Site icon ETHIO12.COM

የጦርነቱ መቀጠል የግድ ከሆነ ?

የሰሜኑ ክፍል ህዝብ ሰላሙ ሊመለስለት ካስፈለገ፣ የዚህኛዉ ዙር ጦርነት በቅጡ መጠናቀቅ አለበት ባይ ነኝ። በሰላም ከሆነ ወያኔ ተሸንፎ ወደ ድርድር እንዲመጣ ማድረግ፣በሀይል ከሆነ ደግሞ ቢያንስ የወያኔ ወታደራዊ አቅም በወሳኝነት ከጭዋታ ዉጭ ሆኖ ጦርነቱ መጠናቀቅ ይኖርበታል። ትግራይ ዉስጥ የወያኔን አመለካከት ማሸነፍ እና አዲስ አሰተሳሰብ መትከል የሚቻለዉ በራሳቸዉ በትግራይ ተወላጆች ብቻ መሆኑን ማመን ይገባል። ይሄን የቤት ስራ በዋነኛነት ለትግራይ ልጆች መተዉ

የገባንበትን የርስበርስ ጦርነት በሰላማዊ መንገድ ለመጨረስ መንግስት፣የአገራችን ህዝብና አለምአቀፉ ማህበረሰብ ያደረጉት ያላሰለሰ ጥረት ወና ቀርቷል። መከረኛዉ የኢትዮጵያ ህዝብ በተለይም ደግሞ የጦርነቱ ግንባር ቀደም ገፈት ቀማሾች የአማራ፣አፋርና ትግራይ ህዝብ ዛሬም ወደሌላ ዉድመት መግባታቸዉን ስናይ እጅግ ያማል።

የዚህ ጦርነት መራዘም በመጀመሪያ ደረጃ ኢትዮጵያን እንደ ሀገር ከባድ ዋጋ እያስከፈላት ነዉ ገናም ያስከፍላታል። በተለይም ደግሞ የጦርነቱን ፊልሚያ በሜዳቸዉ ላይ የሚካሄድባቸዉ አማራ፤ትግራይና አፋር ክፉኛ ዳሽቀዋል፣ እየዳሸቁ ነዉ ገናም መዳሸቃቸዉ አይቀርም። ይህ ሁኔታ ዉሎ አድሮ ከሰላም በሁዋላም ቢሆን እንደ ሀገር የእኩል ማደግና የፍትሀዊነት ጥያቄን ማስከተሉ አይቀርም። ይሄን ሁሉ ከወዲሁ እያሰብን።

ስለዚህ ጦርነቱን ተከትሎ ለገጠመን እና ለሚገጥመን ወቅታዊዉም ሆነ የወደፊቱ ሀገራዊ ፈተና ቁልፍ መፍትሄዉ ይሄን ጦርነት በአጭር ጊዜ መቋጨት ነዉ። ይሄ ሊሆን የሚችለዉ ደግሞ አንድም ተጀምሮ የተሰናከለዉ የሰላም ድርድር እንደገና እንዲቀጥል በማድረግ ሁለትም የሀይል አማራጩን እስከመጨረሻ በመጠቀም ነዉ።

አሁን ለሁላችንም ጥያቄ ሁኖ የመጣዉ መንግስት ለ3ኛ ጊዜ ተገፍቶ የገባበትን ጦርነት እንዴት ይቋጨዉ ይሆን ? የሚለዉ ነዉ። በእኔ እምነት የመንግስታችንም ሆነ የኢትዮጵያ ህዝብ ትዕግስት የተሟጠጠ ይመስለኛል። ስለሆነም ካሁን በሁዋላ ይህ ሳንወድ የገባንበት 3ኛዉ ዙር ጦርነት በሰላምም ሆነ በሀይል መልክ ይዞ መቋጨት ይኖርበታል ባይ ነኝ። ይሄም ማለት:-

1. ጦርነቱ በሰላም ይቋጭ ከተባለ እሰየ። ግን ግን አሁን ወያኔ ወደድርድር መምጣት ያለበት ተሸንፎ መሆን አለበት። ልክ እንደባለፈዉ የአሁኑ ጦርነትም “በጉቢቢነት” አቁሞ ወደ ድርድር ከተገባ እመኑኝ 4ኛ ዙር ጦርነት ይኖረናል። ስለዚህ የ3ኛዉ ዙር ጦርነት ትንሹ መቋጫ ወያኔ በቃኝ ብሎና አምኖ ለሰላማዊ ድርድር እጁን ከሰጠ ብቻ መሆን አለበት። ወያኔ እዚህ ሁኔታ ላይ መድረሱ ሳይረጋገጥ ይሄንን ጦርነት ጀምረን ካቆምነዉ ዉሀ ቅዳ ዉሀ መልስ መሆኑ አይቀርም።

2. ጦርነቱን በሀይል መጨረስ የግድ የሚል ሁኔታ ከተፈጠረ:-ወያኔ በለመደዉ መልኩ የተዘረጋለትን የሰላም እጅ አልቀበልም ብሎ በጦርነቱ የሚገፋ ከሆነ ይህ ጦርነት የመጨረሻ ሊሆን ይገባል ባይ ነኝ። የዚህ ጦርነት ፍፃሜ ከማንም በላይ ለአማራ፣አፋርና ትግራይ ህዝቦች ሲበዛ አሰፈላጊ ነዉ። ስለሆነም ለሀገራችንም ሆነ ለሰሜኑ ክፍል ህዝብ ሲባል ይህ ጦርነት በአጭር ጊዜ መቋጨት ይኖርበታል።

አሰመሳዮች በተለይም የዉጭዉ አለም ይህ ጦርነት እንዲቆም መንግስት ላይ ብቻ አነጣጥረዉ የለመዱትንና አዳዲስ ጫናዎችን መፍጠራቸዉ አይቀርም። የነዚህ ሀይሎች ዋነኛ ፍላጎት እያላዘዙ በተራዘመ ጦርነት ደክመን በቁማችን እንድንወድቅ ነዉ። መጨረሻም ላይ የዘወትር ህልማቸዉ የሆነዉን የደከመች/የፈረሰች ኢትዮጵያን ማየት ነዉ። ስለሆነም መንግስትና የኢትዮጵያ ህዝብ ከዉጭም ሆነ ከዉስጥ ለሚደርስባቸዉ ተፅዕኖ ተንበርክከዉ ከላይ ከተቀመጡት ሁለት መንገዶች አንዱንም በዉል ሳያሳኩ ይህ ጦርነት የሚቆም ከሆነ፣ የአገራችን ፈተና በተለይም የጦርነቱን ፍልምያ የሚያስተናግደዉ የሰሜኑ የአገራችን ክፍል የበለጠ እንዲደቅና እየደቀቀ እንዲቀጥለሰ መፍቀድ ነዉ የሚሆነዉ።

በመሆኑም አገራችን በተለይም የሰሜኑ ክፍል ህዝብ ሰላሙ ሊመለስለት ካስፈለገ፣ የዚህኛዉ ዙር ጦርነት በቅጡ መጠናቀቅ አለበት ባይ ነኝ። በሰላም ከሆነ ወያኔ ተሸንፎ ወደ ድርድር እንዲመጣ ማድረግ፣በሀይል ከሆነ ደግሞ ቢያንስ የወያኔ ወታደራዊ አቅም በወሳኝነት ከጭዋታ ዉጭ ሆኖ ጦርነቱ መጠናቀቅ ይኖርበታል። ትግራይ ዉስጥ የወያኔን አመለካከት ማሸነፍ እና አዲስ አሰተሳሰብ መትከል የሚቻለዉ በራሳቸዉ በትግራይ ተወላጆች ብቻ መሆኑን ማመን ይገባል። ይሄን የቤት ስራ በዋነኛነት ለትግራይ ልጆች መተዉ ያስፈልጋል።

ለሁሉም ይሄኛዉን ዙር ጦርነት ለመቋጨት ከላይ ያስቀመጥኳቸዉ ሁለቱም አማራጮች እንደ አግባባቸዉ በደንብ ሊሰሩ ከሆነ ጦርነቱ በሁለንተናዊ የህዝብ ተሳትፎ መደገፍ አለበት። ለዚህ ደግሞ የመከላከያ ሀላፊዎችና የክልሉ መንግስት ጥሪ አድርገዋል። ስለሆነም ሁሉም ዜጋ አቅሙ በፈቀደለት ሁሉ ለመከላከያና ለክልላችን መንግስት ጥሪ ምላሽ መሰጠት ይገበዋል። አቅሙ እያለዉ ግን ደግሞ ለተደረገለት አገራዊ ጥሪ አወንታዊ ምላሽ መስጠት ያልፈለገ ወገን ደግሞ ቢያንስ አገራዊ ጥሪዉን ከማደናቀፍ መታቀብ ይኖርበታል ባይ ነኝ።

በመጨረሻም አገራዊም ሆነ ክልላዊ ጥሪዉ ያለፉትን ጥሪዎችና የነበረዉን ምላሽ ተመክሮዎች የቀመረ ቢሆን ይመከራል። በተለይም ብዛት ከጥራት ጋር መታየት ይኖርበታል። በዚህ በኩል የሚታወቁ ድክመቶችና ጥንካሬዎች ስላሉ ድክመቶቹን አለመድገም በአንፃሩ ጥንካሬዎቹን አሳድጎ የተሳካ ተግባር መከወን ይገባል። ስራዉ ግን ከወዲሁ ቢጀመር ጥሩ ነዉ። በተለይ አማራ ክልል መፋዘዝ አያለሁና ቢስተካከል ጥሩ ነዉ። አንዳንዴ የክልሉ መንግስት ምን እያለ እንደሆነ ግራ ግቢት ይለኛል።

ወንድም Ztseat Saveadna Ananya ግን አልነቃ ያለዉን አማራ እንደ አጠቃላይ በተለይም ደግሞ የጎንደርን ኤሊት እንዲነቃና በወያኔ ላይ የመረረ ጥላቻ እንዲኖረዉና ራሱን በሚገባዉ ልክ እንዲያዘጋጀ ባልተቋረጠ መልኩ ለምታደርገዉ ጥረት እጅግ አመሰግንሁ¡¡¡ እኛንማ አልሰማን ብሎ ስንት አደከመን መሰለህ ወንድማለም። እንዳንተ ያለ የጠላት ወዳጅ አይቸ አላዉቅም¡¡ እንዲህ ማንቃትህን ቀጥልልኝማ።

መዉጫ!

የገባንበት አዉዳሚና በህዝብ ማዕበል ታጅቦ የሚካሄድ ጦርነት ነዉ። ስለዚህ ይሄን ጦርነት አሰተማማኝና ብልጫ ባለዉ ህዝባዊ ማዕበል መመከትና ማሸነፍ እስካልተቻለ ድረስ በጦርነት ሂደት መገፋፋት ይኖራልና እንደዚህ አይነት ቢያጋጥሙ እንኳን እንደልሙድ መዉሰድ እንጅ መደናገር አይገባም። በዚህ በኩል እኮ የ3ኛዉ ዙር ጦርነት ምርጥ ተሞክሮ አለን።

Exit mobile version