Site icon ETHIO12.COM

ትዊተር የዘጋቸው የኢትዮጵያን እውነት የሚያስረዱ አካውንቶችን ለማስከፈት እንቅስቃሴ ተጀመረ


ትዊተር የዘጋቸው የኢትዮጵያን እውነት የሚያስረዱ አካውንቶች ዳግም እንዲከፈቱ የማድረግ ዓላማ ያለው እንቅስቃሴ ተጀምሯል።

ጋዜጠኛ ሄርሜላ አረጋዊ “ምንም ጥፋት ሳያጠፉ እውነትን በመናገራቸው ብቻ የታገዱ የትዊተር አካውንቶች ዳግም መከፈት አለባቸው” ብላለች።

ትዊተር ኢትዮጵያን ደግፈው የሚንቀሳቀሱ የማኅበረሰብ አንቂዎችን አካውንቶች መዝጋቱ ይታወቃል።

ከተዘጉት አካውንቶች መካከል የ‘ዲፌንድ ኢትዮጵያ ታስክፎርስ ኢሮፕ’፣ ‘ኖሞር ሃብ’፣ ትውልደ-ኢትዮጵያዊው ነቢዩ አስፋው፣ ትውልደ-ኢትዮጵያዊቷ ኔዘርላንዳዊት ዶ/ር ሚድል ላንደርና ሌሎችም ይገኙበታል።

እርምጃው የኢትዮጵያን ድምጽ ለማፈንና ለመገደብ የተደረገ መሆኑንም በኢትዮጵያ የዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት እየገለጹ ይገኛሉ።

ይሄንንም በመቃወም በአሜሪካ የሚኖሩ ትውልደ-ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች በተደጋጋሚ በኩባንያው መቀመጫ ሳን ፍራንሲስኮ ከተማ በሚገኘው የትዊተር ዋና መስሪያ ቤት ሰላማዊ ሰልፎችን ሲያካሂዱ ነበር።

ትናንት የዓለም ቁጥር አንድ ባለሀብት ኤለን መስክ ቲዊተርን በ44 ቢሊዮን ዶላር መግዛቱ ይፋ መደረጉ ይታወቃል።

በ”ነጻ ሃሳብ” እንደሚያምን የሚነገርለት ኤለን መስክ ትዊተርን መግዛቱን ተከትሎ ኩባንያው የዘጋቸውን የኢትዮጵያን እውነት የሚያስረዱ ‘አካውንቶች’ ዳግም ማስከፈትን ዓላማ ያደረገ የማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻ መጀመሩን ኢዜአ ከአስተባባሪዎቹ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

ጋዜጠኛ ሄርሜላ አረጋዊ “ምንም ጥፋት ሳያጠፉ እውነትን ብቻ በመናገራቸው የታገዱ የትዊተር አካውንቶች ዳግም መከፈት አለባቸው” ስትል ተቃውሞዋን ገልጻለች።

በዘመቻው “ሀሳብን በነጻ የመግለጽ መብት መከበር አለበት፣ ነጻ ሃሳብ የዴሞክራሲ መሰረት ነው፣ የኢትዮጵያ ድምጾች መታፈንና መገደብ የለባቸውም፣ ትዊተር የዘጋቸውን የኢትዮጵያ ደጋፊ አካውንቶችን መልሶ ይክፈት እና ኤለን መስክ የታገዱት የትዊተር አካውንቶች እንዲከፈቱ ያደርጉ” የሚሉ መልዕክቶች እየተላለፉ ይገኛሉ።

በ”ነጻ ሃሳብ” የሚያምነው ኤለን መስክ ትዊተርን መግዛቱ አካውንቶቹን ድጋሚ ወደ አገልግሎት ለመመለስ መልካም አጋጣሚን የሚፈጥር እንደሆነም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ-ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች የተጀመረውን የማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻ እንዲቀላቀሉም ጥሪ ቀርቧል።

የዓለም ቁጥር አንድ ባለሃብት ኤለን መስክ በሰጠው አስተያየት “ነጻ ንግግር የዲሞክራሲ መሰረት ነው፤ ትዊተር ደግሞ ለሰው ልጅ ቀጣይ ሕይወት ወሳኝ ጉዳዮች የሚንሸራሸሩበት የዲጂታል ከተማ አደባባይ ነው” ብሏል።

የኩባንያው አርማ የሆነችው “ድንቢጥ ወፍ ነጻ ወጣች” ሲልም ገልጿል።

Exit mobile version