Site icon ETHIO12.COM

ኤርትራዊያንን ጨምሮ የሌላ አገር ዜግነት ያላቸው ዶላር አጣቢዎችና አጭበርባሪዎች ተያዙ

ፍቃድ ሳይኖራቸው የውጭ ሀገር ገንዘብ በመመንዘር የሀዋላ ስራ ሲሰሩ ነበር ተብለው በቁጥጥር ስር የዋሉ 70 የኤርትራ ዜግነት ያላቸው ተጠርጣሪዎች ፍርድ ቤት ቀረቡ።

በተመሳሳይ ወንጀል የተጠረጠሩ ሌሎች ሁለት ግለሰቦች ደግም የኢትዮጲያ ዜግነት እንዳላቸው ለፍርድ ቤት አስመዝግበዋል።

ተጠርጣሪዎቹ ዛሬ ረፋድ ላይ በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት ቀርበው ጉዳያቸው ታይቷል።

በሀዋላ ስራ ላይ ተሰማርቶ እንደሚሰራ ለፍርድ ቤቱ አምኖ የገለጸው ኤርሞን ሳሀለ : የማነ ገ/ሚካኤል : አማንኤል ረዘነ :መንግስቱ ወልደ ገሪማን ጨምሮ ባጠቃላይ 72 ተጠርጣሪዎች ሲሆኑ ከነዚህ ውስጥ አስሩ ሴቶች ናቸው።

ተጠርጣሪዎቹ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከ :በለሚ ኩራ እና በኮልፌ ክ/ከ በተለያዩ ወረዳዎች ኗሪ መሆናቸውን ለፍርድ ቤቱ አስመዝግበዋል።

ተጠርጣሪዎችን ፍርድ ቤት ያቀረቡት የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አራት መርማሪዎች የጥርጣሬ መነሻ ምክንያታቸውን በጥምረት አቅርበዋል።

በዚህም ከደህንነት ተቋም እና ከኢንሳ ጋር በመተባባበር በተካሄደ የኦፕሬሽን ስራ በከተማዋ በተለያዩ አካባቢዎች በህገወጥ መንገድ የተለያዩ ውጭ ሀገር እና የኢትዮጲያ ገንዘብ ሲያዘዋውሩ መያዛቸውን ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል።

ሲዘዋወር ነበረ ከተባለ የገንዘብ መጠን ውስጥ 27 ሺህ 491 የአሜሪካን ዶላር፣ 15 ሺህ 325 ዩሮ፣ 680 ፓውንድ፣ 6 ሺህ 689 የኤርትራ ናቅፋ፣ 5 ሺህ 200 የሲውዝ ፍራንክ፣ 500 የአንጎላ ክዋንዛ፣ 1 ሺህ 680 የኳታር ሪያል፣ 1 ሺህ የኖርዌይ ክሮን እና 49 ሺህ 735 የኢትዮጵያ ብር እና የተለያዩ የባንክ ደብተሮች መያዙን ለፍርድ ቤቱ አብራርተዋል።

በሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬ እጥረት እንዲከሰት ለማድረግ ከብሔራዊ ባንክ ፍቃድ ሳይኖራቸው የውጭ ገንዘብ የመመንዘር ስራ ሲሰሩ ነበር ሲሉ መርማሪዎቹ በየተራ ለፍርድ ቤቱ ገልጸዋል።

የተጠርጣሪዎችን ቃል ለመቀበል: አሻራ እና ፎቶ ለማስነሳትና ተጨማሪ ማስረጃ ለመሰብሰብ የ14 ቀን ጊዜ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።

ቢኒያም ሰመረ የተባለ ተጠርጣሪ በበኩሉ በመኖሪያ ቤቴ የተገኘው 900 ዶላር ከቤተሰቡ በስጦታ በየጊዜው የላከለት ገንዘብ መሆኑን አብራርቷል።

ኤርሞን ሳሀረ የተባለ ተጠርጣሪ ደግሞ በፍተሻ ደረሰኝ ብቻ የተገኘበት ቢሆንም የሀዋላ አገልግሎት በግሉ እንደሚሰራ ግን አምኖ ለፍርድ ቤቱ ገልጿል።

ኢትዮጲያዊ ዜግነት ያላቸው ዳንኤል መረሃ ወልደ ሰንበት የተባሉ ተጠርጣሪ ደግሞ በመምህር ሙያ ለ20 አመት መስራታቸውን ጠቅሰው ከወንጀሉ ጋር ግንኙነት እንደሌለው ገልጸዋል።

በመምህር ሙያ መሰማራታቸው ሌላ ወንጀል አይሰሩም ማለት አደለም ሲል ፖሊስ ምላሽ ሰቷል።

ሰመረ ተስፋ ማርያም የተባለ የኤርትራ ዜግነት ያለው ተጠርጣሪ ጠበቃ የሆነው ተስፋሁን አግደው በበኩሉ

መርማሪ ፖሊስ ለጊዜ ቀጠሮ መጠየቂያ የሚያስችል የጥርጣሬ መነሻ አለማቅረቡን ገልጾ ተከራክሯል።

ደንበኛዬ በስር የሚቆዩበትን ምክንያት በዝርዝር ባልገለጸበት ሁኔታ ታስሮ ሊቆይ አይገባም በማለት ዋስትና እንዲፈቀድለት ጠይቋል።

በወንጀል ህግ አንቀጽ 41 መሰረት ወንጀል ግላዊ መሆኑን የጠቀሰው ጠበቃው የተናጠል ተሳትፏቸው ባልተገለጸበት ሁኔታ ገንዘብ ተገኝቶበታል ተብሎ ማሰር ተገቢ አደለም በማለት ተከራክሯል።

በመርማሪ ፖሊስ በኩሉ ከ100 ሺህ በላይ ገንዘብ ግለሰብ ይዞ መገኘቱ በራሱ በህግ የሚያስጠይቅ ነው ሲል ምላሽ ተሰቷል።

የተለያዩ የውጭ ሀገር ገንዘቦች በመኖሪያ ቤታቸው የተገኘባቸው ከ15 በላይ ተጠርጣሪዎች ኢንባሲ በዶላር እንድንከፍል ስለሚጠይቀን ለክፍያ በቤታችን ያስቀመጥነው ገንዘብ ነው እንጂ ወንጀል አልፈጸምንም ሲሉ አብራርተዋል ።

በቤታቸው በተደረገ ብርበራ ከባንክ የሂሳብ ደብተር እና ከደረሰኝ ውጪ ጥሬ ገንዘብ እንዳልተገኘባቸው ገልጸው ከወንጀል ጋር የሚያገናኛቸው ጉዳይ እንደሌለ ያብራሩ ተጠርጣሪዎችም ነበሩ።

የጊዜ ቀጠሮ መዝገባቸውን የተመለከተው ፍርድ ቤቱ የሁሉም ተጠርጣሪዎች ተሳትፎ በቀጣይ ቀጠሮ በዝርዝር እንዲቀርብ አዟል።

ሁሉም የተጠረጠሩበት ጉዳይ ተመሳሳይ ሲሆን ፍርድ ቤቱ ግን የተለያዩ የምርመራ ቀናቶችን ለፖሊስ ፈቅዷል።

በዚህም ፖሊስ ከጠየቀው የ14 ቀን ጊዜ ውስጥ የምርመራ መዝገብ አደራጅቶ እንዲቀርብና የተጀመረው ምርመራን እንዲያከናውን አርባ ተጠርጣሪዎች ላይ የ7 ቀን የምርመራ ጊዜ የፈቀደ ሲሆን

ሌሎች አስር ተጠርጣሪዎች ላይ የ9 ቀን ተጨማሪ ምርመራ ቀናትን ለፖሊስ የፈቀደው ፍርድ ቤቱ ቀሪ ተጠርጣሪዎችን በተመለከተ ደግሞ የ10 ቀናት የምርመራ ጊዜን ፈቅዷል።

የጊዜ ቀጠሮውን የተመለከቱት ዳኛ ቀጠሮ ከመድረሱ በፊት ከወንጀሉ ጋር ግንኙነት የሌላቸው ግለሰቦች ካሉ ተጣርቶ እንዲለቀቁ የሚል ሀሳብ ለፖሊስ ሰተዋል።

Via Tarik Adugna

Exit mobile version