የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ጥገና በአንድ ወር ይጠናቀቃል

በአሸባሪው ሕወሓት በአማራ እና በአፋር ክልሎች ውስጥ ውድመት የደረሰባቸው የኤሌክትሪክ መሠረተ-ልማቶች ጥገና በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ሲል የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አሳወቀ፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በሰሜን ኢትዮጵያ በተካሄደው ጦርነት በሽብር ቡድኑ ውድመት የደረሰባቸው የኤሌክትሪክ መሠረተ-ልማት ጥገና እየተካሄደ ይገኛል፡፡

ሥፍራዎቹ ከሽብር ቡድኑ መላቀቃቸውን ተከትሎ በአስር ቀናት ውስጥ ጉዳቱንና የሚያስፈልገውን ግብዓት ገምግሞ ወደ ሥራ መግባቱን የጠቆሙት አቶ ሞገስ፤ መሥሪያ ቤታቸው ሥራውን ለማጠናቀቅ በሙሉ አቅሙ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል ብለዋል።

ሥራው ፈጥኖ አገልግሎት መጀመር ስለሚገባው በተባለው ጊዜ ለማጠናቀቅም የሁሉም ሪጅን ሠራተኞች በመረባረብ ላይ እንደሚገኙ የገለጹት አቶ ሞገስ፤ በሰሜን ትግራይ ሪጅን ካለው ውጪ ያሉት በሙሉ ተሳትፎ ማድረጋቸውንም ነው አቶ ሞገስ የተናገሩት።

ከወልዲያ እስከ አላማጣ ድረስ ብቻ ሃምሳ አካባቢዎች ላይ ጉዳት ደርሷል ያሉት ዳይሬክተሩ፤ እያንዳንዱን ሠርቶ ለማጠናቀቅ ወደ ሥራ መገባቱንም ነው ያመላከቱት።

በጥገና ሥራው ከተለያዩ ስፍራዎች በሚመጡ ባለሙያዎች ሥራው እንደሚከወን የገለፁት ዳይሬክተሩ፤ ባለው የሠራተኞቹ ርብርብም መሠረት ከታሰበው ፍጥነት በተሻለ መንገድ የሚያልቅበት እድል መኖሩንም ነው የገለጹት።

አቶ ሞገስ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎትም ከመሥሪያ ቤታቸው ቀጥሎ ያለውን ሥራ የመሥራት ሁኔታ ስለሚጠበቅበት ሥራዎች መጀመራቸውን መረጃው እንዳላቸው ጠቁመዋል።

መሥሪያ ቤቱ እየከወነ በሚገኘው ከፍተኛ የኃይል መስመር እንዲሁም ማከፋፈያ ጣቢያ ጋር በተያያዘ ጥገናው ሰሜን ምሥራቅ የሚባለውና ደሴን ማዕከል ያደረገው ሪጅን ብቻ የሚከታተለው ሳይሆን የሁሉም አካባቢዎች ተሳትፎ ያለበት ነው ብለዋል።

በሰሜን ኢትዮጵያ በተካሄደው ጦርነት የወደሙ የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶችን በፍጥነት በመጠገን ለረጅም ጊዜ በጨለማ ውስጥ የቆየው ኅብረተሰብ ኃይል እንዲያገኝ ለማድረግ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ሁሉም ሪጅን የጥገና ባለሙያዎች በርብርብ እየሠሩ እንደሆነ አቶ ሞገስ ጠቁመዋል።

የሽብር ቡድኑ ሕወሓት ኢትዮጵያ ላይ ባወጃቸው ሦስት ዙር ጦርነቶች በደረሰባቸው በሀገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ሁሉ የኅብረተሰቡን መገልገያ የሆኑ ለትምህርት፣ ለጤና፣ ለኤሌክትሪክ እንዲሁም ለሌሎች መሠረተ ልማቶች መገልገያ የሚውሉ ግብዓቶችን ሲያወድም እንደነበር አቶ ሞገስ አስታውሰዋል።

See also  ባለቀይ መለዮ- በቁርጠኝነትና ታማኝነት የታወቀ የውጊያ የማርሽ ቀያሪ

Leave a Reply