Site icon ETHIO12.COM

መንግስት የሰላም ስምምነቱን መሰረት በማድረግ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እየተገበረ ነው

መንግስት የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት መሰረት በማድረግ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት በተሟላ መልኩ እየተገበረ ነው ሲሉ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ አስታወቁ፡፡

አዎንታዊና ዘላቂ ሰላም የሚመነጨው ከውስጣዊ ፍላጎታችን ነው ያሉት ሚኒስትሩ ውስጣዊ ፍላጎታችን ወደ ውስጥ በመመልከት ቁስላችንን በማከም፣ የህዝቦች እኩል ተጠቃሚነትና አንድነት ማረጋገጥን ማዕከል የሚያደርግና ከእነዚህ ግቦች የሚመነጭ፣ ትልቁን ዓላማና የወደፊቱን ተስፋ የሚመለከት ከሆነ በእርግጥም ለአዎንታዊና ዘላቂ ሰላም መቆማችንን ያስረዳል ብለዋል፡፡

ለዚህም ሲባል ጥቃቅንና ለጊዜው ችግር የሚመስሉ፣ ከዘላቂ ጥቅም አኳያ ግን ፋይዳቸው እምብዛም ጉልህ ያልሆኑ ጉዳዮችን ለዋናው ግባችን ሲባል እንታገሳቸዋለን ብለዋል፡፡

ነገሮችን ውጫዊ በማድረግ፣ ለጊዜው ከጥርጣሬና ፍርሃት የሚመነጩ ችግሮችን በማስተጋባት መጓዝ መቼም ቢሆን ብቻውን የመፍትሄ አካል መሆን እንደማይችል በመጥቀስም ከዚህ አንጻር ተጨባጭ እርምጃዎችን መውሰድ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

በዚሁ አግባብ መንግስት የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት መሰረት በማድረግ የሚጠበቅበትን ሃላፊነት በተሟላ መልኩ እየተገበረ ነው ያሉት፡፡

ሚኒስትሩ አቅም በፈቀደና አጋር አካላት ማቅረብ በቻሉት መጠን የሰብአዊ እርዳታና መድሃኒት በሁሉም አቅጣጫ ወደ ትግራይ ክልል እንዲገባ እያደረገ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

መሰረታዊ አገልግሎቶችን ለማስጀመር በየሴክተሮቹ የሙያተኞች ቡድን ርብርብ እያደረጉ እንደሚገኙ የገለፁት ሚኒስትሩ በአንደንድ አካባቢዎችም አገልግሎት መስጠትም መጀመራቸውን ጠቁመዋል፡፡

ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት ፅሁፍ በየደረጃው ያሉ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎችም ሆኑ መገናኛ ብዙኃን በጥብቅ የሰላም ስምምነቱን መርሆዎች አክብረው እንዲንቀሳቀሱ እያደረገ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ይህ የመንግስት ተጨባጭ ጥረትና ፍላጎት በሌላኛውም ወገን በስምምነቱ መርህ መሰረት ይበልጥ ወደ ተግባር መቀየር ይኖርበታልም ነው ብለዋል፡፡

የሰላም ስምምነቱ መርሆዎች ወደ ተጨባጭ ተግባር እንዳይቀየር እንቅፋት የሚፈጥሩ ሃይሎችንም ፊት ለፊት መታገል እንደሚገባ ጠቁመው፥ ለዘላቂና አዎንታዊ ሰላም የሁሉም ወገን ቅንነት የተሞላበት እንቅስቃሴ ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።

Via walt information

Exit mobile version