Site icon ETHIO12.COM

የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ መልቀቂያ ፈተና የትምህርት አሰጣጥ ለዉጥ አንዱ ማሳያ ነዉ

– የመጀመሪያ ዙር የፈተና አሰጣጡ ከጥቂት ችግሮች በስተቀር በተሳካ ሁኔታ ተከናውኗል፣

– በሀገሪቱ ታሪክ በርካታ ተማሪዎችን በተወሰኑ ማዕከላት ሰብስቦ የመፈተን ልምድ የአሁኑ የመጀመሪያ ነው፣

– የጸጥታ አካላት፣ ትምህርት ተቋማት አመራሮችና ሠራተኞች ላደረጉት አስተዋጽዖ መንግሥት ክፍ ያለ ምስጋና አቅርቧል፣

ሀገራችን ኢትዮጵያ በለውጥ ጎዳና ውስጥ ከገባችበት ጀምሮ በርካታ ተቋማዊ እና የፖሊሲ ሪፎርም ርምጃዎችን ወስዳለች። ከነዚህ የለውጥ ርምጃዎች መካከል አንዱ የትምህርት ዘርፍ ሪፎርም ነው። ባለፉት ዓመታት ከተደራሽነት አንፃር መልካም ሥራዎች የተሠሩ ቢሆንም የትምህርት ጥራት በእጅጉ ተዳክሞ ቆይቷል።

መንግሥት የትምህርት ጥራትን ሊያሳድጉ የሚችሉ ፓኬጆችን በመቅረፅ በርካታ የሪፎርም ርምጃዎች እየወሰደ ይገኛል። ከተወሰዱ ርምጃዎች መካከል የምዘና ሥርዓትን ማሻሻል አንዱ ነው። ይሄንን ለማሳካት አንዱ ምእራፍ የሆነው የ2014 ዓ/ም የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ የመልቀቂያ ፈተና በተለየ ሁኔታ በከፍተኛ ዝግጅትና ተቋማዊ ቅንጅት በመሰጠት ላይ ይገኛል።

የአሁኑ ፈተና አሰጣጥ ከዚህ በፊት በብልሹ አሠራር፣ በስርቆት እና በማጭበርበር ይደረግ የነበረውን የፈተና ሂደት በማስቀረት ሁሉም ተማሪ እኩል የሚመዘንበት ዕድል እንዲፈጥር ታሳቢ ያደረገ ነው።

በዚህ በ2014 ዓ/ም ሀገር አቀፍ የመልቀቂያ ፈተና ከኩረጃና ከስርቆት እንዲሁም ከሌሎች ብልሹ አሠራር የጸዳ እንዲሆን መንግሥት በቢልዮን የሚቆጠር በጀት በመመደብ ወደ አንድ ሚልየን የሚጠጉ ተማሪዎችና ፈታኝ መምህራንን በማጓጓዝ፣ እንዲሁም አስተባባሪዎችን በመመደብ በ160 ማዕከላት ፈተናው በሰላም እና ከጸጥታ ሥጋት ነፃ በሆነ መልኩ እንዲፈፀም በማድረግ ለትምህርት ጥራት ያለውን ቁርጠኝነት አሳይቷል።

እስከ አሁን ባለው አፈጻጸም የመጀመሪያ ዙር የፈተና አሰጣጡ ከጥቂት ችግሮች በስተቀር በተሳካ ሁኔታ ተከናውኗል።

በሀገራችን ታሪክ ሚሊዮን ተማሪዎችን በተወሰኑ ማዕከላት ሰብስቦ የመፈተን ልምድ የአሁኑ የመጀመሪያ ነው።

በትምህርት አመራሩ ቁርጠኝነት፣ በተፈጠረው ተቋማዊ ቅንጅት፣ በጸጥታ አካላት ትጋት፣ በመምህራንና በሌሎች የትምህርት ዘርፉ ባለድርሻ አካላት የዓላማና የተግባር አንድነት፣ የፈተናው ሂደት በተረጋጋና በተፈለገው ሁኔታ ሊቀጥል ችሏል።

አልፎ አልፎ ችግሮች በሚያጋጥሙበት ወቅት እንኳን ማኅበረሰቡ መክሮና ገሥጾ ችግሮች እንዲቀረፉ አድርጓል።

ልጆቹን በማረጋጋትና አስፈላጊውን ሁሉ ትብብርበማድረግ ለትምህርት ጥራት ያለውን ድጋፍና ቀናነት ገልጧል።

በዚህም የሕዝብ ቅቡልነት ያለው ማንኛውም ዕቅድና ሥራ ሁሌም የሚሳካ መሆኑን ለሌሎች የሪፎርም ሥራዎቻም ጭምር ትምህርት ተወስዶበታል።

በዚህ አጋጣሚ ልጆቹን በማበረታታት፣ ተፈታኞቹና ፈታኝ መምህራን ወደየማዕከላቱ ሲገቡ አቀባበል በማድረግ፣ ችግሮች ሲፈጠሩ ተማሪዎቹን በማረጋጋት፣ ሲያጠፉም በመምከርና በመገሠጽ ሂደቱ ሰላማዊና የተረጋጋ እንዲሆን ላደረጉ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና መላው ማኅበረሰብ፣ ፈታኝ መምህራን፣ የጸጥታ አካላትና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አመራሮችና ሠራተኞች ላደረጋችሁ አስተዋጽዖ መንግሥት ክፍ ያለ ምስጋና ያቀርባል።

በቀጣይ ሳምንት የሚሰጠው ሁለተኛው ምእራፍ ፈተና በተሻለ ሁኔታ እንዲከናወን ሁላችሁም የጀመራችሁትን ጥረት እንድታጠናክሩ መንግሥት ጥሪውን ያቀርባል።

ጥቅምት 2 ቀን 2015 ዓም
አዲስ አበባ
የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት

Exit mobile version