Site icon ETHIO12.COM

በካይሮ የተዘረጋው ሰሞነኛ ትህነጋዊ ሴራ

ብሂሉ “ሆድ ካገር ይሰፋል” እንዲሉ ቢሆንም ግን ሆድ ካገር ግን አይበልጥም!

የኡሁሩ ኬንያታ የስልጣን ዘመን ማብቃት በራሱ ራእይ እራመዳለሁ በሚለው ፕሬዝደንት ሩቶ መተካቱ ለሩዋንዳ ሰሞንኛ መንቀልቀል ዋነኛው ገፊ ምክንያት ሊባል ይችላል። ኡሁሩ የህወሃት ውለታ ከምእራባዊያን ታዛዥነቱ ጋር የተዳመረባቸው ነበሩ። ኡሁሩ በኬኒያ የመጀመሪያ ፕሬዝደንታዊ ውድድራቸው ወቅት ዜጎችህን አስጨፍጭፈሃል ያሏቸው ምዕራባዊያን አለም አቀፉን ፍርድ ቤት እያጣቀሱ ሲያጣድፏቸው በጉንፏ ደብቃ ያሻገረቻቸው ህወሃት ነበረች። ይህንኑ ባገናዘበ አካሄድ ነበር ከአሜሪካና ብሪታኒያ ተልዕኮ ተቀብለው ሲቸገሩ የቆዩት።

አል-ቡርሃን፣ የካይሮ ፈርኦኖችን እባብ በመዳፉ ይዞ መርዙን ኢትዮጵያ ላይ በህወሃት በኩል ለማራገፍ የሚንደፋደፍ ለሀገሩ የማያስብ ፍጥረት ሊባል የሚችል ጀነራል ነው። የህወሃትን ተረፈ-ወራሪ ተረክቦ ከስደተኛ ጣቢያ እየቀነሰ ለውጊያ ሲያዘምት በተደጋጋሚ ተስተውሏል።
ካይሮ ከናይሮቢ ጋር ስንቅ አደራጅተው ከሚልኩት ሸኔ ደቡብ ሱዳን ዉስጥ ከተገንጣይ የቤኒሻንጉል አማፂ ቡድን ጋር ጥምረት ፈጥረዉ እየሰለጠኑ መቆየታቸውን፣ ሲቀጥልም የውጊያ ሙከራ ሲያደርጉ እንደነበር የሚታወስ ነው። መሰሉን ፀረ-ኢትዮጵያ ጥልፍልፍ ለአዲስ አበባ አጋር የነበሩት አሜሪካና አውሮፓ ህብረት ክህደትን እስከመፈፀም አድርሷቸዋል። ይህ ነጭ ክህደት አዲስ በርግጥም አዲስ አይደለም።

የአህጉረ አፍሪካን ጂኦፖለቲካዊና የተፈጥሮ ሀብት ለመቀራመት ያመቻቸው ዘንድ ያኔ፣ የወቅቱ አፍሪካዊ ትውልድ መሪዎች ሲሉ ቁልምጫ ያዘነቡላቸው መሪዎች መካከል፣ መለስ ዜናዊ፣ ኢሳያስ አፈወርቂ፣ ፖል ካጋሜ እና ዩዌሪ ሙሴቬኒ እዚጋ የምንጠቅሳቸው ናቸው።
ፕሬዝደንት ኢሳያስ ከጠበቋቸው በተቃራኒ ቅድሚያ ለሉአላዊነት በማለታቸው በጠላትነት ተፈርጆ ሊያንበረክኩት ያልፈነቀሉት ድንጋይ አልነበረም። የዩጋንዳው ሙሴቪኒም በተመሳሳይ..። ኢትዮጵያ ላይ ጥርስ የነከሱትም እንደ ፖል ካጋሜ አይነት ታማኝ አገልጋይ አትሆንም በሚል ጥርጣሬ ነው።

ፖል-ካጋሜ፣ አፍቃረ ህወሃትነታቸው በተለይም የተመድ ፀጥታው ምክር ቤት ስለ ኢትዮጵያ 10ኛውን ጉባኤ ባደረገበት ሰሞን ግልጥልጡ ሲወጣ የታዘብነው ነበር። ከጉባኤው ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ july 2021 ጂኦ-ፓለቲክስ ፕሬስ የተባለ ተቋም ያወጣው ትንተና ነበር።
Geopolitics press እንዳሰፈረው “አሜሪካ በ1980 እና 90ዎቹ በታላላቅ ኃይቆች ሀገራት Great Lakes ቀጣና ሀገራት በዩጋንዳ፣ ሩዋንዳ፣ ቡሩንዲ፣ ኬኒያ፣ ታንዛኒያና ኮንጎ የፈፀሙትን ጥፋት በአፍሪካ ቀንድ ሊደግሙት ማቀዳቸውን አስረድቶ ነበር።
ፅሁፉ ወደ ኋላ መለስ በማለት የዩጋንዳና የሩዋንዳ ፕሬዝዳንቶች በመጀመሪያ በዩጋንዳ መፈንቅለ መንግስት ማድረጋቸውን፣ ሲቀጥልም ሙሴቪኒ ፖል ካጋሜን ወደ አሜሪካ ልኮ የስለላ ስልጠና እንዲወስድ ማድረጉን፣ ከስልጠና ሲመለስም መጥቶ ከ CIA ጋር ተባብሮ የቀድሞውን የሩዋንዳ ፕሬዘዳንት አስገድሎ ስልጣን መያዙን አውስቶ፤ በኋላም ሙሴቪኒ እና ካጋሜ ወደ ኮንጎ ጦር ማዝመታቸውን ጠቅሶ ነበር።

ካጋሜ ከሲአይኤ ጋር ተባብሮ ሞቡቱ ሴሴኮን ከስልጣን አስወግደው ሎውረን ካቢላን ስልጣን ላይ ማውጣታቸው፤ ይሄን ተከትሎም ከቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ቢል ክሊንተን ጋር ትስስር የነበረው የማዕድን ድርጅት፣ እንዲሁም ጆርጅ ቡሽ(ትልቁ) የቦርድ አባል የሆነበት የወርቅ አምራች ድርጅቶች የ 157 ቢሊዮን ዶላር ውል ከኮንጎ መንግስት ጋር መዋዋላቸው በተቋሙ ሪፖርት ተዘርዝሯል። CIA እና የብሪታኒያው MI6 ከፖል ካጋሜ ጋር በመሆን የሩዋንዳውን የዘር ማጥፋት ፈፅመዋል ሲል አስቀምጧል።

ፓል ካጋሜን ከአነሳሱ ጀምሮ በከበሩ ማዕድናት ወደበለፀገችው ኮንጎ የጦር ሀይል አዝምቶ የምእራባዊያንን የብዝበዛ ግዳጅ አየተወጣ የቀጠለ መሪ ነው። 70 በመቶው የዓለም የኮባልት ክምችት የሚገኘው በኮንጎ ነው። (ኮባልት ባትሪዎችን ለማምረት ወሳኙ ንጥረ ነገር ነው፤ ሌሎች በማግኔት የበለፀጉ የኮምፒዩተሮችና ሞባይሎች ኤሌክትሮኒክ ቦርድ ማምረቻ ማዕድን በተመሳሳይ በኮንጎ በብዛት የሚገኝ ነው።
የተመድ አይሮፕላኖችን በመጠቀም ጭምር ካጋሜ የሚያስተባብረው የብዝበዛ ፕሮጀክት የኮንጎ ማዕድናትን ወደ ምዕራባዊ ሀገራት እያጋዙ መቀጠላቸውን ጭምር Geopolitical press በወቅቱ አስነብቧል።

ታዲያ በሐምሌ 2021 የፀጥታው ምክር ቤት ጉባኤ ላይ ካጋሜ የተመድ ጦር ወደ ኢትዮጵያ ጣልቃ ይግባ ማለቱ በአጋጣሚ ሳይሆን “አብሮ አበድ” ጓዱ ህወሃትን ለመታደግ ነበር።

ካጋሜ እዚህ ለመድረሱ ወያኔ ጦር መሣሪያ እየሰበሰበች በዩጋንዳ በኩል ወደ ኪጋሊ እየላከችለት የኸርማን ኮኸን ቡድን በፈጠሩት ማመቻቸት መጠቀማቸው በበርካቶች ተገልጿል። ይህ ትብብራቸውም በበርካታ ባህርያለው የሚመሳሰሉ አድርጓቸዋል።

ካጋሜ የራሱን ግንባር RPF እስኪያቋቁም ከሙሴቬኒ ጋር በዩጋንዳው አማጺ ግንባር NRA ወታደራዊ መሪ ሆኖ አብሮ ተዋግቷል። መለስ ዜናዊ እና ህወሃት ሶማሊያዊ ሆነው ኢትዮጵያን እንደወጓት ማለት ነው..።
ካጋሜ እና ህወሃት በቀጠናቸው ጎልተው ለመታየት ተገንጣይ ሃይሎችን በማደራጀት ሀብትና ሕዝብን የመቆጣጠር ሴራ ሲፈፅሙ የቆዩ ናቸው። ወያኔ በሶማሊያ የፈጸመው፤ ካጋሜ ደግሞ በኮንጎ የፈፀመው ለአብነት ይጠቀሳል። ካጋሜ በኮንጎ ጦርነት 8 ሚሊየን ሰዎች ለመገደላቸው እጃ አለበት ይባላል።

የአሁኑ የሩዋንዳ ፕሬዝዳንት የቀድሞ በ CIA እና MI6 የሰለጠነው ፖል ካጋሜ አቀነባብሮ በመራው መፈንቅለ መንግስት የዩጋንዳው ሚልተን ኦቦቴ ለስብሰባ ወደ ሲንጋፖር በተጓዙበት ከስልጣን ወርደዉ ዩዌሪ ሙሴቬኒ ወደ ስልጣን ሊወጡ ችለዋል፡፡
ሙሶቬኒ 1986 ላይ ስልጣን ከጨበጡ በኋላ የካጋሜን ውለታ ለመመለስ የሩዋንዳ አማፂ ግንባር የተባለ ጦር እንዲያቋቁም በማድረግና ትጥቅና ስንቅ በማቅረብ ያኔ ሥልጣን ላይ የነበረውን በሁቱዎች የተዋቀረውን መንግሥት 1994 ላይ ተክቶ ወደ ሥልጣን እንዲወጣ አድርጎታል።

ህወሃት ሃውዜን ላይ እንደፈፀመው ካጋሜ የሩዋንዳውን ጭፍጨፋ RPF በሚባለው አማፂ ግንባር ታጣቂዎቹ አማካኝነት የወቅቱን የሩዋንዳ መንግሥት በንፁሃን ሞት በማጋለጥና ተጠያቂ በማድረግ ሥልጣን ለመጨበጥ እንደተጠቀመበት ታሪክ ይነግረናል።
ካጋሜ የወቅቱ የሩዋንዳ (ሁቱ የነበሩ) ፕሬዝደንት በተቀነባበረ የአውሮፕላን የሚሳይል ጥቃት ካስገደሉት በኋላ በሁቱዎች መካከል ቂም በቀል እንዲነሳ በማድረግና ቱትሲዎችን በማስጨፍጨፍ የራሱ ጎሳ ሕዝቦች ሞት ለሥልጣን መወጣጫ ማድረጉን በርካታ ድርሳናት ያወሱታል። በሕዝብ እልቂት ሥልጣን የመሸመት ህወሃታዊ መርህ መሆኑ ነው።

▪️አል-ቡርሃን ለህወሃት – ራስ ሳይጠና ጉተና
የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ የህወሃትን ጥፋት እንደሚደግፉ ይታወቀል። በህዳሴ ግድቡ እንዲሁም በድንበር ይገባኛል የሚያነሳው የሱዳኑ አልቡርሃን ስብስብ ከህወሃት በተጨማሪ የጉምዝ እና የቅማንት ታጣቂዎች በድንበር እንዲንቀሳቀሱ ማመቻቸቱ አሁንም ተሰምቷል። ከዛም አለፍ ብሎ የኢትዮጵያን የቀውስ ማዕካል እንድትሆን እነዚህን ታጣቂዎች የጦር መስርያ እና ሎጀስቲክ እንደምታቀርብ እንዲሁም ስልጠና እንደምትሰጥ መረጃ እያስረገጡ ይገኛሉ። ሱዳን የህወሃት ታጣቂዎች እንዳይበተኑና ዳግም ጥቃት እንዲፈፅሙ በስደተኛ ስም ከለላ መሆኗን አሁንም እንደቀጠለችበት መሆኗም ተሰምቷል። ከ 1700 በላይ ትጥቅ የፈቱ ታጣቂዎች አሲራ በሚባል ቦታ በማሰባሰብ በጊዜያዊነት እንዲቀመጡ መደረጋቸውንም ነው የደረሰኝ መረጃ የሚያረጋግጠው።

▪️የካይሮ ምኞት
በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙርያ እንቅልፍ ተኝታ የማታድረው የሀገራችን እድሜ ዘመን ጠላት ግብፅ የህወሃትን ቡድን ከገንዘብ ጀምሮ በፀረ-ኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ጫና ሁሉ ስትተባበረው መቆየቷ የሚታወቅ ነው። በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ጥቃት እንዲሰነዝሩ በመደገፍ ከድሮ ጀምሮ የምትታወቀው ካይሮ አሁን ላይ በወጡ መረጃዎች መሰረት ደግሞ ለህወሃት ቡድን በእዬ 45 ቀናቱ 500 ሺ የአሜሪካ ዶላር ትልካለች ተብሏል።

▪️ካይሮ እና አል-ቡርሃን
ግብፅ እና የሱዳኑ ጀነራል አልቡርሃን ኢትዮጵያ ተዳክማና የግድቡ ግንባታ ተስተጓጉሎ ለማየት ለአሸባሪው ህወሃት እቅድ ለመንደፍ ውይይት ማድረጋቸው ተሰምቷል። በአንድ በኩል ህወሃት ከከተማ ሳይወጣ ውጊያውን እንዲያደርግና ይህን ተከትሎ በሚጠር የንፁሃን ዜጎች እልቂት ለአለም በማሳየት ኢትዮጵያ ላይ ጫና እንዲፈጠር የተሸረበ ሴራ ይገኝበታል።
በሌላ በኩል ህወሃት በመቀሌ መቆየት ካልቻለ ወደ ተራራማ ቦታዎች ሄዶ ጊዜ እንዲገዛና በዚያም ራሱን እንዲያጠናክር ያቀዱት ሁለተኛ አማራጭ እቅድ ማስቀመጣቸው ነው የታወቀው።

▪️የካጋሜ ህወሃታዊ የቤት ስራ
ከሰሞኑ የግብፅ የደህንነት ተቋም ከሩዋንዳ ጋር በመተባበር ከቻይና ወደ ግብፅ የገቡ ድሮኖች እና ፀረ ድኖሮች ሱዳን ለሚገኙ የሽብረተኛው ተዋካዩች ለመስጠት ማቀዳቸውን የደረሰን መረጃዎች ተሰምተዋል። ለህወሃት ከጦር መሳርያ ድጋፍ በተጨማሪ ታጣቂዎቻቸውን ለማሰልጠን አቅጣጫ ማውጣታቸውም ነው የተሰማው።

▪️መጠቅለያ
በኢትዮጵያ እንደ ሀገር የመዉደቅና መነሳት ላይ ታሪካዊ ሀላፊነቱ የኛው እና የኛው ብቻ መሆኑን መዘንጋት የለብንም። ርስ በርስ ስንናከስ የኢትዮጵያ ጠላቶች በያቅጣጫው እየቃኙን ናቸው። ሆድ አደር ከተበራበከተ ደግሞ ሾልከዉ የሚገቡበት ስስ ብልት አገኙ ማለት ነው። በሀገር ሉአላዊነት የምንደራደር ዝንጉዎች አንሁን..።

ሆድ ካገር ይሰፋል ግን ካገር አይበልጥም! የዓባይልጅ እስሌማን ዓባይ

Exit mobile version