Site icon ETHIO12.COM

ኢትዮጵያ በሚቀጥለው ዓመት የስንዴ ምርትን ከራሷ አልፎ ለውጭ ገበያ ማቅረብ ትችላለች”

ኢትዮጵያ በሚቀጥለው ዓመት አንድ ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ በመስኖ ስንዴ በማልማት ከራሷ ፍጆታ አልፎ ለውጭ ገበያ ማቅረብ እንደምትችል የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ገለጸ፡፡

ኢትዮጵያ ከዘጠኝ ዓመት በፊት እንደ አውሮፓውያን የዘመን ቀመር በ2012/13 የቆላ መስኖ ስንዴ ማልማት የጀመረችው በአንድ ሄክታር መሬት ላይ እንደነበር ይታወሳል፡፡

የቆላና የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በአፋር፣ኦሮሚያ፣ሶማሌና በሌሎች ክልሎች ተስፋፍቶ ባለፈው የ2013/14 የምርት ዘመን በ404 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ አንድ ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ቶን ስንዴ ምርት አግኝታለች፡፡

ለብዙ የኢትዮጵያውያን አርሶና አርብቶ አደሮች እንግዳ፤ ለቆላማ አካባቢዎች ባዳ የነበረው የቆላ ስንዴ ምርት ዛሬ ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ አምራቾች እየተሳተፉበት ይገኛል፡፡

በአፋር ክልል አፋምቦ ወረዳ እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል ጀጁ ወረዳ በበጋ መስኖ የቆላ ስንዴ ምርት ላይ የተሰማሩ አርሶና አርብቶ አደሮች “ስንዴ በእርዳታ ሲሰጠን እንጂ ተዘርቶ የሚበቅል ሰብል መሆኑን አናውቅም ነበር” ይላሉ፡፡ የቆላ መስኖ ስንዴ በአካባቢያችን ስናይ ለከብቶቻችን የሚሆን ሳር እንጂ ፍሬ የሚሰጥ ምርት አይመስለንም ነበር ሲሉም ገልጸዋል፡፡

አሁን ላይ በግብርና ምርምር ማዕከላት የግብዓት አቅርቦትና የግብርና ባለሙያዎች ድጋፍ አይተን የማናውቀውን ስንዴ በማልማት የልጆቻችንን ዳቦ በቤታቸን ማዘጋጀት ችለናል ብለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ከውጭ የሚመጣ ስንዴ ከተጠቃሚዎች እጅ ለመግባት እስከ 180 ቀናት የሚዘገይ ሲሆን በአካባቢያቸው የሚመረተው የቆላ መስኖ ስንዴ በሶስት ወራት ብቻ ለምግብ ፍጆታ ይደርስላቸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዓመታዊ የስንዴ ፍላጎት በየዓመቱ እየጨመረ መጥቶ በዚህ ወቅት ከ65 ሚሊዬን ኩንታል በላይ ደርሷል፤ ከዚህ ውስጥ በሀገር ውስጥ ምርት የሚሸፈነው 70 በመቶ ገደማ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ኢትዮጵያ በሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ችግሮች ውስጥም ሆና ራሷን የሚያስችላትን ስንዴ በማምረት ለአፍሪካ አገራት ሞዴል መሆኗን መናገራቸው ይታወሳል፡፡

እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ ኢትዮጵያ 30 በመቶ የሚሆነውን የስንዴ ፍጆታዋን ለማሟላት ከዩክሬንና ሌሎች አገራት ስንዴ ታስገባ ነበር፡፡ በዘንድሮ ዓመት ግን ምንም አይነት ስንዴ ከውጭ አለማስገባቷን ነው የገለጹት፡፡

“በብልጽግና ፓርቲ የመጀመሪያ ጉባኤ እስከ ቀጣዩ ጉባኤ ድረስ በስንዴ ምርት ራሳችን ችለን ለውጭ ገበያ እናቀርባለን ብለን ካስቀመጥነው የጊዜ ገደብ ከሁለት ዓመት በፊት ወደ ዓለም ገበያ መቀላቀል የምንችልበት የግብርና ምርት ማሻሻያ ሪፎርም ተሰርቷል” ነው ያሉት፡፡

በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የመስኖ ስንዴ ፕሮጀክት አስተባባሪ ዶክተር ዳንኤል ሙለታ፤ በኢትዮጵያ ከሶስት ዓመት በፊት የተጀመረው የመስኖ ስንዴ ልማት ተጨባጭ ውጤት ማስገኘቱን ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ በሶስት ሺህ 500 ሄክታር ላይ የተጀመረው የመስኖ ስንዴ ልማት በአሁኑ ወቅት በጥራትና በመጠንም አድጎ 404 ሺህ ሄክታር መሬት ደርሷል ብለዋል፡፡

“በሚቀጥለው ዓመት በአንድ ሚሊዬን ሄክታር መሬት ላይ የመስኖ ስንዴ ብናለማና አሁን ባለው ምርታማነት በሄክታር 40 ኩንታል ምርት ብንሰበስብ 40 ሚሊዬን ኩንታል ስንዴ እናገኛለን” ብለዋል፡፡

ይሄ ደግሞ ከክረምት የስንዴ ምርት ጋር ሲደመር ከአገሪቱ ፍጆታ የሚተርፍ ከ10 ሚሊዬን ኩንታል በላይ ስንዴ ለውጭ ገበያ ማቅረብ እንችላለን ነው ያሉት፡፡

የአርሶ አደሩና ባለሃብቶች ተሳትፎ መጨመር፤ የመንግስት ቁርጠኝነትና የግብርና ግብዓት አቅርቦት በተቻለ መጠን መቅረብ የመስኖ ልማት መርሃ ግብሩ ተስፋ ሰጭ አድርጎታል ብለዋል ዶክተር ዳንኤል፡፡

በአምራቹ የማልማት ፍላጎት ልክ ባይሆንም የተሻሻለ የምርጥ ዘር በመንግስት፣ በባለሃብቶችና በተለያዩ ማህበራት እየለማ እየተከፋፈለ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ዘመናዊ የእርሻ መሳሪያዎች፣የምርት መሰብሰቢያና ጸረ አረም መድሃኒቶች ለአምራቹ ማህበረሰብ በወቅቱ እንዲቀርቡ የሚደረገው ጥረት ተጨባጭ ለውጥ አምጥቷልም ብለዋል ዶክተር ዳንኤል፡፡

የአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት ዶክተር አኪንውሚ አደሲና በቡድን ሰባት አባል ሀገራት የልማት ሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር አፍሪካ በሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ሳቢያ ከ30 ሚሊዬን ሜትሪክ ቶን በላይ የምግብ ፍጆታ እጥረት ገጥሟታል ብለዋል፡፡

ይሁን እንጂ ከ30 በመቶ በላይ የስንዴ ፍጆታዋን ከውጭ የምታስገባው ኢትዮጵያ እንደ አውሮፓውያን የዘመን ቀመር በ2022 ምንም አይነት ስንዴ ወደ አገር ውስጥ ገቢ አላደረገችም ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ እንደ አውሮፓውያን የዘመን ቀመር በ2018 በስንዴ ልማት የተሸፈነው መሬት 50 ሺህ ሄክታር መሬት እንደነበር አስታውሰው በ2022 ወደ 400 ሺህ ሄክታር ከፍ ማለቱን ጠቁመዋል፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት በሰጣቸው ወቅትም፤ “ኢትዮጵያ በሚቀጥለው ዓመት ሁለት ሚሊዬን ሄክታር መሬት ላይ ስንዴ በማልማት ወደ ኬንያና ጅቡት ስንዴ ለዓለም ገበያ ማቅረብ ትችላል፤ ሌሎች አገራት ከዚህ ብዙ ይማራሉ” ሲሉ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡

የአሜሪካ መንግስትም የኢትዮጵያ የስንዴ ልማት ምርታማነት እየጨመረ መምጣቱን ገልጾ ፤ በ2022/23 እስከ አምስት ነጥብ ሰባት ሚሊዬን ቶን ማምረት እንደምትችልም ግምቱን አስቀምጧል ሲል ኢዜአ ዘግቧል፡፡

Exit mobile version