Site icon ETHIO12.COM

ከሰላም ስምምነቱ በሁዋላ ብቻ 32 ሺህ ሚትሪክ ቶን እህል ወደ ትግራይ ገብቷል

አዲስ አበባ ኢዜአ ህዳር 18 ቀን 2015 መንግስት እና ህወሃት ያደረጉትን የሰላም ስምምነት ተከትሎ እስከ አሁን ወደ ትግራይ ክልል 32 ሺህ ሜትሪክ ቶን የምግብ እህልና ከ360 ሺህ ሊትር በላይ ነዳጅ ተደራሽ መሆኑን የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ሺፈራው ተክለማርያም ተናገሩ።

በሀገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልድ ኢትዮጵያውያን መንግስት በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች ለመደገፍ እያደረገ ያለውን ጥረት እንዲያግዙም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የፌደራል መንግስትና ህወሃት በሰሜን ኢትዮጰያ ያለውን ግጭት በዘላቂነት ለማቆም ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል።

የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ መንግስት የትግራይ ክልልን ጨምሮ በሰሜን ኢትዮጵያ ሌሎች አካባቢዎችም የሰብዓዊ እርዳታን በስፋት ተደራሽ በማድረግ ላይ ይገኛል።

የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ሽፈራው ተክለማርያም ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት፤ መንግስት የሰላም ስምምነቱን መሰረት በማድረግ ሰብዓዊ ድጋፍ ወደ ትግራይ ክልል ያለ ገደብ ተደራሽ እንዲሆን እያደረገ ነው፡፡

በዚህም በአራት ኮሪደሮች በየብስ እንዲሁም በመቀሌና በሽሬ አውሮፕላን ማረፊያዎች በኩል እርዳታ ተደራሽ እየተደረገ ይገኛል ነው ያሉት።

ከፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት በኋላ እስከ ህዳር 16 ቀን 2015 ዓ.ም ባሉት ጊዜያት መንግስት በራሱ አቅም 13 ሺህ ሜትሪክ ቶን ጥራጥሬና አልሚ ምግብ ተደራሽ አድርጓል ብለዋል።

በእርዳታ ድርጅቶች በኩል ደግሞ 19 ሺህ ሜትሪክ ቶን የምግብ እህል ወደ ትግራይ ክልል ማሰራጨቱን ዶክተር ሽፈራው ገልጸዋል።

ባለፉት ሳምንታት ወደ ትግራይ ክልል የተላከው የሰብዓዊ እርዳታ ከ2 ሚሊዮን በላይ የክልሉ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ነው የተናገሩት።

ከምግብ አቅርቦት ባለፈም ትግራይ ክልልን ጨምሮ በሰሜን ኢትዮጵያ ለሰብዓዊ እርዳታ ማጓጓዣ የሚውል ከ360 ሺህ ሊትር በላይ ነዳጅ ወደ አካባቢው ተልኳል ብለዋል።

መቀሌ የገባው ነዳጅም በዓለም ምግብ ፕሮግራም በኩል ለአስፈላጊው ዓላማ ጥቅም ላይ እንደሚውል አንስተዋል።

መንግስት ከፍተኛ መድሃኒትና የህክምና ቁሳቁስ፣ ለትምህርት ቤቶችና ለአካባቢው ነዋሪ የውሃና ለንጽህና መጠበቂያ የሚያገለግሉ ቁሳቁሶችን ተደራሽ እያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ሰብዓዊ ድጋፉ በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያረጋገጡት ኮሚሽነሩ፤ ለዚህም ከአጋር አካላትና ከዜጎች ጋር በቅንጅት እተየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በአማራና አፋር ክልሎች የተለያዩ አካባቢዎች በነበረው ግጭት የጉዳት ሰለባ የሆኑ ወገኖችን በማገዝ መንግስት እያደረገ ካለው ጥረት ባለፈ የማህበረሰቡም ተሳትፎ የሚደነቅ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይሄው ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።

በጦርነቱ ተፈናቅለው የነበሩ ዜጎችን ወደ ቀያቸው በመመለስ በዘላቂነት ለማቋቋም መንግስት አስተባባሪ ኮሚቴ አደራጅቶ እየሰራ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል።

መደበኛ አገልግሎቶችን ከማስጀመር ጎን ለጎን ዜጎች ወደ መደበኛ ህይወታቸው እስከሚመለሱ ድረስ ሰብዓዊ ድጋፉን አጠናከሮ ለመቀጠልም በቂ ዝግጅት ማድረጉን ነው የተናገሩት።

መንግስት ሀብት ከማሰባሰብ ባለፈ የእርዳታ ድርጅቶችን አቅም ለመጠቀም እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ በሀገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልድ ኢትዮጵያውያን ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።

Exit mobile version