Site icon ETHIO12.COM

አልሸባብ በድህረ-ፎርማጆ ሶማሊያ

ፀሀፊው በኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የዓለም-አቀፍ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ ጉዳዮች ተመራማሪ ሲሆኑ ፅሁፉ የተጠቀሰው ሀሳብ ሙሉ በሙሉ የፀሀፊው እንጂ የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩትን ሆነ ሌላ የትኛውንም ተቋም ሆነ ግለሰብ አይወክልም።

1. መግቢያ

አልሸባብ እ.እ.አ በ2011 በአፍሪካ ህብረት ጥምር ጦር ከሞቃዲሾ የተባረረ ቢሆንም አሁንም ሰፊ ግዛት በተለይም በማዕከላዊ እና በደቡባዊ ሶማሊያ ይቆጣጠራል። ቡድኑ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አጥፍቶ-መጥፋት፤ ድንገተኛ ደፈጣ የመሳሰሉ ዘዴዎችን በመጠቀም የሚያደርሳቸው የሽብር ጥቃቶች እየጨመሩ ይገኛሉ። የእነዚህ ጥቃቶች ዋነኛ ኢላማዎች የሶማሊያ ፌደራል መንግሥትና የራስ ገዝ ክልሎች ባለስልጣናት እንዲሁም በአገሪቱ የተሰማሩ የውጭ አገራት ወታደሮች ናቸው።

ለምሳሌ እ.እ.አ ግንቦት 4 ቀን 2022 በአፍሪካ ህብረት ሰላም አስከባሪ ጦር ካምፕ ላይ ቡድኑ ባደረሰው ጥቃት ቢያንስ 10 የቡሩንዲ ወታደሮች የተገደሉ ሲሆን 25 ደግሞ ቆስለዋል። በአልሸባብ የሽብር ጥቃቶች የብዙ ሰው ሕይወት ከመቀጠፉ በተጨማሪ በአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት፤ ሰብአዊ ሁኔታ ብሎም ኢኮኖሚ ላይ ቡድኑ የሚያደርሰው ተጽኖ እንደቀጠለ ነው። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (የተ.መ.ድ) መረጃዎች እንደሚያሳዩት አልሸባብ በወር እስከ 10 ሚሊዮን ዶላር ገቢ የሚሰበስብ ሲሆን በአሁን ጊዜ ከ12 ሺ በላይ ተዋጊዎችን በመያዝ ትልቁ፤ ሀብታሙ እና አደገኛው የአልቃይዳ ተጣማሪ ለመባል በቅቷል።

ሶማሊያ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆና እ.እ.አ ግንቦት 15 ቀን 2022 በተደረገው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ መሀመድ አብዱላሂ መሀመድ (ፎርማጆ) በሀሴን ሼክ መሀመድ ተተክተዋል። አልሸባብን መዋጋት ከአዲሱ ፕሬዚዳንት ዋነኛ ፈተናዎች አንዱ ሲሆን የቡድኑ ተጽኖ ከአገሪቱ አልፎ በአፍሪካ ቀንድ እና ባሻገር ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚችል ተንታኞች ይገልጻሉ። ለመሆኑ ከአልሸባብ አሁናዊ ሁኔታ ጋር በተያያዘ ያሉ ዋና ዋና ስጋቶች ምንድናቸው? የቡድኑ በአንጻራዊነት ዳግም መጠናከር ምን ተስፋና ዕድል ይዞ ይመጣል?

2. ስጋቶች

የተለያዩ አካላት በሶማሊያ ያለውን የአክራሪዎች እንቅስቃሴ ለማምከን ጥረቶችን አድርገዋል፣ እያደረጉም ነው። ይሁንና አሁንም እንደ አልሸባብ ያሉ ቡድኖች በአገሪቱ በስፋት የሚንቀሳቀሱ ሲሆን ይህም ለሶማሊያ፤ ለጎረቤት አገራት ብሎም ለአለም-አቀፉ ማህበረሰብ ዘርፈ-ብዙ ስጋቶችን ያስከትላል። አንደኛ ቡድኑ አሁንም አቅም አለው በሚል ቀላል የማይባል የሶማሊያ ዜጋ (በተለይም ወጣቱ) ሆነ ከሌሎች አገራት ጂሀድስቶች ቡድኑን ለመቀላቀል ሳቢ ምክንያት ሊሆናቸው ይችላል። ይህም አዲሱ የፕሬዚዳንት ሀሴን ሼክ መሀመድ መንግሥት በጦርነት የደቀቀችውን ሶማሊያ የማረጋጋት ስራዎች ፈታኝ የሚያደርገው ይሆናል።

ሁለተኛ በቀጠናው አገራት ላይ የደህንነት፤ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተጽኖዎችን ያሳድራል። በተለይም ቡድኑ ለዓመታት በቀጥታና በተዘዋዋሪ የተለያዩ ህገ-ወጥ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችን ለጦር መሳሪያ ግዥ፤ ለተዋጊዎች ክፍያና ለሌሎች ሽብር ተግባራት የገቢ ምንጭ አድርጎ በስፋት ሲጠቀም የነበረ ሲሆን በሚቆጣጠራቸው አካባቢዎች አሁንም አጠናክሮ ቀጥሏል።

የቡድኑ ኢኮኖሚያዊ ብሎም ወታደራዊና ፖለቲካዊ ተጽኖ እየሰፋ ሲሄድ መሰል ህገ-ወጥ ተግባራት ሊስፋፉና የሶማሊያን እና የቀጠናውን መረጋጋት ሊያናጉ ይችላሉ። በተለይም በምስራቅ እና ደቡብ ምስራቅ የአገራችን አካባቢዎች እና በሰሜን ኬንያ የፀጥታ ስጋት (ለምሳሌ ህገ-ውጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር፤ የሽብር ጥቃት) እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖዎች (ለምሳሌ የኮንትሮባንድ ንግድ፤ በፀጥታ ስጋት የተለያዩ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች መቀነስ) እንዲስፋፋ ሊያደርግ ይችላል።

ሶስተኛ ለሶማሊያ ሰላምና መረጋጋት የተለያየ አስተዋጾ በሚያደርጉ አካላት ዘንድ ተስፋ መቁረጥና ድጋፎቻቸውን መቀነስ ሊያስከትል ይችላል። ለምሳሌ በያዝነው 2022 ለሶማሊያ ከሚያስፈልገው 1.5 ቢሊዮን ዶላር ውስጥ እስከ አሁን ከለጋሾች የተገኘው ከ30 በመቶ በታች መሆኑን የተ.መ.ድ ሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ አሳውቋል። በተያያዘ በአገሪቱ ያለውን የአፍሪካ ህብረት ጦር ቆይታን በተመለከተ እ.እ.አ ከ2021 አጋማሽ ጀምሮ ለብዙ ወራት በተለያዩ አገራትና ተቋማት መካከል አለመግባባቶችና ክርክሮች ነበሩ።

በተለይም የዓለም ፖለቲካዊ-ኢኮኖሚያዊ ትኩረት በአሁን ወቅት ከዩኩሬን-ራሽያ ጦርነት ጋር እጅግ መያያዙ እና ለዓመታት ብዙ የገንዘብና ሌሎች ድጋፎች ቢደረጉም ሶማሊያ ውስጥ ከተወሰነ መሻሻል ውጪ የአክራሪዎችን ተጽኖ ሊቋቋሙ የሚችሉ ጠንካሪ የፀጥታ ተቋማትን መገንባት አለመቻሉ ተጠቃሽ ምክንያቶች ሊሆኑ ይችላሉ። በዚህም አገራትና ተቋማት ለሶማሊያ ሰላምና መረጋጋት ስራዎች ቀጥታ ገንዘብና ሌሎች ድጋፎች ከመስጠት ድሮንን መጠቀም ወደ መሳሰሉ ዘላቂ ውጤት የማያመጡ ስትራቴጂዎች ላይ ትኩረት ሊያደርጉ ይችላሉ።

በተያያዘ የአልሸባብ ጥቃት እየተጠናከረ መምጣት ወታደሮቻቸውን ወደ ሶማሊያ የላኩ አንዳንድ አገራት የጦራቸውን ቁጥርና የስምሪት ሽፋን እንዲቀንሱ ወይም በሙሉ እንዲያስወጡ ሊገፋፋቸው ይችላል። ይህም ለአገራችን ትልቅ የብሔራዊ ደህንነት ስጋት ምንጭ ሊሆን የሚችል ሲሆን በአገራችን ላይ ቀላል የማይባል ወታደራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጽኖ ይኖረዋል።

ሌላው ሊጠቀስ የሚችለው ስጋት አሁን ካለው የአገራችን ውስጣዊ ሁኔታ አንጻር አንዳንድ አገራት አልሸባብን ተልዕኮ ፈጻሚ አድርጎ ሊጠቀሙብን የሚችሉ መሆኑ ነው። በተለይም የህዳሴው ግድብ ድርድር የሚፈለገውን ያህል ውጤት ያላመጣ መሆኑ እንዲሁም በአገራችን ብሔራዊ ውይይት ለማካሄድ ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆኑና በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረውን ጦርነት በድርድር ለመቋጨት ጥረቶች መጀመራቸው ያላስደሰታቸው አካላት በፌደራሉ መንግሥታችን ላይ ተጽኖ ለማሳደር በሶማሊያ ያለውን የአክራሪዎች ሁኔታ በተለያየ አኳኋን እንደ ምቹ አጋጣሚ ሊጠቀሙ ይችላሉ።

3. ተስፋዎችና ዕድሎች

ከላይ በዝርዝር የተጠቀሱ ዋና ዋና ስጋቶች እንዳሉ ሆነው በሶማሊያ ካለው የአክራሪዎች በተለይም ከአልሸባብ እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ ተስፋዎችና ዕድሎችም አሉ። አንደኛ ሁኔታው በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ቀጠናዊ ትብብር እንዲጠናከር በር ሊከፍት ይችላል። አልሸባብ ለኢትዮጵያ፤ ለኬንያ፤ ለጂቡቲ ብሎም ለዩጋንዳ ቀጥተኛ የብሔራዊ ደህንነት ስጋት ነው። እነዚህ አገራት ቁጥሩ፤ ዓይነቱና መጠኑ ይለያይ እንጂ በቡድኑ የጥፋት በትር አርፎባቸዋል። ስለዚህ በአሁን ወቅት የአልሸባብ በአንጻራዊነት ዳግም መጠናከር እነዚህ አገራት ቡድኑ የሚጋርጠውን አደጋ ለመመከት እንዲተባበሩ የማነሳሳት ዕድሉ ከፍተኛ ነው።

በዚህ ረገድ ሊጠቀስ የሚችለው ሁነት እ.እ.አ ሰኔ 9 ቀን 2022 በሞቃዲሾ በተካሄደው የፕሬዚዳንት ሀሴን ሼክ መሀመድ በዓለ ሲመት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ የቀጠናው አገራት መሪዎች በአንድ ላይ መገኘታቸው ነው። ደህንነትን ማዕከል አድርጎ ሊፈጠር ወይም ሊጠናከር ስለሚችለው ቀጠናዊ ትብብር ፍንጭ ደግሞ አዲሱ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት በበዓለ ሲመት ንግግራቸው ሰጥተዋል። ተመራጩ ፕሬዚዳንት ሞቃዲሾን ከአሸባሪዎች መጠበቅ ከመጀመሪያዎቹ የፕሬዚዳንትነት ስራዎች አንዱ መሆኑን ጠቅሰው ለዚህም ስኬታቸው የሌሎችን ድጋፍና ትብብር እንደሚጠይቁ ብሎም ፍላጎት ካላቸው ሁሉ ጋር አብሮ መሥራት እንደሚፈልጉ ገልጸዋል።

ሁለተኛ የአልሸባብ ወቅታዊ ሁኔታ በኢትዮጵያ እና በምዕራብ አገራት (በተለይም ከአሜሪካ ጋር) የተጀመረው ዲፕሎማሲያዊ መልሶ-ቅርርብ እንዲጠናከር የራሱን አስተዋጾ ሊያደርግ ይችላል። ለብዙ ዓመታት በሶማሊያ አክራሪነትንና የሽብር ቡድኖችን መዋጋት በኢትዮጵያ እና በአሜሪካ መካከል ከነበሩት ዋነኛ የትብብር መስኮች አንዱ ነበረ። ይሁንና በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ግንኙነት ባለፉት ጥቂት ዓመታት ተቀዛቅዞ የነበረ ሲሆን በአሁን ወቅት የመልሶ-ቅርርብ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑ ይታወቃል።

ኢትዮጵያ በሶማሊያ ካላት ተጠቃሽ የፀረ-ሽብርና ሰላም ማስከበር ስራዎች አንጻር በሶማሊያ ሆነ በአጠቃላይ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ለሚደረጉ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴዎች ሚናዋ የጎላ መሆኑ በምዕራባዊያን ዘንድ ይታወቃል። ይህም ማለት የአልሸባብ ዳግም መጠናከር አሜሪካ ቡድኑ ላይ እርምጃዎችን ለመውሰድ እንድትንቀሳቀስ ስለሚያደርጋት ኢትዮጵያ እና አሜሪካ በዚህ ረገድ ተባብረው ወደ መስራት የሚመጡበት አግባብ የመፍጠር ዕድሉ ከፍተኛ ነው። ከዚህ ጋር በተያያዘ እ.እ.አ ከታህሳስ 2020 በኋላ አሜሪካ በሶማሊያ እግረኛ ወታደሮቿን ዳግም ለማስፈር እ.እ.አ ግንቦት 2022 ላይ መወሰኗ አገሪቱ ከሀሰን ሼክ መሀመድ መንግሥት ጋር በፀጥታ ዙሪያ በተሻለ ሁኔታ ተባብረው መስራት ይቻላል የሚል ዕምነት እንዳላት ማሳያ ነው።

ሶስተኛ የአፍሪካ ቀንድ ካለው ጂኦ-ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታና በአካባቢው እየተስተዋለ ካለው የብዙ አገራት ፉክክር አንጻር የአልሸባብ በአንጻራዊነት ዳግም መጠናከር ለሶማሊያ ብሎም ለቀጠናው የሚሰጠው የለጋሽ አገራት እና አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ተቋማት ትኩረት እንዲጨምር ሊያደርግ ይችላል። ለምሳሌ መላው የድርጅቱ ተቋማት ከአዲሱ የሶማሊያ መንግሥት ጋር በጋራ ግቦች ዙሪያ አብሮ ለመስራት በጣም ዝግጁ መሆናቸውን የተ.መ.ድ ዋና ፀሃፊ ልዩ ተወካይና የሶማሊያ ተልዕኮ ኃላፊ እ.እ.አ ግንቦት 23 ቀን 2022 ለፀጥታው ምክር ቤት ባቀረቡት ሪፖርት ገልጸዋል።

በተጨማሪም አለም ባንክ እና የአለም የገንዘብ ድርጅት ለአዲሱ የሶማሊያ መንግሥት ድጋፎችን አጠናክሮ የመቀጠል እንቅስቃሴዎችን ማሳየታቸው ሌላው ሊጠቀስ የሚችል ሁነት ነው። እነዚህ ሁነቶች በሶማሊያ ካለው የፀጥታና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ጋር በተያያዘ ያለውን ሰብአዊ ቀውስ ለመከላከል ከመርዳቱም በላይ የፀጥታ እና ሌሎች መንግሥታዊ ተቋማትን የመገንባት ስራዎችን የሚያጠናክር ይሆናል።

4. ማጠቃለያ

በሶማሊያ እየተስተዋለ ያለው የአልሸባብ ዳግም የማንሰራራት አዝማሚያ ለአገሪቱ፤ ለኢትዮጵያ ሆነ ለቀጠናው ስጋቶችንና ዕድሎችን ይዟል። አገራችን ከብሔራዊ ጥቅሟ አንጻር ስጋቶችን ቢያንስ ለመቀነስ እና ተስፋዎችንና ዕድሎችን ለማስፋትና ለመጠቀም ዘርፈ-ብዙ ስራዎችን መስራት ይጠበቅባታል። በተለይም የድንበር አካባቢ ቁጥጥሮችን ጨምሮ የአገር ውስጥ የሰላምና ደህንነት ስራዎችን ማጠናከር፤ ከጎረቤቶቻችን በተለይም ከሱዳን እና ከኤርትርያ ጋር ያለንን ግንኙነት ማጠናከር፤ ከኬንያ፣ ዩጋንዳ፣ ቡሩንዲ እንዲሁም አሜሪካ ጋር ተቀራርቦ መስራትና ቡድኑን በጋራ መዋጋት አማራጭ የሌለው መፍትሄ መሆኑን በተጠናከረና ተከታታይነት ባለው መልኩ ማስገንዘብ፤ የተለያዩ ተቋማት ከሶማሊያ ላይ ትኩረታቸውን እንዳያነሱ ወይም እንዳይቀንሱ ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊና ፖለቲካዊ ስራዎችን አጠናክሮ መስራት ያስፈልጋል።

 በፍቃዱ ቦጋለ

አዲስ ዘመን ሐምሌ 25/2014

Exit mobile version