ETHIO12.COM

እንዲህ ባለ ሁኔታ አጨብጭቤ ቀረሁ

በጣም የምወደው አብሮ አደግ ጓደኛዬ ከአሜሪካ ማስታወሻ ሊልክልኝ ማሰቡን ነገረኝ፡፡ “ከቻልክስ Samsung S10+ ሞባይል ገዝተህ ላክልኝ” አልኩት፡፡ “መግዛቱን እገዛልሃለሁ፤ ግን በፖስታ ቤት ላያደርሱህ ስሚችሉ ብሩን ልላክልህ!” አለኝ፡፡ “ግድ የለህም የ120 ዓመት የዕድሜ ባለጸጋ የኾነዉን ፖስታ ቤት በአንድ ስልክ አንጠርጥው፤ ገዝተህ ላክልኝ እንጅ ያደርሰኛል፡፡ ደግሞ ፖስታ ሳጥን ቊጥር ጭምር ያለኝ ደንበኛ ነኝ” አልኩት፡፡ በሦስት ቀናት ውስጥ ገዝቶ “ይኸው ተቀበል እንግዲህ!” አለና የገዛባቸዉንና የላከባቸዉን ደረሰኞች ላከልኝ፡፡

ከሳምንታት በኋላ በሰጠኝ የምሥጢር ኮድ ስከታተል መልእክቱ ባሕር ዳር መድረሱን አረጋገጥኩ፤ ወደ ፖስታ ቤት ሔጄ ጠየቅሁ፡፡ መጀመሪያ “አልደረሰም” ተባልኩ፡፡ ምናልባት ገና ከአዲስ አበባ ወደ ባሕር ዳር እየመጣ ይኾናል ብየ ተመለስኩ፡፡ በቀጣዩ ቀን ሔጄ ጠየቅሁ፤ “ቀረጥ ሳይተመን ስለመጣ መልሰን ወደ አዲስ አበባ ልከነዋል፤ ጥቂት ቀን ጠብቅ” ተባልኩ፡፡ አቤት ምቀኝነት? ጉምሩክ አንድ የድሀ ሞባይል አልቀርጥም ብሎ ቢልክ መለሳችሁት? እያልኩ በሆዴ ተመለስኩ፡፡

ከቀናት በኋላ ብመላለስም መልሳቸው “አልመጣም” ኾነ፡፡ እሽ አዲስ አበባ ከማን ዘንድ እንደላካችሁት ንገሩኝ ብየ ሳፋጥጥ የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ባሕር ዳር ቅርንጫፍ ኃላፊዋን አናግር አሉኝ፡፡ ኃላፊዋን ሳናግር “የመጣልህ ባዶ ካርቶን ነው፤ ካርቶኑ መከፈቱን ስላየን ተፈራርመን መልሰን ወደ አዲስ አበባ ልከነዋል” አሉኝ፡፡ ያኔ ጓደኛዬ ላያደርሱህ ይችላሉ ያለኝ ትዝ አለኝና ደነገጥኩ፡፡ እንዴት ሊኾን ቻለ ስላት “እኛም አላወቅንም፤ ተጣርቶ ይነገርሃል” አለችኝ፡፡

አዲስ አበባ ከማን ዘንድ እንደተላከ ስጠይቃት ልትነግረኝ ፈቃደኛ አልኾነችም፤ ስልክም ልትሰጠኝ አልቻለችም፡፡ የምሥጢር ኮዱን ሰጥቸ አዲስ አበባ ያለ ሰው ላክሁ፡፡ “ወደ ባሕር ዳር ልከናል” የሚል ምላሽ ተሰጠ፡፡ ባሕር ዳር ወደ አዲስ አበባ አዲስ አበባ ወደ ባሕር ዳር፤ ዥዋዥዌ፡፡

በመጨረሻ ራሴ አዲስ አበባ ሔድኩና ከኃላፊዋ (ዋና ሥራ አስጻሚ) ዘንድ ቀርቤ ጉዳዩን አስረዳው፡፡ ለሚመለከተው ክፍል ደውላ “በአስቸኳይ አጣርታችሁ ምላሹን አሳውቁት” ብላ ወደሌላ የሥራ ክፍል ኃላፊ መራችኝ፡፡ ያ ሰው ደግሞ “መልእክቱ ስለመጥፋቱ ማመልከቻ ጻፍ” አለኝ፡፡ ጽፌ ሰጠሁት፡፡ “ከሰሞኑ እደውላለሁ” ስልኬን ተቀብሎ አሰናበተኝ፡፡ ተመለስኩ፡፡ ከቀናት በኋላ ደወለና “የተላከዉ መልእክት ጠፍቷል፤ እስከ ጉሙሩክ ሔደን ለማጣራት ሞከርን፤ ዕቃው ሲገባ የተወሰደን የስክሪን ምስል ጭምር ዐየን፤ ባዶ ካርቶን ነው የተረከብን!” አለኝ፡፡ እሽ አሁን ምን ላድርግ? አልኩት፡፡ “የላከልህ ሰው መክሰስ ይችላል፤ አንተ ምንም ማድረግ አትችልም” አለኝ፡፡ እንዲህ ባለ ሁኔታ አጨብጭቤ ቀረሁ፡፡

ከዚያን ቀን ጀምሮ የፖስታ ቤት ደንበኝነቴን ሰርዣለሁ፤ የፖስታ ሳጥን ቊጥሬንም ዘግቻለሁ፡፡ የገዛልኝ አብሮ አደግ ወንድሜን ውለታ ግን አልረሳም፡፡

Abraham Bewket

Exit mobile version