ETHIO12.COM

የጆ.ባይደን አስተዳደር የሰላም አማራጭ ንግግሩን ቀድሞ የትህነግን ፍላጎት አቋም አድርጎ አቀረበ

በተደጋጋሚ የትህነግ አመራሮችና ደጋፊዎች፣ የአውሮፓ ህብረትና የህብረቱ አካላት ሲደጋግሙ የነበሩትን አቋም አሜሪካ በአራት አሳቦች ጠቅላላ ከንግግሩ ፍጻሜ የሚጠበቅ እንደሆነ አስታወቀች። መንግስት ጣልቃ ገብነቱ አሳስቢ መሆኑንን ጠቅሶ ለጫናው እንደማይንበረከክ ማስታወቁ ይታወሳል።

በቅርቡ በትህነግ ሚዲያ አቶ ስዬ አብርሃ በዝርዝር ያቀረቡትን መሰረታዊ የድርጅታቸው ፍላጎቶችን ቃል በቃል ደግማ አሜሪካ በትናንትናው እለት እንዳስታወቀችው አራት አንኳር ጉዳዮች ላይ ስምምነት ይደረጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ነው።

“በኢትዮጵያ ተፋላሚ ወገኖች መካከል የሚደረገው የሰላም ንግግር አራት ግቦች አሉት ። አፋጣኝ የተኩስ አቁም፣ ያልተገደበ ሰብዓዊ ዕርዳታ ፣ የሰላማዊ ሰዎችን ደህንነት ለመጠበቅ ተጨማሪ እርምጃዎች መውሰድና የኤርትራ ወታደሮች ከሰሜን ኢትዮጵያ መውጣታቸውን ማረጋገጥ” ስትል አሜሪካ ያስታወቀችው በውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ቃል አቃባይ ኔድ ፕራይስ በኩል ነው።

መንግስት አካሄዱን በውል በመገንዘብ ከላይ የተነሱትን ፍላጎቶች አንድ በአንድ እያነሳ ከህግ፣ ከመንግስት ስልጣንና ከአገሪቱ ሕገ መንግስ ጋር በማያያዝ እንደማይቀበላቸው፣ የተነሱት ነጥቦች አግባባቸውን ጠብቀው በህግ በተቀመጠ ስልታን እንደሚከናወኑ፣ አማጺው ቡድን የሚለው አካል በህገ መንግስቱ መሰረት የስራ ጊዜው ያበቃና ህጋዊ ማንዴት የሌለው በመሆኑ የሽግግር አስተዳደር እንደሚተከል፣ ትህነግም ይህን አክብሮ ልክ እንደ ጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉል፣ አፋር … ክልሎች አንድ መሆኑንን አምኖና በተለየ መልኩ ራሱን ማየት እንዲያቆም፣ በአገሪቱ አንድ መከላከያ ብቻ ስለሚኖር ትጥቅ እንዲፈታ የያዘውን አቋም ለህዝብ ይፋ ሲያደርግ መቆየቱ ይታወሳል። ሕዝብም ከዳር እስከዳር ወጥቶ ” አሜሪካ በአገራችን ጉዳይ ጣልቃ አትግቢ” ብሏል። ከሁሉም በሁዋላ መንግስት ስም ሳይጠቅስ ” ግንኙነቴን ለመረመር እገደዳለሁ” ሲል አቋሙን አጽንቶ መቆየቱ ይታውሳል።

ቀደም ስሊ ባወጣነው ዘገባ ድርድሩ ከመጀመሩ በፊት ትህነግ ትጥቅ ለመፍታት መስማማቱን፣ ራሱን እንደክልል ለማየትና የፌደራል መንግስቱን ለማክበር መስማማቱ መዘገባችን ይታወሳል። “አሜሪካ አታለሉን” ብለው የሚደርሳባቸውን ጫና እንዲያልፉ ምክር መስጠቷንና የኢትዮጶያ መንግስ አቋም ከበረታ ምንም ማድረግ እንደማይቻል ለትህነግ ሰዎች ማስታወቃቸውን በዜናው ማካተታችን ይታወሳል።


ትህነግ ትጥቅ ለመፍታት ወሰነ – ቴዎድሮስ አድሃኖም አብይ አህመድን በስልክ ተማጸኑ፤ አዲግራት መከላከያ መዳፍ ገባች

“ከውጭም ሆነ ከውስጥ በትህነግ ተስፋ የቆረጡ ቁርጠኛ አቋማቸውን በገሃድ ባያስታውቁም፣ ነገሮች ሁሉ መገለባበጣቸውን እያመኑ ነው” ሲሉ የሚናገሩ፣ በዚህ ስሜት ላይ የመንግስት ጦር አዲግራትን ከተቆጣጠረ በደቡብ አፍሪካው ንግግር ትህነግን ከሚወክሉ አካላት ጋር ምን ዓይነት ስምምነት እንደሚደረግ ከወዲሁ መገመት አዳጋች እንዳልሆነ እየገለጹ ነው።


ከስር ጉዳዩን አስመልክቶ ኢትዮጵያ ኢንሳይደር የዘገበውን ያንብቡ።

የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት እና የህወሓት የሰላም ንግግር መራዘም፤ ሁለቱ ወገኖች “የተራራቀ” አቋም ይዘው ወደ ደቡብ አፍሪካ ማምራታቸውን እንደሚጠቁም የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ቃል አቃባይ ተናገሩ። ቃል አቀባዩ ኔድ ፕራይስ በአፍሪካ ህብረት መሪነት የሚካሄደው የሰላም ንግግር የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት እና ህወሓት “ልዩነታቸውን የሚወያዩበት እና በመካከላቸው ያለውን ርቀት ማጥበብ የሚቀጥሉበት እንደሚሆን ተስፋ እናደርጋለን” ብለዋል። 

ቃል አቃባዩ ይህን ያሉት፤ ስምንተኛ ቀኑን ስላስቆጠረው የኢትዮጵያ መንግስት እና የህወሓት የሰላም ንግግርን በተመለከተ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ትላንት ምሽት በሰጡት መግለጫ ነው። ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ የተጀመረው የሰላም ንግግር እስከ እሁድ ጥቅምት 20 እንደሚቆይ የደቡብ አፍሪካ መንግስት አስታውቆ የነበረ ቢሆንም፤ ንግግሩ እስከ ትላንት ምሽት መቀጠሉን ከቦታው የወጡ ዘገባዎች አመልክተዋል።

በፕሪቶሪያ ከተማ እየተካሄደ ለሚገኘው ለዚህ የሰላም ንግግር የተቀመጠ የቀን ገደብ እንደሌለ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ቃል አቃባይ ኤባ ካላንዶ ትላንት ለፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ተናግረዋል። በንግግሩ ላይ በ“ተሳታፊነት እና በታዛቢነት” እየተካፈሉ የሚገኙት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ማይክ ሐመር፤ ንግግሩ እስከሚያበቃበት ዕለት ድረስ በደቡብ አፍሪካ እንደሚቆዩ ኔድ ፕራይስ ተናግረዋል።

የሰላም ንግግሩ እስከ ረቡዕ ድረስ ይቀጥላል መባሉ የሂደቱን አለመሳካት ያመልክት እንደሆነ የተጠየቁት ፕራይስ፤ ሁለቱ ወገኖች “የተራራቀ” አቋም ይዘው ወደ ደቡብ አፍሪካ ማምራታቸውን የሚጠቁም ነው ብለዋል። የሰላም ንግግሩ መራዘም ሁለቱ ወገኖች “አብረው ለመቀመጥ ፈቃደኛ ሆነው መቀጠላቸውንም አመላካች” ጭምር ሊሆን እንደሚችልም ጠቁመዋል። የደቡብ አፍሪካው ውይይት የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት እና ህወሓት “ልዩነታቸውን የሚወያዩበት እና በመካከላቸው ያለውን ርቀት ማጥበብ የሚቀጥሉበት እንደሚሆን ተስፋ እናደርጋለን” ሲሉም ሀገራቸው ከሰላም ንግግሩ የምትጠብቀውን አመልክተዋል። 

ፕራይስ በትላንቱ ዕለታዊ ጋዜጣዊ መግለጫቸው፤ በኢትዮጵያ ተፋላሚ ወገኖች መካከል የሚደረገው የሰላም ንግግር አራት ግቦች እንዳሉት አስረድተዋል። አፋጣኝ የግጭት ማቆም ላይ መድረስ፣ ለተቸገሩ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ሰብዓዊ ዕርዳታ ማድረስ፣ የሰላማዊ ሰዎችን ደህንነት ለመጠበቅ ተጨማሪ እርምጃዎች መውሰድ እና የኤርትራ ወታደሮች ከሰሜን ኢትዮጵያ መውጣታቸውን ማረጋገጥ ፕራይስ የጠቀሷቸው የሰላም ንግግሩ አራት ዋነኛ ዓላማዎች ናቸው። በደቡብ አፍሪካ እየተካሄደ የሚገኘው የሰላም ንግግር ሁለቱ ወገኖች ”ልዩነቶቻቸውን ለማጥበብ” እና ለአራቱ ግቦች ስኬት “መልካም ዕድል” እንደሆነ ቃል አቃባዩ ጠቅሰዋል። 

ከነገ በስቲያ ሐሙስ ጥቅምት 24፤ 2015 ሁለተኛ ዓመቱን በሚደፍነው የሰሜን ኢትዮጵያዊው ጦርነት የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች እና ግፎች መፈጸማቸውን ያጋለጡ በርካታ ተአማኒ ሪፖርቶች መኖራቸውን በጋዜጣዊ መግለጫቸው ያስታወሱት የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ቃል አቃባይ፤  የሰላማዊ ሰዎችን ደህንነት መጠበቅ አሁንም “አንገብጋቢው ጉዳይ” እንደሆነ ጠቅሰዋል። “በግጭቱ ወቅት በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን የሚገልጹ ሪፖርቶች እጅግ እንደሚያሳስቡን በድጋሚ እንገልጻለን” ያሉት ኔድ ፕራይስ፤ ሁሉም ታጣቂ ኃይሎች መሰል ጥቃቶች አቁመው ለሰላማዊ መፍትሔ ዕድል እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበዋል።

በትላንቱ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት መግለጫ ላይ በተሳተፉ ጋዜጠኞች ከቀረቡ ጥያቄዎች መካከል፤ የኢትዮጵያ መንግስት “ያልተረጋገጡ እና ፖለቲካዊ ዓላማ ያላቸውን ውንጀላዎች” ከሚያቀርቡ ከአንዳንድ ሀገራት እና ተቋማት ጋር ያለውን ግንኙነት መልሶ ለማጤን እንደሚገደድ ማስታወቁን የተመለከተ ይገኝበታል። የኢትዮጵያ መንግስት ላቀረበው ውንጀላ ያቀረበውን “መረጃ” እና “ዓላማውን” መመልከት እንደሚኖርባቸው የገለጹት ኔድ ፕራይስ፤ “የዩናይትድ ስቴትስ ዓላማ፤ በአፍሪካ ህብረት መሪነት የሚካሔደው የሰላም ንግግር ግብ ቀላል ነው። ድብቅ የፖለቲካ ዓላማ የለውም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

በደቡብ አፍሪካ እየተካሔደ ያለውን የሰላም ንግግር በተመለከተ በሳምንቱ መጨረሻ ከቻይናው ሲቲጂኤን የቴሌቭዥን ጣቢያ ጋር ቃለ መጠየቅ ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ፤ “ከግራ እና ከቀኝ የሚደረጉ ጣልቃ ገብነቶች” የሰላም ንግግሩን “ከባድ” ሊያደርጉ እንደሚችሉ ስጋታቸውን ገልጸው ነበር። “ህወሓት የአገሪቱን ህግ እና ህገ መንግስቱን እንዲያከብር ለማሳመን እየሞከርን ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “ጥቅማችንን ተረድተው፤ በህገ መንግስታቸው አምነው በዚሁ መሰረት ቢሰሩ ኖሮ ሰላም ይፈጠር ነበር” ሲሉ ተደምጠዋል።

Exit mobile version