊቀመንበር መዋቅር ሰዎች ከሰገባው የማይወጣው?

ከሰባቱ ስህተቶችና የንግግር ወለምታዎች ጋር የማይደመሩ የሚከተሉት ህጸጾችም ከቃለመጠይቅህ የታዪ ነበሩ፡፡

፨ በኢዜማ ቤት ባልተለመደ መልኩ ህወሓትን ጁንታ ብለዋል፤ ይህን ተቀጽላ ስም ያወጣው ዶክተር ዐቢይ ነበር፡፡ በመግለጫም ሆነ በንግግር Derogatory labeling ስለሆነ አንጠቀመውም፤ አንተ ግን ሁለት ጊዜ መጠቀምህ የንግግር ወለምታ ነበር፡፡

፨ የኢዜማን የቤት ስራና የጠቅላላ ጉባዔው እንጂ ሌላው አባል እንኳን ሊወስንበት የማይችል ሆኖ ሳለ ህዝብ እንዲያውቅልን የምንፈልገው በሚል ለህዝብ ቀጥታ ቅስቀሳ አድርገሃል፡፡ ይህ እንኳን ደጋግማችሁ ያደረጋችሁት በመሆኑ ስህተት ሳይሆን የአመለካካት ችግር ነው፡፡

፨ ህወሐት የአማራ ክልልን ተቆጣጥሮ ባለበት ሁኔታ ነው መደራደር አለበት ያላችሁት ለሚለው ጥያቄ ረዥም የማሰቢያ ጊዜ ወስደው ለመመለስ ቢሞክሩም የአንዱዓለም የሰላም ሀሳብ መች እንደተነሳ ለማስታወስ አልቻሉም፡፡ እኔ ላስታውሳቸው፤ ወዳጄ አንዱዓለም ከህወሐት ጋር ድርድር ይደረግ ሲሉ ህወሓት ወልዲያ ለመግባት ከበባ ላይ ነበር፡፡ ወደ አምስት ገጽ ሃሳባቸውን ሲያሳጥሩ ደግሞ ወልዲያ ተይዛ ወደ ደሴ እየገሰገሰ ባለበት ወቅት ነው፡፡ ምስራቅ አማራ በከፊል ተይዞ ታዲያ የምን ድርድር ነው፤ የሰላም ጥሪውስ እንዴት ከማን ጋርና በምን አግባብ ይሆን የሚከወነው?

፨ ዜጎችን በይፋ የሚጨፈጭፈውን ኦነግ ሸኔን በተመለከተ አቋም አልያዝንም ብለሃል፡፡ ይህም ያሳስብል፡፡ እንዴት ለህወሓት የተዘረጋ የድርድር ጥያቄ ነፍጥ ላነገበ ሌላ ቡድን አይሆንም ይባላል ?

በስተመጨረሻ ግን በትይዩ ካቢኔው ላይ የተናገከውን ላጸናልህ ፈልጋለሁ፤ አንተ ቡድንህን አዋቅረሃል፣ እኔም የዓመት ዕቅድህንና የመጀመሪያውን የመንግስት ትችት በማዘጋጀት ሒደት ያሳየኸውን ትጋት አደንቃለሁ፡፡

Henok Mesay Bella Tesfaye

Exit mobile version