Site icon ETHIO12.COM

ደረሰኝ ሻጮቹና አገናኙ ደላላ በፅኑ እስራትና በገንዘብ ተቀጡ

በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዘርፍ የኢኮኖሚ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ህግ ከፖሊስ ጋር በመሆን ግብይት ሳይኖር ከ29 ሚሊየን ብር በላይ ሀሰተኛ ደረሰኝ በማዘጋጀትና በመሸጥ ለግል ጥቅማቸው ባዋሉ ሶስት ግለሰቦች ላይ ምርመራ በማጣራ፤ ዐቃቤ ህግ ክስ መስርቶ ክርክር በማድረግ ከ3 እስከ 14 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ አድርጓል፡፡

ክርክሩ በፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 11ኛ ወንጀል ችሎት የተደረገ ሲሆን

የዐቃቤ ህግ የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው 1ኛ ተከሳሽ ተስፋሁነኝ ተሾመ፣ 2ኛ ተከሳሽ ገነት ኃይሉ፣ 3ኛ ተከሳሽ አብዲ ጃቢር፣ የተባሉት ላይ ዐቃቤ ህግ 10 የተለያዩ ክሶች አቅርቦ በመከራከር ረቷል።

ተከሳሽ ተስፋሁነኝ ተሾመ ሐምሌ 24/2013 ዓ.ም በን/ስ/ላ/ክ/ከተማ ወረዳ 06 ልዩ ቦታው ቄራ ዳውን ታወን አካባቢ ካለው ንግድ ቤት ውስጥ ለ1ኛ የዐቃቤ ህግ ምስክር ግብይት ሳይኖር ደረሰኝ ብቻ እንደምትፈልግ ለ3ኛ ተከሳሽ የነገረችው እና በእርሱ አገናኝነት ደረሰኙ ከሚይዘው ገንዘብ የደላላ 1% እና የደረሰኝ ኮሚሽን 3% እንደምትከፍል ተስማምተው በደላላው አማካኝነት 1ኛ ተከሳሽ ከሚገኝበት ንግድ ድርጅት ከገቡ በኋላ በሀሰተኛ መታወቂያ በአንድ ግለሰብ ስም ከወጣ የሽያጭ መመዝገቢያ ማሽን ላይ ግብይት ሳይኖር 17 ሚሊዮን 940 ሺ ብር ሃሰተኛ ደረሰኝ በማዘጋጀት ቆርጦ ሲሰጣት እጅ ከፍንጅ የተያዘ በመሆኑ በፈፀመው ሀሰተኛ ወይም አሳሳች መግለጫ ማቅረብ ወንጀል የተከሰሰ ሲሆን እንዲሁም ሀሰተኛ ደረሰኞችን ለማዘጋጀትና ለማተም የሚያገለግሉ ማሽኖችን ይዞ በመገኘት ወንጀል በ3 ተደራራቢ ክሶች ክርክር ሲያደርግ ቆይቷል።

በዛው ዕለት የዐቃቤ ህግ ምስክሯ በተጨማሪ ሌላ ደረሰኝ ከሌላ ማሽን እንደምትፈልግ ለ1ኛ ተከሳሽ ስትነግረው ተከሳሹ ስልክ በመደወል ደረሰኝ የሚፈልግ ሰው አለ መጣን በማለት በመዝገቡ ላይ 2ኛ ተከሳሽ የሆነችው ገነት ሀይሉ ከምትገኝበት በልደታ ክ/ከተማ ባልቻ ሆስፒታል አካባቢ ከሚገኝ አህመድ ህንጻ ውስጥ በሀሰተኛ መታወቂያ ስም ከወጣ ህጋዊ ማሽን ላይ ግብይት ሳይኖር 12 ሚሊየን 135 ብር ሃሰተኛ ደረሰኝ በማዘጋጀት ቆርጣ ስትሰጣት እጅ ከፍንጅ የተያዘች በመሆኑ በተጨማሪም ተከሳሿ ምንም አይነት የሽያጭ መመዝገቢያ ለመጠቀም የሚያስችል ህጋዊ ፍቃድ እና ሰነድ ሳይኖራት በሀሰተኛ መታወቂያ ስም የወጣ የሽያጭ መመዝገቢያ መሳሪያ፣ ይዛ የተገኘች በመሆኑ በፈፀመችው ሀሰተኛ ደረሰኞችን ለማዘጋጀትና ለማተም የሚያገለግሉ ማሽኖችን ይዞ በመገኘት ወንጀል፣ ሀሰተኛ ወይም አሳሳች መግለጫ ማቅረብ፣ ግብይት ሳይፈጸም ደረሰኝ መስጠት እና የተጭበረበሩ ደረሰኞችን ማዘጋጀት፣ መሸጥና ማሰራጨት ወንጀል በ4 ተደራራቢ ክሶች ክርክር ስታደርግ ቀይታለች

በሌላ በኩል 3ኛ ተከሳሽ የሆነው አብዲ ጃቢር ከላይ በተገለጸው ሁኔታ ለራሱ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት በማሰብ ሃሰተኛ ደረሰኝ እንዲቆረጥ ለሽያጭ ያመቻቸ እና ሃሰተኛ ደረሰኞች ጥቅም ላይ እንዲውሉ ያደረገ በመሆኑ በፈፀመው የተጭበረበሩ ወይም ህገወጥ የሆኑ ደረሰኞች ለሽያጭ ማመቻቸት ወንጀል በቀረበበትተደራራቢ ክሶች ክርክር ሲያደርግ ቆይቷል።

ዐቃቤ ህግም ሶስቱ ተከሳሾች የማይገባቸውን ጥቅም ለማግኝት በማሰብ ህግን በመተላለፍ ፈጽመውታል ባላቸው 10 የተለያዩ ክሶች ማስረጃ በማቅረብ ክሱን በበቂ ሁኔታ ያስረዳ በመሆኑ የዐቃቤ ህግን እና የተከሳሾችን ክርክር የመራው የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ 11ኛ ወንጀል ችሎትም 1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች በተከሰሱባቸው ክሶች በሙሉ የጥፋተኛነት ፍርድ በመስጠት የቅጣት ውሳኔ በማሳለፍ በአጠቃላይ በ1ኛ ተከሳሽ በ 14 ዓመት ጽኑ እስራት ፣ 2ኛ ተከሳሽ በ12 ዓመት ጽኑ እስራት ፣ እንዲሁም በ3ኛ ተከሳሽ እና የማገናኘት ሥራ የሰራው ተከሰሰባቸው 4 ክሶች መካከል በአንድ ክስ ብቻ የጥፋተኝነት ውሳኔ በማሳለፍ በ3 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ሲወስን ከእስራት ቅጣቱ በተጨማሪ 1ኛ ተከሳሽ የ360 ሺ ብር፣እና 2ኛ ተከሳሽ በ210 ሺ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ሲል ወስኗል፡፡

Exit mobile version