Site icon ETHIO12.COM

በይነመረብ ማህበርዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ለውጥ ለማምጣት!!

“በይነመረብ የማህበርዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ለውጥ ለማምጣት ወሳኝ ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ

ኢትዮጵያ ባለፉት አራት አመታት በኮቪድና በሌሎች ሰው ሰራሽ ችግሮች በተፈተነችበት ወቅት የተለያዩ ተግባራትን በበይነመረብ ማካሄድ ችላለች ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ

[ኢንተርኔትን በተመለከተ] ባለፉት አራት አመታት ኢትዮጵያ ፈተና አጋጥሟታል፣ እድሎችንም አግኝታለች። ለምሳሌ ኢንተርኔት ለሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን አግዟል። በሌላ በኩል ኮቪድ ባጋጠመበት ወቅት አንዳንድስራዎችን በኢንተርኔት አማካኝነት ለመስራት እድል ፈጥሯል።
አሁን ላይ የኢንተርኔት ነፃነት ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ ገብቷል። ትልልቅ ፕላትፎርሞች ተጠቃሚዎች የሚያገኟቸውን መረጃዎች ተቆጣጥረዋል። በፖለቲካም በርካቶችን ተሳታፊ ቢያደርግም ሉአላዊነትን፣ የዴሞክራሲ ባህሎችን እና የፖለቲካ መረጋጋት ላይ ጥላውን አጥልቷል።
ከዚህም በተጨማሪ የሀሰተኛ መረጃ እና የአሉባልታዎች በማይታወቁ አካላት እንዲሰራጩ እድል ከፍቷል። ጠ/ሚር አብይ አህመድ ዛሬ በተጀመረው የኢንተርኔት አስተዳደር ጉባኤ (IGF) ላይ ከደቂቃዎች በፊት ከተናገሩት የተወሰደ:

በይነመረብ ማህበርዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ለውጥ ለማምጣት ወሳኝ መሆኑንም ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በ17ኛው የአለም አቀፍ የበይነመረብ ጉባኤ ላይ ተገኝተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለጹት፣ በይነመረብ ለአፍሪካ አህጉር እድገት ወሳኝ ነው። ኢትዮጵያ ባለፉት አራት አመታት በኮቪድና በሌሎች ሰው ሰራሽ ችግሮች በተፈተነችበት ወቅት ስራን በበይነመረብ ማካሄድ ችላለች።

በይነመረብን በአግባቡ በመጠቀም የባህል፣ የኢኮኖሚና በሌሎች ዘርፎች ለውጥ ማምጣት ይቻላል።

ኢትዮጵያ ለዘርፉ ትኩረት በመስጠት በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ፣ በትኩረት እየሰራች ነው፤ ያላትን የህዝብ ቁጥር ያማከለ የኢንተርኔት ተደራሽነት ለማሳደግ በስራቸው ስራ ብዙ ለውጦች አምጥታለች ብለዋል።

አፍሪካ የበይነመረብን በአግባቡ ለመጠቀምና ለእድገት ለማስመዝገብ ደህንነቱ የተጠበቀ የበይነመረብ አስተዳደር ሊኖራት እንደሚገባ ገልጸዋል።

ለጉባኤው ተሳታፊዎች እንኳን ደህና መጣችሁ፣ መልካም ቆይታ እንዲኖራቸው መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኖዮ ጉተሬዝ በ17ኛው አለም አቀፍ የበይነመረብ ጉባኤ ላይ በዙም ታግዘው ባደረጉት ንግግር አለም ወድፊት ደህንነቱ የተረጋገጠ የጋራ ተጠቃሚነትን ያማከለ ሊሆን ይገባል ብለዋል።

አለም በቀጣይ አስተማማኝና አካታች የዲጂታል ደህንነት ያስፈልጋልም ብለዋል።

ከትላንት ህዳር 19 እስከ ህዳር 23 ቀን 2015 ዓ.ም እየተካሄደ በሚገኘው 17ኛው ዓለም አቀፍ የበይነመረብ አስተዳደር ጉባኤ ላይ ከሶስት መቶ በላይ ሁነቶች በሚከናወኑበት ጉባኤው ላይ ኢትዮጵያን ለውጭው ዓለም በበጎ ጎን የሚያስተዋውቁ ልዩ ልዩ ተግባራት ይከወናሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በጉባኤው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን ጨምሮ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤና የተለያዩ የውጭ ሀገራት ተወካዮች ተገኝተዋል።

በሞገስ ተስፋ እና በዳግማዊት ግርማ

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት

Exit mobile version