Site icon ETHIO12.COM

“መብራት የሌለው የኢንዱስትሪ ፓርክ” ሲገነባ ተጠያቂው ማነው?

የፓርኩ የኀይል አቅርቦት ችግርስ የሚፈታው መቼ ነው?

በመንግሥት ተቋማት “አይን ያወጣ መገፋፋት” አቅሙን ያጣው የቡሬ የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክ፣ በገጠመው የኀይል እጥረት በፓርኩ ወደ ሥራ ለገቡት ፋብሪካዎች ለማምረት ችግር፣ ለሚገቡትም ስጋት ኾኗል።

በፌዴራል ደረጃ ሞዴል ተብለው ከተመረጡት አራት የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪያል ፓርኮች መካከል አንዱ የኾነው ቡሬ የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ግንባታው የተጀመረው በ2010 ዓ.ም ነበር፡፡ በዚህ ዘገባ የፓርኩ የመቋቋም ዓላማና አሁናዊ ቁመናውን የምንዳስስበት ነው። ይህን ፓርክ ኀይል አልባ ሊያደርገው የቻለው ችግር ምንድን ነው? አራት ዓመታትን ያዘገመው ፓርኩ “መብራት የሌለው የኢንዱስትሪ ፓርክ” ለምን ለመባል በቃ?

የአካባቢው ነዋሪዎች ስለ ፓርኩ እንደሚሉት መንግሥት በዚህ ኢንዱስትሪ ፓርክ የኀይል አቅርቦት ላይ ያለበት ችግር የአቅም ማጣት አይመስለንም፣ የፍላጎት አለመኖር እንጂ። አማላይ የልማት እቅድ ያለው ኢንዱስትሪ ፓርክ ከጎናችን ገንብቶ እቅዱን እንዳያሳካ -ማነቆ መኾን ተገቢ አይደለም ይላሉ የአካባቢው ነዋሪዎች።

ኢንዱስትሪ ፓርኩ በተቋማት መገፋፋት ” አቅሙን አጥቷል። ይህ ግዙፍ ኢንዱስትሪ ፓርክ የራሱ ሰብስቴሽን የለውም፣ ኃይል የሚያገኘው ከከተማው ነው። ፓርኩ ከ46 እስከ 50 ሜጋ ዋት ያስፈልገዋል የሚል ጥናት ቢጠናም አሁንም መፍትሄ አላገኘም።

የፓርኩ ሥራ አስኪያጅ ዳኛቸው አስረስ እንደሚሉት ኢንዱስትሪ ፓርኩ በኤሌክትሪክ ኀይል አቅርቦት ችግር አቅም አልባ ኾኗል። ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኩ 22 ባለሃብቶች ገብተዋል፡፡ ከገቡት መካከልም አንዱ ሪችላንድ ካምፓኒ ማምረት ቢጅምርም ማግኘት ከነበረበት 12 ሜጋ ዋት 3 ሜጋ ዋት ብቻ ነው ማግኘት የቻለው። አሁን ግንባታ ላይ ያሉት ፓርኩ ውስጥ የገቡ ፋብሪካዎችን የማምረት ሥራ የሚያስጀምር የኀይል አቅም የለም ብለዋል። የኃይል አለመኖር ደግሞ ቀጣይም ሌሎች ባለሃብቶች ወደ ፓርኩ እንዳይገቡ ስጋት ፈጥሯል ነው ያሉት አቶ ዳኛቸው።

እናም ይላሉ አቶ ዳኛቸው የዚህ ኢንዱስትሪ ፓርክ ጉዳይ ጠንከር ያሉ ንግግሮች ያስፈልጉታል፡፡ ጉዳዩ ከመልማት ጥያቄ በላይ የመልካም አስተዳደር ችግር ምንጭ መኾኑ አይቀርምና አፋጣኝ መፍትሔ ያሻዋል። “ጉዳዩ የፖለቲካል ውሳኔዎችንም የሚፈልግ ይመስላል” ባይናቸው አቶ ዳኛቸው።

23 ሄክታር መሬት ቦታ ተረክቦ ሥራ የጀመረው ሪች ላንድ ባዮ ኬሚካል ኀላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ በ900 ሚሊየን ብር ነው ወደ ሥራ የገባው፡፡ በሙሉ አቅሙ መሥራት ሲጀምርም 66 ሚሊየን ዶላር ዓመታዊ ገቢ እንደሚያስገኝ ይጠበቃል፡፡ ሪች ላንድ በዓመት 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ኩንታል አኩሪ አተርን ይጠቀማል ተብሏል። በቀን 5ሺህ ኩንታል አኩሪ አተርን በግብዓትነት ይጠቀማል ነው የተባለው። ከዚህም ደረጃውን የጠበቀ ያለቀለት የምግብ ዘይት ያመርታል። በአጠቃላይ ሪች ላንድ ካምፓኒ በወሰደው 23 ሄክታር መሬት ላይ ወደ 8 አይነት ምርቶች ፋብሪካዎችን ከፍቶ ይሠራል፣ ያመርታል።

የኢንዱስትሪ ፓርኩ ስራ አስኪያጅ አቶ ዳኛቸው አስረስ እንደሚሉት ሪች ላንድ ከሁለት የግብርና ጥሬ እቃዎች ከአኩሪ አተርና ከቦቆሎ ምርቶች የዘይትን ሽያጭ ሳይጨምር በሌሎቹ ምርቶች ባለፉት አምስት ወራት ብቻ 8 ነጥብ 1 ሚሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሬ (465 ሚሊየን ብር ገቢ) ማግኘት ችሏል። (በጠቅላላው 21 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማስገኘቱ ተነግሯል፣ ይህንም በ20 ከመቶ በኾነ የማምረት አቅሙ ብቻ ነው ገቢውን ያስገኘው)፡፡ በሚቀጥለው የበጀት ዓመት ኀይል ካገኘ በዓመት እስከ 2 ነጥብ 5 ሚሊየን ኩንታል ቦቆሎ የመጠቀም እቅድ ይዞ እየሠራ ነው።

ከዚሁ ፓርክ ኀይል የሚጠቀመው ፊቬላ የዘይት ፋብሪካም ቢኾን ማግኘት ከነበረበት 12 ሜጋ ዋት 3 ሜጋ ዋት ብቻ ነው እየተጠቀመና ከአቅም በታች እያመረተ ያለው። አሁም “የቡሬ የኀይል አቅርቦት ችግር የተቋማት ከልማት ንግግር ባለፈ ፖለቲካዊ ንግግሮች የሚያስፈልጉት ይመስላል” የሚለውን የአቶ ዳኛቸውን ሃሳብ ይዘን ተቋማት በጉዳዩ ላይ ምን እያደረጉ ነው ምንስ ይላሉ የሚለውን እንፈትሽ።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኀይል በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 302/ 2006 ዓ.ም በአዋጅ በአዲስ ከተደራጀ በኃላ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኀይል የኀይል ማመንጫዎችን፣ ማስተላለፊያዎችን እና ማከፋፈያዎችን የመገንባትና የማሻሻያ ሥራዎችን እንዲሁም የኦፕሬሽንና ጥገና ሥራዎችን የማከናወን፤ የንድፍና የቅየሳ ሥራዎችን፣ የኤሌክትሪክ ኀይል ጅምላ ሽያጭና፣ የአጫርቶ ማሠራትንና መሰል ተግባራትን እንዲያከናውን ስልጣን ተሰጥቶታል።

አቶ አያልነህ አበዋ በኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ደጋፊ ፕሮጀክት ፕሮግራም ኮርዲኔተር ለአሚኮ እንዳሉት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኀይል በሚመለከታቸው አካላት ተደጋጋሚ ንግግሮች ተደርገው ተበድሮ እንዲያስገነባ ቢጠየቅም “ብድር ስለበዛብኝ በስሜ አልበደርም ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በራሱ ይበደር” የሚል ምላሽ ሰጠ ይሉናል።

የዚህ ኢንዱስትሪ ፓርክ ጉዳይ ለ’ስትሪንግ’ ኮሚቴው ቀረበ። ይህ ኮሚቴ ጠቅላላ የሀገሪቱን ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ጉዳይ የሚመለከት የጠቅላይ ሚኒስተሩ ከፍተኛ የኢኮኖሚ አማካሪ ሰብሳቢ የኾነበትና የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ገንዘብ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኀይልን ጨምሮ 13 አካላት የተካተቱበት ብሔራዊ ኮሚቴ ነው። በዚህ ኮሚቴ ውሳኔ ገንዘብ ሚኒስቴር ለኤሌክትሪካ ኀይል የክፍያ ጋራንቲ ሰጠ። ኤሌክትሪክ ኀይል አሁንም ሌላ ሃሳብ አቀረበ ገንዘቡ በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በኩል አካውንት ተከፍቶ ይንቀሳቀስ አለ። በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ተከፍቶ ከገንዘብ ሚኒስቴር በተሰጠ ገንዘብ ለኤሌክትሪክ ኀይል የግንባታው 10 በመቶ ተሰልቶ ለሥራ ማስጀመሪያ 318 ሚሊየን 714 ሺህ ብር እንደተሰጠው አቶ አያልነህ ነግረውናል።

አቶ አያልነህ እንደሚሉት ጫራታው ወጥቶም ተቋራጮች ይፋ ተደረጉ። ሃይኖ ሃይድሮ፣ሲኖ ሃይድሮ (የቻይና ኩባንያዎች) እና ካልፓቱራ (የህንድኩባንያ) ጫራታውን ያሸነፉት ኩባንያዎች ናቸው።

የኤሌክትሪክ ኀይል ደግሞ ሌላ ጉዳይ ይዞ ብቅ አለ “ለዲዛይንና ለሲቪል እንጅነሪንግ ብቻ የሚውል ነው፣ (ፎሬን ከረንሲ ኮምፖነንት ስለሌለው) ተጨማሪ 6 ሚሊዮን ዶላር እፈልጋለሁ” አለ ይላሉ። በዚህም መፍትሔ አልተገኝም እንዲያውም ሌላ ጉዳይ መጣ፣ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ”ኤል ሲ” ከፍቶ ፎሬን ከረንሲ ለኢሌክትሪክ ኀይል ማቅረብ ከኀላፊነት ውጭ ነው ተባለ።

በተደረጉ ውይይቶች የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተጠየቀውን ማቅርብ እንደሚችል፣እንደ አስፈላጊነቱም የፎሬን ከረንሲ ተጨማሪ ከብሔራዊ ባንክ ፈቃድ መጠየቅ እንደሚችል እና ለኤሌክትሪክ ኀይል ገንዘብ ማበደር እንደሚችል አስታወቀ። አቶ አያልነህ በስተመጨረሻ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ፈቃዱን ሰጥቶ በውሳኔው ተስማምቶ ጉዳዩን በራሱ እንዲፈጽም ኃላፊነቱን ወስዷል።

ሰብስቴሽኑ ከተገነባ በኋላ የሚቆጣጠረው ድርጅት፣ ከአገልግሎቱም ገንዘብ ሰብስቦ የሚጠቀመው ድርጅት ከአሳለፍነው ሰኔ 2014 ዓ.ም ጀምሮ ኀላፊነቱን ወሰዶ ሥራ መጀመሩን አቶ አያልነህ ነግረውናል። ለተቋራጮችም የኀይል ግንባታውን ለማጠናቀቅ የ14 ወራት ውል ተሰጧቸዋል ነው የተባለው።

ከወደ ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የተገኘው መረጃ ግን ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ማብራሪያ የራቀ ነው። የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬት የኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ ሞገስ መኮነን እንደሚሉት በቡሬ ኢንዱስትሪ ፓርክ ጉዳይ መብራት ኀይል ከተቋቋመለት ዓላማ ውጭ እየተጠየቀ ነው። አቶ ሞገስ በሰጡን ማብራሪያ መብራት ኀይል ፋይናንስ ለሌለው ተቋም ፕሮጀክት አይገነባም። ኀይል የማቅረብና የመገንባት እንጂ ፋይናንሱን የመሸፈን ግዴታ የለበትም።

ኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ አቶ ሞገስ “በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኀይልና በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መካከል ለአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች የኀይል አቅርቦትን በተመለከተ የተደረገው ስምምነት፣ ለፕሮጀክቱ የሚያስፈልግን ምንዛሬ ሂደቱን በሙሉ የንግድ ሚኒስቴር ከብሔራዊ ባንክ ጋር ተነጋግሮ ይጨርሳል የሚል ነው” ብለዋል። የቡሬ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ባለቤቱ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ነውና የፋይናስ ወጭውን ይሸፍናል መብራት ኀይል፣ ኀይል ያቀርባል። የታወር ብረቶች፣ ለሰብስቴሽን የሚኾኑ የኤሌክትሮ ሜካኒካል እቃዎችን ለማስገባት ኤል ሲ ያስፈልጋል፣ ይሄ ደግሞ የባለቤቱ ኀላፊነት ነው ብለዋል።

አሁንም ሂደት ላይ ያሉ ንግግሮች በስምምነቱ መሰረት ነው እንጂ “መብራት ኀይል ኀላፊነቱን ወስዶ ሊገነባ ነው “የሚለው መረጃ ትክክል አይደለም ይላሉ አቶ ሞገስ። ኾኖም ግን ይላሉ አቶ ሞገስ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ኃላፊነቱን እስኪወጣ ድረስ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኀይል በኩል የሰብስቴሽን የሲቪል ሥራዎችንና የዲዛይን ሥራዎችን ጎን ለጎን ለማስኬድ እየተሠራ ነው።

ታዲያ የቡሬ ኢንዱስትሪ ፓርክ የኀይል ችግር እንዴት ይፈታ ለሚለው ቡሬ ላይ ለሰብስቴሽን ግንባታ ተብሎ 10 ሄክታር መሬት ተከልሎ፣ ቦታው ከሶስተኛ ወገን ነፃ ኾኖ ታጥሮ ከተቀመጠ ሦስት ዓመታትን ያለአገልግሎት ማሳለፉን ልብ ይሏል። ያም ተባለ ይህ በዚህ ሁሉ “የአድርግ-አላደርግም” ሂደት ዓመታት ነጎዱ። ቡሬ የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክም “ከእቅዱም -ከልኩም” በታች ኾኖ አራት ዓመታትን አዘገመ። ተጠያቂው ማን ነው?

እንደ ማሳያ-ሌሎች አቻ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ስንመለከት ቡሬ ኢንዱስትሪ ፓርክ ገና በመጀመሪያው ምዕራፍ ምርት የጀመሩት ሁለት ኩባንያዎቹ በኀይል እጥረት ምክንያት ከ20 በመቶ በታች አቅም እየሠሩ ነው። ግንባታ ላይ ያሉትን ደግሞ ማምረት ማስጀመር የሚያስችል አቅም የለም እየተባለ፣ በሌሎች አቻ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ይህ ችግር አለመኖሩ ሲነገር “እንዴት” የሚል ጥያቄ ብቻ በቂ አይኾንም።

በእርግጥ ሌሎቹ የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ለምን የኀይል ችግር አልገጠማቸውም ወይም እንዴት ችግራቸውን ፈቱ ለሚሉ ጥያቂዎች አቶ ሞገስ የሰጡን ምላሻ ያሉበት ከተማ “ትርፍ የኀይል አቅርቦት ስላለው ነው” የሚል ነው። አማራ ክልል ደግሞ ቀድሞውኑም ከኀይል አቅርቦት ችግሩ አልተላቀቀም። እናም ለቡሬ የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክ የሚኾን በቂ ኀይል የለውም። የክልሉ የኀይል እጥረት መፍትሔ እስካላገኘ ድረስ የተገነባውን የኢንዱስትሪ ፓርክ ከግቡ ለማድረስ አስቸጋሪ ይኾናል። እናም እንደተባለው “ፖለቲካዊ መፍትሔ ያስፈልግ” ይኾናል።
ከአሰራር ውጭ የሚመስሉ “አድርግ አታድርግ” ክርክሮች፣ ከሲስተም ያፈነገጡ የሚመስሉ ተቋማዊ ሳይኾን በተቋሙ መሪዎች ይሁንታ ብቻ በሚገኝ ፈቃድ የሚሳኩ ሥራዎች ልማትንም የተጠቃሚነት አስተሳሰብንም ይጎዳሉ። ለጉዳዩ ከ”ለምን ክርክር” ባሻገር ተጠያቂነትን የሚያመጣ ተቋማዊ አሠራር በልኩ መተግበር ግድ ይላል።

አሚኮ

Exit mobile version